ኢራን 1.5 ሚሊዮን አፍጋናውያንን አንዳንዶቹን የእስራኤል ሰላዮች ናቸው በሚል አባረረች

አሊ አህመድ በጀርባው ላይ ያለውን ብልዝ ለማሳየት ሸሚዙን ከፍ ሲያደርግ ዓይኖቹ በእንባ ተሞሉ።

እሱ በእስር ላይ እያለ የኢራን የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ ፈጽመውበት፣ በሰላይነት ከሰሱኝ ይላል።

"እኔን ለመደብደብ ቱቦዎች፣ የውሃ ጎማዎች እና የእንጨት ቁራጮች ተጠቅመዋል። እንደ እንስሳ ነው የቆጠሩን።"

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ አፍጋኒስታን ከመሻገሩ በፊት በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ በምትገኘው ኢስላም ቃላ ለቢቢሲ የደረሰበትን ተናግሯል።

*ማንነቱን ለመደበቅ በሚል ስሙ ተቀይሯል።

ኢራን ከአገራቸው ግጭትን ሸሽተው ወደ ግዛቷ የገቡ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰነድ የሌላቸውን አፍጋናዊያንን ታስተናግዳለች።

ለወራት ግን ወደ አገራቸው የመመለስ ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

በመጋቢት ወር ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው በፍቃደኝነት አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ እስከ ሐምሌ ድረስ የሚቆይ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር።

ነገር ግን በሰኔ ወር ከእስራኤል ጋር ባደረጉት የ12 ቀናት ጦርነት የተነሳ ባለስልጣናቱ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት መሆናቸውን በመግለጽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያንን በግዳጅ ወደ አገራቸው ልከዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በየቀኑ ወደ 50,000 የሚጠጉ አፍጋኒስታናውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ አስቸጋሪ ጉዞ አንደሚያደርጉ አስታውቋል።

አሊ አህመድ የኢራን ባለስልጣናት ገንዘቡን እና ስልኩን በመቀማት "ለመመለስ ቤሳ ቤስቲን አልነበረኝም" ሲል ተናግሯል።

አሊ በኢራን ውስጥ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ኖሯል።

"የጦስ ዶሮ"

የኢራን እርምጃ አፍጋኒስታናውያኑን ከእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ጋር ይሰራሉ ከሚል ሰፊ ውንጀላ በኋላ የመጣ ነው።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሰው አንዳንድ ግለሰቦች ሲሰልሉ ተይዘዋል ሲሉ ዘግበዋል።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ ለቢቢሲ ኒውስ አፍጋን "በተደጋጋሚ በሰላይነት እንወነጀላለን በሚል ወደ የትኛውም ቦታ ለመሄድ እንፈራለን" ብሏል።

ግለሰቡ እንደሚለው ከሆነ "እናንት አፍጋኒስታኖች ሰላዮች ናችሁ"፤ "ለእስራኤል ትሰራላችሁ" ወይም "በቤታችሁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ትሰራላችሁ" የሚሉ ውንጀላዎች ሁሌም ይቀርብባቸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ያገለገሉት ባርኔት ሩቢን ቴህራን ከእስራኤል ጋር ባደረገችው ጦርነት ለታየባት ድክመት "የጦስ ዶሮ ትፈልጋለች" ብለዋል።

"የኢራን መንግሥት በደህንነት ተቋሙ ውድቀት በጣም አፍሯል" ይህም የሚያሳየው በኢራን "የእስራኤል የስለላ ቡድን በጣም ዘልቆ መግባቱን ነው" ብለዋል።

"ስለዚህ የሚወነጅሉት ሰው መፈለግ ነበረባቸው።"

ተቺዎችም የስለላ ውንጀላው መንግሥት ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን አፍጋኒስታናውያንን ለማስወጣት ላለው እቅድ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነው ይላሉ።

ቢቢሲ የኢራንን መንግሥት ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

ሐምሌ 18 የእስላማዊ ሪፐብሊክ የዜና አገልግሎት የአፍጋኒስታን ስደተኞች መመለስ "በሰላም፣ ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር… ይህም ግብ በየትኛውም ደረጃ ባሉ ተፈፃሚ ነው" ሲል ዘግቧል።

"አራት ቀን እንደ አራት ዓመት"

