ታሊባን በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍት በአፍጋኒስታን ዩኒቨርስቲዎች ለማስተማሪያነት እንዳይውሉ አገደ

የታሊባን መንግሥት ከአፍጋኒስታን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍትን አስወገደ።

ይህ እገዳ በቅርቡ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችን እና የወሲባዊ ትንኮሳን ማስተማርን ሕገወጥ ያደረገው ውሳኔ አካል ነው ተብሏል።

140 በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍት "ሴፍቲ ኢን ዘ ኬሚካል ላቦራቶሪ" የሚለውን ጨምሮ "ፀረ ሸሪዓ እና የታሊባን ፖሊሲዎች" በሚል "ችግር አለባቸው" ከተባሉ 680 መጻሕፍት መካከል ናቸው።

ዩኒቨርስቲዎቹ በተጨማሪም 18 የትምህርት ዓይነቶችን ከዚህ በኋላ ማስተማር እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።

አንድ የታሊባን ባለሥልጣን የዚህን ምክንያት ሲያስረዱ "ከሸሪዓ መርሆዎች እና ከሥርዓቱ ፖሊሲ ጋር ይጋጫሉ" ብለዋል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ከጣላቸው የተለያዩ እገዳዎች እና ገደቦች መካከል ይህ የቅርብ ጊዜው ነው።

በዚህ ሳምንት ብቻ በአገሪቱ 10 አውራጃዎች የታሊባን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ኢሞራላዊነትን ለመከላከል በማለት ባስተላላፉት ውሳኔ መሠረት የፋይበር ኦፕቲክ ኢንተርኔት ታግዷል።

ታሊባን ያስተላለፋቸው እገዳዎች የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት በተለያየ መንገድ የሚጎዳ ቢሆንም ሴቶች እና ልጃገረዶች ግን የበለጠ ተጋላጭ ሆነዋል።

ታሊባን ሴቶች ከስድስተኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ እንዲሁም እአአ ከ2024 ጀምሮ መሳተፍ ይችሉባቸው የነበሩትን ስልጠናዎች በመዝጋት የአዋላጅ ነርስነት ትምህርት እንዳያገኙ ሆነዋል።

አሁን በዩኒቨርስቲዎች ይሰጡ የነበሩ እና ሴቶች በብዛት ይሳተፉባቸው ከነበሩ 18 የትምህርት ዓይነቶች መካከል ስድስቱ በተለይ ሴቶች ላይ የሚያተኩሩ የነበሩ መሆናቸውን ተገልጿል።

ጄንደር ኤንድ ዴቬሎፕመንት፣ ዘ ሮል ኦፍ ዉሜን ኢን ኮሙኑኬሽን እና ዉሜንስ ሶሲዮሎጂ በአፍጋን ዩኒቨርስቲዎች እንዳይሰጡ ከተዘጉ የትምህርት ዓይነቶች መካከል ይገኙበታል።

የታሊባን መንግሥት የሴቶችን መብት በአፍጋን ባሕል እና በእስላማዊ ሕግ መሠረት እንደሚያከብር ይናገራል።

በሴቶች የተጻፉ መጽሐፍትን ማገድ ላይ በኮሚቴነት የተሳተፉ ግለሰብ ለቢቢሲ አፍጋን "ሁሉም በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍት ለማስተማሪያነት እንዳያገለግሉ ተደርጓል" ሲሉ የውሳኔውን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት የፍትህ ምክትል ሚኒስትር የነበሩት እና በርካታ መጽሐፍትን የጻፉት ዛኪያ አዴሊ መጽሐፍቱን የማገድ ውሳኔ እንዳላስደነቃቸው ይናገራሉ።

"ባለፉት አራት ዓመታት ታሊባን ያደረጋቸውን በመመልከት በስርዓተ ትምህርቱ ላይ ለውጥ እንደሚያደርግ እጠብቅ ነበር" ብለዋል።

"ታሊባኖች ባላቸውን ሴት ጠል አስተሳሰብ እና ፖሊሲዎች የተነሳ ሴቶችን እንዳይማሩ መከልከል ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባቸው፣ ሃሳባቸው እና ጽሑፎቻቸው ራሱ ጭቆና ይደርስበታል።"

ይህ አዲሱ መመሪያ የተላለፈው ነሐሴ ውስጥ መሆኑን ቢቢሲ አፍጋን የተመለከተው ሰነድ ያስረዳል።

የታሊባን መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ምክትል አካዳሚክ ዳይሬክተር የሆኑት ዜኡር ራህማን አሪዩቢ ለዩኒቨርስቲዎች በጻፉት ደብዳቤ ውሳኔው የተላለፈው "በሃይማኖት ምሁራን እና ባለሙያዎች" መሆኑን ገልፀዋል።

እገዳው በሴቶች የተጻፉ መጽሐፍትን ብቻ ሳይሆን በኢራን ደራሲያን ወይንም አሳታሚዎች የታተሙትም እገዳ እንደተጣለባቸው ተገልጿል።

መጽሐፍቶችን በገመገመው ኮሚቴ ውስጥ የተሳተፉ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ "ወደ አፍጋን ስርዓተ ትምህርት ኢራናዊ ይዘት ያላቸው አስተምህሮዎች ሰርገው እዳይገቡ" ለመከላከል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍጋኒስታን ለሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሁሉ በተላከው 50 ገጽ ዝርዝር ውስጥ 679 የመጽሐፍ ርዕሶች የሰፈሩ ሲሆን 310 በኢራናውያን ደራሲዎች የተጻፉ ወይም ኢራን በሚገኙ አሳታሚዎች የታተሙ ናቸው።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በአንድ የትምህርት ተቋም የሚያስተምሩ ፕሮፌሰር በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት አዳጋች እንዳይሆን ፍርሃት እንዳላቸው ገልፀዋል።

"በኢራናውያን ደራሲያን እና ተርጓሚዎች የተጻፉ መጻሕፍት በአፍጋኒስታን ዩኒቨርስቲዎች እና በዓለም አቀፉ አካዳሚክ ማኅበረሰብ መካከል ቀዳሚ ድልድይ በመሆን እያገለገሉ ነበር። እነዚህን መጽሐፍት ማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል" ብለዋል።

በካቡል ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑ ሌላ ምሁር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ታሊባን ያስቀመጣቸውን ክልከላዎች ከግምት በማስገባት ራሳቸው የመማሪያ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት እንደሚገደዱ ገልጸዋል።

ነገር ግን ትልቁ ጥያቄ የሚዘጋጁት ማስተማሪያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው አይደሉም የሚለው ነው።

ቢቢሲ የታሊባን መንግሥት ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አላገኘም።