ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ጦር በመልሶ ማጥቃቱ ‘ጥሩ እመርታ’ እያሳየ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቀች
ዩክሬን በወረራ የተያዙባትን ግዛቶች ከሩሲያ ለማስመለስ በምታደርገው መልሶ ማጥቃት ‘ጥሩ እመርታ እያሳየች’ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቀች።
ዩክሬን፣ የሩሲያ ጦር በከፍተኛ ሁኔታ በተከማቸበት ደቡባዊ ክፍል ‘ጎልተው የታዩ’ ግስጋሴዎችን እንዳደረገችም ነው የተሰማው።
የዋይት ሃውስ የደህንነት ቃለ አቀባይ ጆን ከርቢ እንዳሉት በዛፖሪዝሂያ በስተደቡብ በኩል የዩክሬን ጦር በባለፉት 72 ሰዓታት ውስጥ ድሎችን ተቀናጅቷል ብለዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ የዩክሬን ኃይል እየገሰገሰ ቢሆንም “ጠንካራ ውጊያ እየተካሄደ ነው” ሲሉ ለሲኤኤን ተናግረዋል።
ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው በኩፒያንስ ከተማ አቅራቢያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ኮረብታማ ስፍራ ተቆጣጥሬያለሁ ብላለች።
ሁለቱም አገራት በአውደ ውጊያዎች ላይ ድልን ተቀዳጅተናል ማለታቸውን ቢቢሲ በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።
ቃለ አቀባዩ በበኩላቸው ዩክሬን በደቡባዊ ግዛቷ በኩል እያደረገችው ግስጋሴ ሩሲያን ከክሪሚያ የሚያገናኛትን የመሬት መተላለፊያ መስበር ቢሆንም ከተጠበቀው በላይ መዘግየቱን አምነዋል።
የዩክሬን ጦር በዛፖሪዝሂያ ክልል የምትገኘውን የሮቦቲኒን ግዛት መቆጣጠሩን ተናግሯል።
ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን ጦር ነጻ ያወጣቸውን ግዛቶች ለማስመለስ በርካታ ጦር አሰማርታለች።
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው በደቡባዊ የዩክሬን ግዛቶች ከፍተኛ ሰራዊቷን ከማሰማራት በተጨማሪ፣ ከባድ መሳሪያዎች፣ 'የድራጎን ጥርስ’ የተሰኙ የኮንክሪት ጸረ-ታንክ ማገጃዎች፣ እንዲሁም የተራቀቁ ምሽጎች፣ ዋሻዎች እና መተላለፊያዎች እንደገነባች ይታመናል።
ዩክሬን ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን የጀመረችው ከምዕራቡ ዓለም አጋሮቿ የጦር መሳሪያዎች ካገኘች በኋላ ነው።
የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ግስጋሴ አዝጋሚ መሆኑ ሲገለጽም ቆይቷል።
ኪዬቭ የኔቶ አገራት ታንኮች፣ ፈንጂ ማምከኛ፣ በተለይም አሜሪካ ሰራሹ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ የጦር አውሮፕላኖች እንዲሰጧት መወትወቷን ቀጥላለች።
ሐሙስ እለት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኩሌባ የዩክሬንን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መዘግየቱን የሚተቹትን ወቅሰዋል።
“ሁሉም ተቺዎች ዝም እንዲሉ እመክራለሁ። ወደ ዩክሬን መጥተው አንድ ኢንች መሬት በራሳቸው ነጻ ለማውጣት ሞክሩ” ሲሉም በስፔን በነበረው የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉባኤ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።