የቻይና ሠራተኞች በየሄዱበት አገር ጥቃት የሚደርስባቸው ለምንድነው?

ባለፈው ሳምንት ሁለት ቻይናውያን ፓኪስታን ውስጥ ተገደሉ። ሌሎች ብዙዎች ቆሰሉ። በካራቺ አየር ማረፊያ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ነው የሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳት የደረሰው።

ባሎቺስታን አማጺ ኃላፊነቱን ወሰደ። ይህ በፓኪስታን ቻይኖች ላይ ዒላማ ያደረገ ጥቃት የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ሆኗል።

በዓለም ዙሪያ ከግማሽ ሚሊዮን የሚልቁ ቻይናውያን ሠራተኞች ተሰማርተዋል። ብዙዎች የግድያ ጥቃት ወይም የመታገት ዕጣ ፈንታ ሲደርስባቸው ይሰማል።

ይህ ጥቃት ለምን በቻይና ሠራተኞች ላይ ይበረታል?

በፓኪስታን በቅርቡ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደው አማጺ “ዒላማ ያደረኩት ከፍተኛ የቻይና መሐንዲሶችን እና ባለሃብቶችን ነው” ብሏል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቃቱን “አስነዋሪ ተግባር’ ብለውታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ጥፋተኞቹ በዋዛ አይታለፉም ብሏል።

ይህ አማጺ የሚታገለው ባሎቺስታን ውስጥ ለሚገኙት “ባሎች” ለሚባሉት ሕዝቦች ነጻ አገርነት ለማቀዳጀት ነው።

ሁለቱ የተገደሉት ቻይናውያን በቃሲም ወደብ ካራቺ አጠገብ ሲንድ አውራጃ ውስጥ ሠራተኞች ነበሩ።

ይህ አማጺ ከዚህ ጥቃት ሌላ ግዋዳር ወደብ አጠገብ የነበረ የአየር ኃይል ቀጣና ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ይፋ አድርጓል። ይህ ቀጣና በቻይናዎች እየተገነባ የነበረ ነው።

በዚህ ብቻ አላበቃም። በካራቺ ዩኒቨርስቲ የኮንፊሽየስ ማዕከል የሚሠሩ ሦስት መምህራንን ገድሏል። በዚህ ጥቃት ፓኪስታናዊ ሾፌራቸውም ተገድሏል።

ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ 2022 ነበር።

ይህ ታጣቂ እንደሚለው የባሎች ሕዝቦች በዚህ የካራቺ ክፍል ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደለም። ነዳጅ እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ከክልሉ በውጭ ኩባንያዎች አማካይነት እየወጡ ቢሆንም ግን ሕዝቡ ተጠቃሚ አልሆነም።

ለዚህ ነው ጥቃት የሚሰነዝረው።

ምን ያህል የቻይና ሠራተኞች ከቻይና ውጭ ይሠራሉ?

የቻይና የንግድ ሚኒስቴር በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው አንድ ጥናት 568,000 ቻይናውያን በተለያዩ ፕሮጀክቶች በተለያዩ አገሮች ውስጥ ሠራተኛ ሆነው ያገለግላሉ።

ከእነዚህ የሚበዙት በቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት ላይ የተሰማሩ ናቸው።

በእዚህ ፕሮጀክት ቻይና ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ አውጥታለች። ይህ አውራ ጎዳናዎችን፣ ባቡሮችን ወደቦችን እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን የሚያገናኝ ነው።

ይህ ፕሮጀክት ቻይና ጥሬ እቃዎችን ከተለያዩ አገራት እንድታገኝ ምርቶቿን ደግሞ በወጪ ንግድ ለየአገራቱ እንድታደርስ ያግዛታል።

ፓኪስታን የዚህ ፕሮጀክት ተፈጻሚነት በጉልህ የሚታይባት አገር ናት። የቻይና -ፓኪስታን የኢኮኖሚ ኮሪደር ተብሎ ይጠራል።

ይህ ኮሪደር በምዕራብ ቻይና ድንበር በርካታ አውራ ጎዳናዎችን ከባቡር መስመሮች ጋር እያገናኘ በፓኪስታን አልፎ ወደ አረቢያን ባሕር የሚደርስ ነው።

ልክ እንደ ፓኪስታን ሁሉ በርካታ የአፍሪካ አገራት ላይም ይህ ፕሮጀክት ተፈጻሚ እንዲሆን ቻይና በቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ታደርጋለች። በዚህም ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ይጠቀሳሉ።

በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለቻይናውያን እንጂ ለእነርሱ ብዙም ሥራ አላመጣም እያሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።

