ሲጨፍሩ የታዩት የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር “ኃላፊነታቸውን ችላ ብለዋል” በሚል ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ተባሉ

የፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን፣ ነሐሴ ወር ላይ በአንድ ፓርቲ ላይ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ከወጣ በኋላ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል በሚል ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ተባሉ።

የ36 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጓደኞቻቸው እና ከሌሎች ዝነኞች ጋር ሲጨፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ አፈትልኮ ከወጣ በኋላ ራሳቸውን ሲከላከሉ ቆይተዋል።

በርካታ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትሯ ድርጊት “የፊንላንድን ስምና ደኅንነት” ጎድቶታል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ የፍትሕ ሚኒስትሩ ቱማስ ፖይስቲ፣ ማሪን የጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነታቸውን ችላ አላሉም ብለዋል።

ፖይስቲ “ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሥራቸው አፈጻጸም ሕገ ወጥ ድርጊት ፈፅመዋል፣ አሊያም ኃላፊነታቸውን ቸልተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ምንም ምክንያት የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንዶች “በቪዲዮው ላይ ‘ናርኮቲክ’ [ዕጽ] የሚል ድምጽ ሰምተናል” ሲሉ አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ያለውን ጥርጣሬ ለማጥራት ማሪን የአደገኛ ዕፅ ምርመራ አድርገዋል። ውጤቱም ከዚህ ነጻ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቪዲዮው የተቀረጸው በአንድ የግል ቅጥር ግቢ ውስጥ ምሽቱን ከጓደኞቻቸው ጋር እያሳለፉ እንደነበር ተናግረዋል።

ቪዲዮውን በተመለከተ በጋዜጠኞች ሲጠየቁም “እኔም ሰው ነኝ። በዚህ ደመና መሃል ደስታ፣ ብርሃን እና ጨዋታን እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ይህ አጋጣሚም በርካታ ሴቶች ማሪንን እንዲደግፉ አድርጓቸዋል።

በፊንላንድ በራካታ ሴቶች በጋራ ሲጨፍሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አጋርተዋል።

አሜሪካዊቷ ፖለቲከኛ ሂላሪ ክሊንተንም ጠቅላይ ሚኒስትሯ መደነሳቸውን እንዲቀጥሉ ነግረዋቸው ነበር። ለዚህ አስተያየታቸውም ማሪን በአደባባይ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ማሪን በ34 ዓመታቸው ሥልጣን ላይ የወጡት እንደ አውሮፓውያኑ 2019 ሲሆን በዓለም ወጣቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።

የፊንላንድ የጤና፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው ግራ ዘመም ተደርገውም ይታያሉ።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በፈፀመችበት የመጀመሪያ ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜያቸው ምን እንደሚመስል አሳይተዋል።

ለሩሲያ ወረራ ምላሽ ለመስጠት ሕዝባዊ ድጋፍ ከጨመረ በኋላ የምዕራቡ ዓለም የመከላከያ ጥምረት አባል ለመሆን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅትን [ኔቶ] ለመቀላቀል ማመልከቻ አቅርበዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ በግብፅ የሚካሄደውን ኮፕ27 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ሌሎች የዓለም መሪዎችን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።