ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማይክ ሐመር በአማራ እና በኦሮሚያ ያሉ ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ለመወያየት ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ለመወያየት ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው።
ልዩ መልዕክተኛው በኬንያ እና በኢትዮጵያ ከትናንትና ሰኞ ነሐሴ 22 አስከ ጳጉሜ 3/2015 ዓ.ም. ድረስ ለአስር ቀናት ቆይታ እንደሚያደርጉም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸው በዋነኝነት ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር የሚወያዩ ይሆናል።
በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በቀጠሉ ግጭቶች በርካታ ንጹሃን መገደላቸው እና መቁሰላቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ልዩ መልዕክተኛውም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ጥበቃ አስፈላጊነትን ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደሚያነሱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።
ልዩ መልዕክተኛው ወደ አህጉሪቱ ከመምጣታቸው በፊት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ሰላማዊ እልባት እንዲያገኙ አገራቸው፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት እንዴት መደገፍ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ከኅብረቱ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ነበር።
ማይክ ሐመር በአውሮፓ አገራት ስዊድን እና ብራሰልስ ከነሐሴ 13 አስከ ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም. በነበራቸው ቆይታ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር ከሁለቱ ክልሎች ግጭቶች በተጨማሪ የፕሪቶሪያውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዲተገበር እያደረጉት ባለው የጋራ ጥረት ዙሪያም መክረዋል።
በአማራ ክልል ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበው ውጊያ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ በደብረ ታቦር ከተማ ካለፍነው ቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ውጊያ ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እስከ ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ዓ. ም. ረፋድ ድረስ በቀጠለው ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት እና ለጉዳት መዳረጋቸው እንዲሁም ደብረ ታቦር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል።
በአማራ ክልል በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት አስታውቀው ነበር።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ከፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌዴዮን ጢሞቲዮስ ጋር በመሆን ማብራሪያ የሰጡት አቶ ደመቀ ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለማግኘት ስለተጀመረው ጥረት ዝርዝር መረጃ ስለመስጠታቸው የተባለ ነገር የለም።
በፌደራሉ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም መካከል እየተካሄደ ያለውን እና ለበርካታ ነዋሪዎች ሰቆቃ ምክንያት የሆነውን ጦርነት ለመቋጨት በራስ ገዟ አስተዳደር ዛንዚባር ውይይት ቢካሄድም ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱ ይታወሳል።
ማይክ ሐመር በተጨማሪም ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን ከአስራ አንድ ወራት በፊት የተፈረመውን የፕሪቶሪያውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸም አስመልክቶም ከባለሥልጣናቱ ጋር ይነጋገራሉ።
ልዩ መልዕክተኛው በአገራቱ በሚያደርጉት የአስር ቀናት ቆይታ ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ባለሥልጣናት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ።
በቀጣናው የእርስ በርስ ጦርነት እየበጠበጣት ባለችው ሱዳን የተከተለውን ቀውስ፣ ጦርነቱን ለማቆም እየተደረጉ ያሉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶች፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የማስፈን አስፈላጊነትን እንዲሁም ፍትህ እና ተጠያቂነት መደገፍን በተመለከተም ከተለያዩ አመራሮች ጋር ንግግር ያደርጋሉ።
ማይክ ሐመር በአውሮፓ ቆይታቸውም የሱዳንን ግጭት አንስተው ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር የመከሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም በስቶክሆልም የዓለም የውሃ ሳምንትም ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
በስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም እና የምርምር ተቋም አማካኝነት በተካሄደው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅን እያወዛገበ ያለውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተም አንደኛው ተናጋሪ እንደነበሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አሜሪካን በመወከል የታላቁ የሕዳሴ ግድብን የሚከታተሉት ማይክ ሐመር ከውሃ አስተዳደር፣ አጠቃቀም እና ተደራሽነት ጋር የተያያዙ ስምምነቶች ለአፍሪካ ቀንድ ፀጥታ እና መረጋጋት እንዴት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ በሚለውም ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።
ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ነሐሴ 21/2015 ዓ.ም. ተጀምሮ በማግሥቱ ነሐሴ 22/ 2015 ዓ.ም መጠናቀቁ ተገልጿል።
የሦስትዮሹ የመጀመሪያው ዙር ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ዙሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አሠራር ላይ ያተኮረ እንደነበር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።
የአገራቱ ተወካዮች ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ስምምነት ላይ ለመድረስም ሃሳብ መለዋወጣቸውን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀጣዩም ዙር መስከረም 2016 በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መግባባት ላይ ተደርሷልም ብሏል።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላትን ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ በተመሠረተም የሦስትዮሽ ድርድር ስምምነትም ላይ እንዲደረስ እንደምትጥር ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የሚያስረዳው።
ግድቡን በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር በመጨረሻ ከሁለት ዓመታት በፊት ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።
ግብፅ እና ሱዳን ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ስምምነት በሦስቱ አገራት በኩል እንዲፈረም፣ ይህ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባት ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፤ ይህንንም አስመልክቶ የግድቡን የውሃ ሙሌት በመቃወም ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወቀሳ የተሞላበት ደብዳቤ አስገብታ ነበር።
የዘንድሮው ሙሌት እስከ መስከረም መጀመሪያ እንደማይከናወን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።
“ኢትዮጵያ የሱዳንን እና ግብፅ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የሕዳሴ ግድብ ሙሌቱ እስከ መስከረም መጀመሪያ አታከናውንም” ብለው ነበር።
የግድቡ ሙሌት ስለመከናወኑ አንዳንድ መረጃዎች ቢወጡም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።