በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአዲስ አበባ ከተያዙት መካከል የተሰወሩ እና ወደ አዋሽ አርባ የተወሰዱ አሉ ተባለ

በአማራ ክልል ከተቀሰቀው ግጭት ጋር በተያያዘ እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የተሰወሩ እና ወደ አዋሽ አርባ የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።

ኢሰመጉ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር በተያያዘ በርካታ የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነ አርብ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

እየተፈጸሙ ያሉት እስሮች “የሕግ ሥነ ሥርዓት ያልተከተሉ እና አንዳንዶቹም አስገድዶ የመሰወር ባህርይ” እንዳላቸው ኢሰመጉ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች እንደነገሩት አስፍሯል።

በከተማዋ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በፌደራል ፖሊስ አንዳንዶቹም የሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው መኪኖች አፋር ክልል ወደሚገኝ አዋሽ አርባ የተወሰዱ እንዳሉ ነው ከቤተሰቦች መረጃ የሰበሰበው።

ኢሰመጉ የቤተሰቦቹን ቅሬታ አስመልክቶ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በደብዳቤ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ነው በመግለጫው ያተተው።

ከእነዚህም መካከል ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ከቤተሰቦቹ ሰምቷል። ጋዜጠኛው ነሐሴ 15/ 2015 ዓ.ም ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱንም ቤተሰቦቹ ከተለያዩ ምንጮች እንደሰሙ ነገር ግን ማረጋገጥም እንዳልቻሉ አስፍሯል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለው የአልፋ ሚዲያ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ያለበት እንደማይታወቅ ተገልጿል።

እንዲሁም አቶ ዳንኤል መላኩ የተባለ ግለሰብ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አካባቢ በሥራ ላይ እያለ ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም. ሁለት ሰሌዳ በሌላቸው መኪናዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተወስዶ ያለበት እንደማይታወቅም አስፍሯል።

በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር ያለመከሰስ መብታቸው እንዳልተነሳ እንዲሁም ያሉበትን ማወቅ እንዳልተቻለ ኢሰመጉ አስታውቋል።

የምክር ቤት አባላቱ ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም. ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ፖሊስ ግለሰቦቹን አለማቅረቡን እና ያሉበት እንዳልታወቀ ነው ኢሰመጉ የገለጸው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” በማለት በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ውስጥ የምክር ቤት አባላት መካተታቸው ይታወሳል።

የምክር ቤት አባላቱ ታስረውበት ከነበረው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የማቆያ ቦታ እንደሌሉ እና ያሉበትን ቦታ ማወቅ እንዳልቻሉ ከጠበቆቻቸው አንዱ ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል።

ኢሰመጉ በአማራ ክልል በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየደረሱ እንደሚገኝ በዛሬው መግለጫው አካቷል።

በባሕር ዳር፣ መራዊ፣ ደምበጫ፣ አማኑኤል፣ ሉማሜ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ብቸና፣ ደብረ ታቦር፣ ወረታ፣ አዲስ ዘመን እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ እስር፣ ዘረፋ እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት ቀጥሏል ብሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች እንቅስቃሴ መገደቡን ያተተው መግለጫው ተጨማሪ የምርመራ ሥራ በማከናወን ዘርዘር ያለ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ጠቁሟል።

ኢሰመጉ “በአማራ ክልል እየተስተዋለ ያለውን የንጹሃን እልቂት፣ የንብረት ውድመት እና በአጠቃላይ የሰላም እጦት ከዚህ የከፋ ሁኔታ ላይ ከመድረሱ በፊት በጦርነት መፍትሄ ላይ መድረስ እንደማይቻል ታውቆ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው” ጠይቋል።

ሌላው ኢሰመጉ በመግለጫው ያካተተው ጉዳይ አዲስ የተመሠረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን ነው።

በአሌ ልዩ ወረዳ የዞን መዋቅር ተሰጥቶታል መባሉን ተከትሎ ነሐሴ 14/ 2015 ዓ.ም. ደስታቸውን በመግለጽ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶ ሕይወት ጠፍቷል ብሏል። የተጠረጠሩ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ገልጿል።

በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቀደም ሲል በገበሬ ማኅበር ተከልሎ ሲተዳደር የቆየውን ቆላ ሻራ ቀበሌን ወደ አርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ለመከለል በሚል በተፈጠረ አለመግባባት ከነሐሴ 12/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የፌደራል ፖሊስ፣ የአካባቢው ፖሊስ እና አድማ በታኝ ኃይል በጋራ ወደ ቀበሌው በመግባት በነዋሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎች መግደላቸው ሰፍሯል።

አንዳንድ የሟች ቤተሰቦችም አስከሬን ወስደው እንዳይቀብሩ መከልከላቸውን እንዲሁም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤቶች በማፈስ ወዳልታወቀ ስፍራ እየወሰዱ በማሰር ላይ እንደሚገኙ እና ዘረፋዎችም ጭምር እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ መረጃ ሰብስቤያለሁ ብሏል።

በተመሳሳይ የዲራሼ ልዩ ወረዳ በዞን አስተዳደር እንዲደራጅ በመወሰኑ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

እንዲሁም በዚሁ ዞን የፀጥታ ኃይሎች በመኖሪያ ቤቶች በማገት እስር እየፈጸሙ እና ሴቶችንም ባሎቻችሁን አምጡ እያሉ እያንገላቱ መሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢዎቹ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመገንዘብ መቻሉን ገልጿል፡፡

ኢሰመጉ በአዲስ አበባ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በቆላ ሻራ ቀበሌ፣ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ በዴራሼ ዞን እና በአሌ ዞን በፀጥታ አካላት የሚፈጸሙ ሕግን ያልተከተሉ የጅምላ እስሮች፣ አስገድዶ የመሰወር ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና የታሰሩ ሰዎች ያሉበት ስፍራ ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል።