የጁሊ ምህረቱ ሥዕል በዓለም በከፍተኛ ገንዘብ በመሸጥ የአፍሪካ ክብረ ወሰንን ሰበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊት ጁሊ ምህረቱ የሥዕል ሥራ ዳግም የአፍሪካን የጥበብ ሥራ ክብረ ወሰን በመስበር በጨረታ በትልቅ ዋጋ የተሸጠላት አፍሪካዊት አርቲስት ሆነች።
ባሳለፍነው ረቡዕ ኅዳር 5/2016 ዓ.ም. በኒው ዮርክ በተካሄደ ጨረታ ዎከርስ ዊዝ ዘ ዶውን ኤንድ ሞርኒንግ የተሰኘው የሥዕል ስራዋ በ10.7 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።
ይህ በሸራ ላይ የተሳለ የጥበብ ሥራ ስያሜውን ያገኘው ላንግስተን ሂዩስ እአአ በ1920 ካሳተመው ግጥም ነው።
የ52 ዓመቷ ጁሊ የተወለደችው በኢትዮጵያ ሲሆን በፖለቲካዊ ምክንያት በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከቤተሰቧ ጋር ወደ አሜሪካ አምርታለች።
ጁሊ ምህረቱ ትልቅ ዕድገት እያሳየ ባለው ዘመናዊ የአፍሪካ የሥነ-ጥበብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ዝናን ካፈሩ ሰዓሊያን መካከል አንዷ ነች።
ጁሊ ይህን ክብረ ወሰን የሰበረውን ዎከርስ ዊዝ ዘ ዶውን ኤንደ ሞርኒንግ የተሰኘውን ሥዕሏን የሳለችው እአአ 2005 ላይ ሄሪኬን ካትሪና የተባለው ንፋስ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ኒው ኦርሊያንስ ከተማ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ላይ ነበር።
ሥዕሉን ለመግዛት ሁለት ተጫራቾች እየተፎካከሩ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ 9.5 ሚሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ሌሎች ክፍያዎች ተጨማምረው አጠቃላይ ዋጋው 10.7 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, SOTHEBY'S
ጁሊ ምህረቱ በተመሳሳይ የሥዕል ሥራዋ በከፍተኛ ክፍያ በመሸጡ ቀደም ሲልም የአፍሪካ አሜሪካዊ አርቲስት ክብረ ወሰንን የያዘ ነበር።
ይህም ሥራዋ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ 9.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢን በማስገኘቱ ነው ቀዳሚ ሆኖ የቆየው።
‘ዎከር ዊዝ ዘ ዶን ኤንደ ሞርኒንግ’ የተባለው እና በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ክፍያ የተፈጸመበት የሥዕል ሥራዋ የተለያዩ ቀለማትን እና የሥዕል ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን የሥዕሉ አጫራች ሶዝቢስ ገልጿል።
ይህ የጁሊ የሥዕል ሥራ በዚህ ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለሽያጭ መብቃቱ በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ላለው ለወቅታዊው የአፍሪካውያን የአብስትራክት ሥዕል የጥበብ ሥራ ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን አመላካች ነው ተብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሶዝቢስ የአፍሪካ ዘመናዊ እና ወቅታዊ የጥበብ ሥራዎች ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሃናህ ኦሌሪ ባለፈው ወር ‘አርት’ ለተባለው ጋዜጣ እንደተናገሩት የጥበብ ሥራዎቹ ዋጋ “ከመጀመሪያ ደረጃ ከፍ ወዳለው ደረጃ እየተሸጋገሩ” መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱ በጥበብ ሥራዎቿ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከፍ ያለ ዕውቅናን ያገኘች አርቲስት ስትሆን ሥራዎቿንም በተለያዩ ታላላቅ ኤግዚቢሽኖች ስታሳይ ቆይታለች።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የጀርመኑ ታዋቂ የመኪና አምራች ኩባንያ ቢኤምደብሊው ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርበውን ተሽከርካሪውን በጥበብ ሥራዋ እንድታስውብለት መርጧታል።
የቢኤምደብሊው ‘አርት ካር’ በጁሊ የሥዕል ጥበብ ካጌጠ በኋላ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት በሚካሄደው ‘ለ ሜንስ’ በተባለው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናል።












