የካፒቶል ሂል አመጽን የመራው ግለሰብ የ18 ዓመት እስራት ተፈረደበት

በአሜሪካው ካፒቶል ሂል የተነሳውን ነውጥ መርቷል የተባለው ‘ፕራውድ ቦይስ’ የተሰኘው የቀኝ ጽንፈኛ አክራሪው ቡድን ሁለት አባላት እስር ተፈረደባቸው።

የቡድኑ አባል የ46 ዓመቱ ዶሚኒክ ፔዞላ በፖሊስ ላይ ጥቃት በማድረስ እንዲሁም መንግሥታዊ ስራዎችን በማደናቀፍ ክስ ቀርቦበት የ10 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ የምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነውጠኞችን መርቷል የተባለው የ32 ዓመቱ ኢታን ሮርዲያን ከበድ ባለ በአመጽ ሴራ ክስ 18 ዓመት ተፈርዶበታል።

የቡድኑ የቀድሞ መሪ ኤንሪኩ ታሪዮ በሚቀጥለው ሳምንት የእስር ቅጣት ይወሰንበታል።

በከባድ የሴራ ዓመጽ 18 ዓመት የእስር ቅጣት የተፈረደበት ሮርዲያን ከብያኔው በፊት “በእለቱ በነበረው የአመራር ጉድለቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል።

አክሎም የተነሳውን ሁከት “ፍጹም አሳዛኝ” መሆኑንም ነው የገለጸው።

“በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበደልኳችሁ ሁሉ ይቅርታ አድርጉልኝ” ሲልም ተናግሯል።

ነገር ግን የአሜሪካ ግዛት ዳኛ ቲሞቲ ኬሊ በዕለቱ የተከሰቱት ክስተቶች አገሪቷ ረዘም ላለ ጊዜ የገነባችውን የፖለቲካ ባህልን የገረሰሰ እንደሆነ የተናገሩት።

“በዚህች አገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከሌለን ምንም የለንም” ሲሉ ዳኛ ቲሞቲ ተናግረዋል።

ሩፊዮ ፓንማን በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ኖርዲያን ጸረ-ፋሺስት እና ዘረኝነትን ከሚታገለው አንቲፋ ከተሰኘው ቡድን ጋር በተደጋጋሚ ፍጥጫ ውስጥ በመግባትም ይታወቃል።

የፕራውድ ቦይስ አባሉ ኖርዲያን ቅጣት ለካፒቶል አመጽ ከተበየኑት ረዥሙ እስራት አንዱ ነው። ‘ኦዝ ኪፐርስ ሚሊሻ’ የተሰኘው ሌላ የቀኝ ጽንፈኛ አክራሪ ቡድን መሪ ስቱዋርት ሮድስ የ18 ዓመት እስር ከወራት በፊት ተፈርዶበታል።

አርብ ዕለት የተፈረደበት የ46 ዓመቱ የቀድሞ የአሜሪካ የባህር ኃይል አባል ሲሆን ከፖሊስ ጋር በመታገል እንዲሁም መስኮት መስበሩም ተገልጿል።

የካፒቶል ሂል አመጽ ከተነሳ ሁለት ዓመት ሊደፍን ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ መሸነፍ ያልተቀበሉ ነውጠኛ ደጋፊዎች የጆ ባይደንን የምርጫ አሸናፊነት በመቃወም የምክር ቤት አባላቱን ጉባኤ ማወካቸው ይታወሳል።

የምክር ቤቱ አባላት ይነጋገሩ የነበረውም የጆ ባይደንን መመረጥ ለማጽደቅ ነበር።

ከዚህ የካፒቶል ሂል ግርግር ትንሽ ቀደም ብሎ በምርጫ ተሸንፈው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸውን እስከመጨረሻው እንዲፋለሙ ቀስቅሰው ነበር።