አብደላህ ረዛኢ (ስሙ ተቀይሯል) ከአሊ አህመድ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ አለው።

እሱ በታሰረበት እስር ቤት 15 የሚጠጉ የኢራን የፀጥታ ኃይሎች በእሱ እና በሌሎች አፍጋኒስታናውያን ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሰዋል ሲል አብደላህ በኢስላም ቃላ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አብደላህ ከመያዙ በፊት በኢራን ውስጥ የቆየው ለሁለት ወራት ብቻ መሆኑን እና ቪዛ እንደነበረውም ገልጿል።

"የኢራን ፖሊሶች ቪዛዬንና ፓስፖርቴን ቀድደው ክፉኛ ደበደቡኝ፣ ሰላይ ነህ፤ አገራችንን ልታበላሽ ነው" ብለው ከሰሱኝ።

የታሰረው ለአራት ቀናት ቢሆንም "አራት ዓመት ያህል እንደሆነኝ ነው የተሰማኝ" ይላል።

በእስር ቤቱ ውስጥ የማያቋርጥ እንግልት፣ አካላዊ ጥቃት እንደደረሰበት እንዲሁም የምግብ እጥረት መኖሩንም ገልጿል።

በአፍጋኒስታናውያን እና በእስራኤል የደህንነት ተቋም መካከል ትብብር አለ የሚለው ክስ መሰማት የጀመረው የ12 ቀናቱ ጦርነት እንደጀመረ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 13 እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ተቋማትን ባጠቃችበት ቀን፣ መንግሥት ዜጎች ያልተለመዱ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ካዩ፣ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ከተመለከቱ የእስራኤል ወኪሎች መሳሪያ እያጓጉዙ ሊሆን ስለሚችል እንዲጠቁሙ ለሕዝቡ አስታውቋል።

ብዙ ተከታዮች ያሏቸው የቴሌግራም ገፆች ከመንግሥት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ቃላትን በመጠቀም የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በትልልቅ ከተሞች ውስጥ መኪና እያሽከረከሩ ብዙ ጊዜ አፍጋኒስታናውያንን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውለው አገላለጽ በመጠቀም ሕዝቡ ከ"ባዕድ ዜጎች" እንዲጠነቀቅ ሲቀሰቅሱ ነበር።

በማግስቱ፣ ከእስራኤል ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎች፣ አንዳንድ አፍጋናውያንን ጨምሮ መታሰራቸው ተዘገበ።

ሰኔ 16፣ በዜና ማሰራጫዎች አፍጋኒስታናውያን ድሮኖችን ይዘው በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚሉ ቪዲዮዎች ተሰራጭተዋል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል በሰፊው የተጋራ ቢሆንም ከተቀረፀ የቆየ መሆኑ ታውቋል።

ሰነድ አልባ አፍጋኒስታናውያኑ የታሰሩት ሕጋዊ የሆነ ወረቀት ስለሌላቸው መሆኑንም አሳይቷል።

እአአ ሰኔ 18፣ አፍጋን ዊትነስ የተባለው ቡድን ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓዶች ጋር ግንኙነት ባለው የቴሌግራም ገጽ ላይ በማሽሃድ ከተማ 18 አፍጋኒስታናውያን ለእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ሲሰሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሚገልጽ መረጃ መጋራቱን ሪፖርት አድርጓል።

በማግስቱ የግዛቲቱ የጸጥታ ምክትል ኃላፊ እስሩ "ሰው አልባ አውሮፕላን ከመስራት ጋር" ወይም ከእስራኤል ጋር ትብብር ከማድረግ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ሲሉ መናገራቸው ተጠቅሷል።

"በሕገወጥ መንገድ ኢራን ውስጥ በመገኘታቸው ብቻ ነው የተያዙት።"

ነገር ግን ሲሰልሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚሉ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርቷል።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በኤክስ ገጽ ላይ "የአፍጋኒስታናውያን መባረር ብሔራዊ ፍላጎት ነው" የሚል ሃሽታግ ከ200,000 ጊዜ በላይ ተጋርቷል፤ ይህም በሐምሌ 2 ላይ ከ20,000 በላይ ጊዜ ተጠቅሶ ተገኝቷል።

በኢራን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያለው ፀረ አፍጋኒስታን ስሜት አዲስ አይደለም።

