እስራኤል በቀይ መስቀል የጋዛ ማዕከል አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት 22 ፍልስጤማውያን ተገደሉ

የቀይ መስቀል መኪና

የፎቶው ባለመብት, AFP

እስራኤል በጋዛ በአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ማዕከል አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት 22 ፍልስጤማውያን ተገደሉ።

የቀይ መስቀል ቢሮዎችም በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተቋሙ ያስታወቀ ሲሆን በግቢው ዙሪያ ተጠልለው የነበሩ 22 ሰዎችም ተገድለዋል።

አርብ ከሰዓት በኋላ የተፈጸመው ጥቃት ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቢሮ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች በሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

ቀይ መስቀል ጥቃቱን አውግዞ በሰላማዊ ሰዎች እና በረድዔት ተቋማት ማዕከላት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም አካላት ጥንቃቄዎችን የማድረግ ግዴታ አለባቸው ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃለ አቀባይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በመጀመሪያ ምልከታ ጦሩ በአካባቢው ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት እንደሌለ ቢጠቁሙም ጥቃቱ እየተገመገመ ነው ብለዋል።

“ጥቃቱ የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት ቢሮዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በዙሪያው በርካታ ፍልስጤማዊ ባልደረቦቻችንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው ድንኳኖች ይገኛሉ።” ሲል ቀይ መስቀል አስታውቋል።

በጥቃቱም 22 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 45 ሰዎች መቁሰላቸውን ያስታወቀው ቀይ መስቀል ሌሎች ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳሉ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል። በርካቶችም በአቅራቢያው ወደሚገኘው የቀይ መስቀል ሆስፒታል መጉረፋቸውን ተቋሙ ገልጿል።

ቀይ መስቀል በቅርብ ቀናት እንዲህ ዓይነት የከፉ የጸጥታ ችግሮች እያጋጠሙ እንደሆነ ገልጾ ይህ ጥቃትም አንዱ ነው ብሏል።

መግለጫው አክሎም “እነዚህን የሰብዓዊ የረድዔት ተቋማትን እና ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ክስተቶችን እናወግዛለን” ብሏል።

የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በጥቃቱ 25 ሰዎች ሲገደሉ 50 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጾ ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ37 ሺህ 390 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው ተወስደዋል።