በዩኬ ዝቅተኛው የመራጮች ዕድሜ 16 እንዲሆን የሚጠይቅ ረቂቅ ለምክር ቤት ሊቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ዝቅተኛው ድምጽ መስጫ ዕድሜ 16 ዓመት እንዲሆን የሚያስችል ረቂቅ ዛሬ ለምክር ቤት ሊቀርብ ነው።
ረቂቁ ለፖለቲከኞች የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ እና የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትን በተመለከተም ገደቦች ያስቀምጣል።
የምርጫ ጣቢያዎችን በባቡር ጣቢያዎች እና መደብሮች አካባቢ በመክፈት ሙከራ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የመራጮችን ዝቅተኛ ዕድሜ 16 ማድረግ፤ ታዳጊዎች በዴሞክራሲ ሒደት ተሳታፊነታቸው እንዲጨምር እና ድምጻቸው እንዲሰማ ያስችላል ተብሏል።
ዝቅተኛው ድምጽ መስጫ ዕድሜን 16 ዓመት ማድረግን የሚቃወሙ ፖለቲከኞች በበኩላቸው ታዳጊዎቹ በሕይወት በቂ ልምድ አለማካበታቸውን እንደ መከራከሪያ አቅርበዋል።
የዩኬ ትይዩ መንግሥት ጸሐፊ ሰር ጄምስ ከቭለሪ "ሰዎች አዋቂ የሚሆኑት 18 ዓመት ሲሞላቸው ስለሆነ እንደ መምረጥ ያሉ የዜግነት መብቶች ሊሰጧቸው የሚገባው 18 ዓመት ሲሞላቸው መሆን አለበት ብለን ወግ አጥባቂዎች እናምናለን" ብለዋል።
ስኮትላንድ እና ዌልስ ውስጥ በሚካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎች ዝቅተኛው ድምጽ መስጫ ዕድሜ 16 ነው።
በኢንግላንድ እና ሰሜን አየርላንድ የአካባቢ ምርጫ እንዲሁም በዩኬ ብሔራዊ ምርጫ ደግሞ ዝቅተኛው ድምጽ መስጫ ዕድሜ 18 ነው።
ዝቅተኛው የመራጮች ዕድሜ 16 ዓመት እንዲሆን የሚጠይቅ ረቂቅ ለምክር ቤት መቅረቡ፤ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1969 ወዲህ የምርጫ ሕግ ላይ የተደረገ ጉልህ ማሻሻያ ነው።
በ1969 ዝቅተኛው የመራጮች ዕድሜ ከ21 ወደ 18 ዓመት እንዲወርድ ተወስኗል።
ረቂቁ በሕዝብ እንደራሴዎች ይሁንታ አግኝቶ እስከሚተገበር ድረስ ወራት ይወስዳል። ቀጣዩ የዩኬ አገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄደው እአአ በ2029 ነው።
ዝቅተኛው የመራጮች ዕድሜ 16 ዓመት መሆኑን የሚቃወሙ ተቺዎች እንዳሉት፤ ታዳጊዎች በብዛት ለግራ ዘመም ፖለቲከኞች ድምጻቸውን እንደሚሰጡ በማሰብ የተዘጋጀ ረቂቅ ነው።
ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሌበር ፓርቲ በበለጠ የወጣቶች ድጋፍ ያለው ግሪን ፓርቲ ነው።
በአገሪቱ የ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች ብዛት ከጠቅላላ ሕዝቡ 3% ይሆናል።
አጥኚዎች እንደሚሉት፤ ታዳጊዎች እምብዛም ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ስለማይታሰብ የሕግ ለውጡ በምርጫ ውጤት ላይ ሰፊ ለውጥ ያመጣል ለማለት ያስቸግራል።
የሊበራል ዴሞክራት ካቢኔ ቃል አቀባይ ሊሳ ስማርት በበኩላቸው "ዝቅተኛው የድምጽ መስጫ ዕድሜ 16 መሆን የነበረበት ከዚህ ቀደም ነበር። ረቂቁ ብቻውን ካለንበትን የዴሞክራሲ ቀውስ አያወጣንም" ብለዋል።
"ፍትሐዊ ያልሆነውን የምርጫ ሥርዓታችንን ማረም አለብን። የአገሪቱ ላዕላይ ምክር ቤት ዴሞክራሲያዊ መሆን ይገባዋል። የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነትንም እናስወግድ" ሲሉ አክለዋል።
በዩኬ ፖለቲከኞች የገንዘብ ድጋፍ መቀበል የሚችሉት በአገሪቱ የምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ ወይም አገር በቀል ከሆኑ ተቋማት ነው።
ሆኖም ግን የውጭ አገር ዜጎች ዩኬ በተመዘገቡ ተቋማት አማካኝነት ለምርጫ ገንዘብ ሊለግሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
በአዲሱ ረቂቅ መሠረት ለፖለቲከኞች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ግባቸው የአገሪቱን ፖለቲካ ማሻሻል እንደሆነ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የተቋማቱ ዋና መቀመጫ በዩኬ መሆኑን እንዲሁም አብዛኞቹ ባለድርሻዎች የአገሪቱ ዜጎች እንደሆኑ ማስረጃ ማቅረብም ይኖርባቸዋል።