በለንደን የቻይና ኢነስቲትዩት የሚሠሩት ፕሮፌሰር ስቲቭ ዛንግ “በአፍሪካ አገራት ያሉ ዜጎች ሥራቸው በቻይናዎች በመወሰዱ ይከፋቸዋል” ይላሉ።

“ፕሮጀክቱ በርካታ ቻይናውያን ሠራተኞችን ነው የሚያስመጣው። አፍሪካውያን የሚፈለጉት ከባድ የጉልበት ሥራዎችን እንዲሠሩ ብቻ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ ለቢቢሲ።

ዶክተር አሌክስ በዩናይትድ ኪንግደም አንድ የምሁራን ቡድን አባል ናቸው። “ቻይና ይሄ ፕሮጀክት ለሁለቱም አገራት ዜጎች በእኩል የሚጠቅም ነው” ብላ ታስባለች ሲሉ ያብራራሉ።

“እውነታው ግን በቻይና ያለውን ሥራ አጥነት ጫና ለመቅረፍ ነው ፕሮጀክቶቹን የምታውላቸው።”

በቻይናውያን ላይ የሚደርሰው አደጋ ምን ያህል የከፋ ነው?

ቻይና በውጭ ያላት ኢንቨስትመንቷ በበርካታ አገራት ሩቅ አካባቢዎች ጭምር ስለሚገኝ ዜጎቿ አደገኛ በሚባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተጉዞው ለመሥራት ይገደዳሉ።

ፓኪስታን ለምሳሌ የፖለቲካ አለመረጋጋት የማይርቃት አገር ናት።

በካራቺ የቢቢሲ ወኪል ሪያዝ ሶሃይል እንደሚለው በቅርብ ጊዜ ብቻ 16 ጥቃቶች ቻይናውያንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። 12 ቻይናውያን ተገድለዋል። ሌሎች 16 ቻይናውያን ቆስለዋል።

በ2018 ደግሞ አንድ ታጣቂ በፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ የቻይና ቆንስላ ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት በማድረስ አራት ሰዎችን ገድሏል።

ለዚህ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

በአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ ጥቃቶች ተስተውለዋል። በዲሞክራቲክ ኮንጎ የወርቅ ማውጫ ላይ ቻይናውያን ተገድለዋል። በናይጄሪያ ቻይናውያን በተደጋጋሚ ታግተዋል። በኒጀርም ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ፒተርሰን ኢንስትትዩት ባወጣው አንድ ጥናት እንዳስረዳው በብዙ የአፍሪካ እና የደቡብ ምሥራቅ እሲያ አገራት ቻይናውያንን ማገት አትራፊ እንደሆነ ይታሰባል። ይህም የሆነው የሚቀጥራቸው ድርጅት ከፍ ያለ የማስለቀቂያ ገንዘብ ሊከፍል ስለሚችል ነው።

ባለፉት ሁለት አሥርታት በአፍጋኒስታን ቻይናውያን በተደጋጋሚ ይታገቱ ነበር። ዋናው ቻይናውያንን የማገቱ ተግባር ለገንዘብ የሚፈጸም ነው።

ቻይና በውጭ ያሉ ዜጎቿን እንዴት ትጠብቃለች?

ይኸው ጥናት እንዳስታወቀው ቻይና አብዛኞቹን እገታዎች ክፍያ በመፈጸም ታስለቅቃቸዋለች። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቻይናውያን የሚሠሩባቸውን አገራት ለዜጎቿ የተሻለ ጥበቃ እንዲያደርጉ ትጠይቃለች። ይህን ለማጠናከር የሚረዱ የቅኝት ካሜራ መሣሪያዎችንም ታቀርባለች።

ቻይና ዜጎቿ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለፀጥታ ኃይሎች ሥልጠና እና ድጋፍ ታደርጋለች። በአንዳንድ አገራት ደግሞ የግል ጥበቃ ድርጅቶችን በመቅጠር ጭምር የዜጎቿን ደኅንነት ለመጠበቅ ጥረት ታደርጋለች።

ያም ሆኖ ቻይና የዜጎቿ ደኅንነትን በአስተማማኝ ለመጠበቅ አንዱ ፈተና ፕሮጀክቶቿ የሚገኙባቸው አገራት ደካማነት ነው። ብዙዎቹ የቻይና ፕሮጀክቶች የሚካሄዱባቸው አገራት የተረጋጉ አይደሉም።

በካራቺ ፓኪስታን የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የቻይና ኤምባሲ በዚያ የሚገኙ ዜጎቹ ጠንቃቃ እንዲሆኑ አሳስቧል።