በእንግሊዝ ጎዳና የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእንግሊዝ ባለፉት አራት ዓመታት ጎዳና የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር አራት እጥፍ መጨመሩን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አሳየ።
የእንግሊዝ መንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓውያኑ 2021/22 የነበረው ቁጥር 3560 ሲሆን በ2024/25 ወደ 19310 አድጓል።
የእርዳታ ድርጅቶች መኖሪያ ቤት የሌላቸው ስደተኞች ቁጥር የጨመረው በመንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ነው ይላሉ።
የእንግሊዝ መንግሥት አዲሱ ፖሊሲ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ ያገኘ ስደተኞች ከተሰጣቸው ሆቴል በ28 ቀናት እንዲወጡ ያዛል።
መንግሥት "ጎዳና የሚኖሩ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ" ጥገንኝነት ሲጠይቁ ከሚቆዩበት ማረፊያ ወደ ራሳቸው ቤት የሚተላለፉበትን ሒደት ለማገዝ "ቁርጠኛ እንደሆነ" ይናገራል።
በተከታታይ ዩናይትድ ኪንግደምን ያስተዳደሩ መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ የሆነባቸው ሲሆን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው የሚጠባበቁ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
የጥገኝነት ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝበት ፍጥነት ቀርፋፋ እንደሆነ እና በአንድ ወቅት ቆሞ እንደነበር ይታወሳል።
ገዢው ሌበር ፓርቲ ጥያቄያቸው በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኝ ለማድረግ እና በቋሚነት የሚኖሩበትን ሥፍራ ለማመቻቸት ሐሳብ እንዳለው ገልጿል።
አንድ ጎዳና የሚኖሩ ስደተኞችን የሚደግፍ የእርዳታ ድርጅት በተለይ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ሴት ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን ይናገራል።
በሱዳን ያለውን ጦርነት በመሸሽ በጀልባ ተሳፍራ እንግሊዝ የገባችው ዩስራ አንዷ ናት። የ26 ዓመቷ ሱዳናዊት ወደ ዩኬ ከመምጣቷ በፊት መላ ቤተሰቧ በጦርነቱ እንደተገደለ ትናገራለች።
ወደ እንግሊዝ ከመጣች በኋላ ለአምስት ወራት ያክል መንግሥት ባቀረበላት ሆቴል ውስጥ ቆይታ ባለፈው ነሐሴ የጥገኝት ጥያቄዋ ምላሽ ቢያገኝም ግሬተር ማንቸስተር አካባቢ መንገድ ዳር የተከለችው ድንኳን ውስጥ እንደምትኖር ትገልጻለች።
"አንዳንድ ጊዜ ሰካራም ሰዎች መጥተው ድንኳኑን ለመክፈት ሲሞክሩ ጩኸቴን አሰማለሁ። አንዳንድ ጊዜ እስከ ጥዋት ድረስ አልተኛም" ትላለች።
መንግሥት ካቀረበላት መኖሪያ ቤት ከመውጣቷ በፊት የአካባቢውን ምክር ቤት ደውላ መኖሪያ እንደሌላት ብትናገርም ልጅ የሌላት አዋቂ በመሆኗ ቅድሚያ እንደማይሰጣት ተነግሯታል።
ዩስራ በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽታ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ወደ ዩኬ ብትመጣም አሁን ግን በውሳኔዋ እንደምትፀፀት ትናገራለች። ቤት አልባ ከሆነች በኋላ ሕይወት "በጣም ከባድ" መሆኑንም ታክላለች።
ስቶክፖርት ሬስ ኢኳሊቲ ፓርትነርሺፕ የተሰኘው ተቋም እርዳታ ከሚያደርግላቸው ስደተኞች መካከል አንዷ ናት።
በ28 ቀናት ጊዜ ውስጥ መንግሥት ካቀረበላቸው መኖሪያ ቤት እንዲወጡ የሚደረጉት ስደተኞች በዚህ ጊዜ ሥራ ማግኘት አሊያም አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ዩኒቨርሳል ክሬዲት የተባለ የክፍያ ሥርዓት ይዘጋጅላቸዋል።
ቤት አልባ መሆናቸውን ለአካባቢያቸው ምክር ቤት ያሳወቁ ብቻ በመመዝገባቸው አሁን ያለው ጎዳና የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይገመታል።
ዋና ከተማዋ ለንደን እና የሰሜን ምዕራቦቹ ማንቸስተር እና ሊቨርፑል በርካታ ቤት አልባ እና ጎዳና ለመውጣት ቋፍ ላይ ያሉ ስደተኞች ያሉባቸው ሥፍራዎች ናቸው።















