የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት 'በስደተኞች ጉዳይ' ላይ ያተኮረ መሆኑ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, PMO
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የኮመንዌልዝ፣ ልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር የኢትዮጵያ ጉብኝት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተዘገበ።
ሮይተር የዜና ወኪል እንደዘገበው ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ካደረጉት ጉብኝት አስቀድመው በሰጡት መግለጫ፣ ጉብኝታቸውን እየጨመረ የመጣውን የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች ቁጥር ለመግታት በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ለማተኮር እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
ወደ ዩኬ ለመግባት የሚፈልጉ ስደተኞችን ቁጥር ለመግታት የሥራ ፈጠራ እና የሕግ ማስፈፀም ትብብር ወሳኝ መሆናቸውን ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
"የሥራ ፈጠራ ትብብር ሰዎች ከአገራቸው እንዳይሰደዱ ያደርጋል፤ ጠንካራ የሕግ ማስፈፀም ትብብር ደግሞ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመከላከል እና በዩኬ መቆየት የሌለባቸውን ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ አገራቸው የመመለስ ሒደት ፈጣን እንዲሆን ያስችላል" ብለዋል ሚኒስትሯ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም እሁድ ጥር 24/2018 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ከሚኒስትር ይቬት ኩፐር ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ይቬት ኩፐር የስደተኞችን ጉዳይ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት አገራቸውን ዩናይትድ ኪንግደምን እና አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ሕገ ወጥ ስደትን ለማስቆም የሚወስዱትን የተለያዩ እርምጃዎች ባጠናከሩበት ወቅት ነው።
ዩኬ በሕገ ወጥ መንገድ የኢንግሊሽ ቻናልን በአነስተኛ ጀልባዎች አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም አሁንም የተለያዩ አማራጮችን እያማተረች ነው።
ቀደም ባለው የሪሺ ሱናክ አስተዳደር ወቅት ጥገኝነት ጠያቂዎች በሦስተኛ አገር ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል ስምምነት ከሩዋንዳ ጋር ተፈራርመው የነበረ ሲሆን፣ ብዙ ክርክሮችን ካስነሳ በኋላ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።
በቅርቡም ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈፀም የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ጉዳይ እንደ አዲስ የስደተኞች ጉዳይ በአገሪቷ ፖለቲከኞች መካከል መወዛገቢያ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ይህም በአንዳንድ ከተሞች ጎራ የለዩ ከባድ ተቃውሞዎችን አስነስቷል።
እንደ ዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ በአነስተኛ ጀልባ የኢንግሊሽ ቻነልን አቋርጠው ከገቡ ስደተኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን ስደተኞች ናቸው።
ይቬት በሮይተርስ የዜና ወኪል ላይ በተጠቀሰው መግለጫቸው "ሕገ ወጥ ስደትን የሚያስከትሉ ገፊ ምክንያቶችን እንዲሁም በሰዎች በመነገድ የሚያተርፉ በዓለም ላይ የተንሰራፉ ወንጀለኛ ቡድኖችን ለማስወገድ በጋራ እየሠራን ነው" ብለዋል።
ይህም ሰዎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ አደገኛ ጉዞዎችን ከማድረግ ይልቅ በአገራቸው የተሻለ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ የንግድ እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን በኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ ትብብርን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለመርዳትም ኢትዮጵያ ከዩኬው የኢንቨስትመንት ድርጅት ግሪድወርክስ የሚመራው የኢነርጂ ማስተላለፊያ ሁለት ፕሮጀክቶች ስምምነት እንደሚፈራረሙ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ይህንኑ ያረጋገጡ ሲሆን "በኢንቨስትመንት አማካሪዎች ማዕቀፍ ሥር የኢንቨስትመንት እና ሃብት አስተዳደር ቴክኒካዊ ትብብር የመግባቢያ ስምምነት እና የሁለት የጋራ ልማት ስምምነቶች ፊርማ ላይ መገኘታቸውን" ገልጸዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶችም የሁርሶ-አይሻ 400 ኪሎ ቮልት እና ደጋ ሃቡር - ቀብሪደሃር 132 ኪሎቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች ስምምነቶች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ስምምነቶቹ "ትብብረን በማጠናከር እና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ትልቅ እምርጃን የሚያሳዩ ናቸው" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሚኒስትሯ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም እንዲሁም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ያሉ 68 ሺህ ሕጻናትን ለመደገፍ እና ተፈናቃዮች ላይ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ 17 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።