አሁን የታየው ልዩነት ግን "ሐሰተኛ መረጃው የመጣው ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆን ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ካላቸው ሚዲያዎች ጭምር ነው" ሲል አፍጋን ዊትነስ የተባለው ገለልተኛ ቡድን አስታውቋል።

ከ'ነፍሰ ገዳይነት' ወደ 'ሰላይነት'

ከጥር ወር ጀምሮ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ኢራንን ለቀው መውጣታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።

የታሊባን የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከ918,000 በላይ አፍጋኒስታናውያን ከኢራን ከሰኔ 22 እስከ ሐምሌ 22/2025 ባለው ጊዜ ውስጥ አፍጋኒስታን ገብተዋል።

አንዳንዶቹ ኢራን ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ናቸው።

ከ1970ዎቹ ሶቪየት ኅበረት አፍጋኒስታንን መውረሯን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ወደ ኢራን እና ፓኪስታን ተሰደዋል።

በቅርቡ ደግሞ በ2021 ታሊባን ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ የስደተኞች ቁጥር ጨምሯል።

ባለሙያዎች አፍጋኒስታን በታሊባን አገዛዝ ስር ወደምትገኝ አገራቸው በግዳጅ የሚመለሱትን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ለመቀበል የሚያስችል አቅም እንደሌላት አስጠንቅቀዋል።

አገሪቱ ከፓኪስታን በብዛት በጎርፉ ስደተኞች ተጥለቅልቃለች፤ ይህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ለቀው እንዲወጡ እያስገደደ ነው።

በለንደን ስኩል ኦፍ ኦሬንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ተመራመራዊ የሆኑት ዶክተር ኸዲጃ አባሲ መጀመሪያ ላይ አፍጋኒስታናውያን በኢራን አቀባበል ተደርጎላቸዋል ይላሉ ።

ነገር ግን ፀረ አፍጋኒስታን ስሜት ቀስ በቀስ እየጨመረ በመምጣቱ የመንግሥት ሚዲያዎች አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ለኅብረተሰቡ "የኢኮኖሚ ሸክም" አድርገው ይቀርባሉ ብለዋል።

በኢራን ውስጥ ስለ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ሐሰተኛ ትርክቶችን መሰራጨት ጀምረዋል።

እአአ በ 1990 ዎቹ ውስጥ ፣ በቴህራን ውስጥ ተከታታይ አስገድዶ መድፈር እና ግድያዎች ሲፈጸሙ ያለምንም ማስረጃ የአፍጋኒስታናውያን ስራ ነው በሚል ይወነጀሉ ነበር።

ይህም የጥላቻ ወንጀሎች እንዲጨምር አድርጓል። በኋላ ላይ ወንጀሉን የፈጸሙት ኢራናውያን መሆናቸው ታውቋል።

በድህረ 2021 ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚገመቱ አፍጋኒስታኖች ወደ ኢራን ሲሰደዱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ አፍጋናውያን በአገሪቱ እንደሚኖሩ ተነግሯል።

በወቅቱ ኢራን ስደተኞችን በከፍተኛ መጠን እንዲገቡ የፈቀደች ብቸኛዋ ጎረቤት አገር ነበረች።

"አፍጋኒስታንን ከኢራን ማባረር ፣ አብዛኞቹ ኢራናውያን ከመንግሥት ጋር የሚያስማማው ብቸኛ ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም" ይላሉ ብለዋል ዶ/ር አባሲ።

በሐምሌ ወር ከ1,300 በላይ የኢራን እና የአፍጋኒስታን አክቲቪስቶች በኢራን ውስጥ በአፍጋኒስታን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዲቆም የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ተፈራርመዋል።

ዛሬ በኢራን የፀረ አፍጋኒስታናውያን አመለካከት በሰፊው ተስፋፍቷል።

የዚህንም አስከፊነት ሲያስረዱ "በጣም አደገኛ ሆኗል፤ ስለዚህ ሰዎች ቤታቸው ለመቆየት ይሞክራሉ" ብለዋል።

ከአሁን በኋላ ለግዙፍ ቁጥሮች አማራጭ የለም። ድንበሩ በሰዎች መጨናነቁ ቀጥሏል።

አብደላህ ወደ አገሩ መባረሩ እቅዱን አበላሽቶበታል።

"ሁሉንም ነገር አጣሁ" ሲል በቁጭት ይናገራል።