ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ጣልቃ ብትገባ የሚፈጠረውን አደጋ የሚያሳዩ 4 ታሪካዊ ምሳሌዎች
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ግንቦት ወር ከእሳቸው በፊት የነበሩትን የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚዳንቶችን በጣልቃ ገብ ፖሊሲዎቻቸው ክፉኛ ሲተቿቸው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2003 የኢራቅን አወዛጋቢ ወረራ በግልፅ በማጣቀስ "አገር ገንቢ ተብዬዎች ከገነቡት በላይ ብዙ አገራትን አወድመዋል" ብለዋል።
"ጣልቃ ገቢዎቹ የማይረዱት ውስብስብ ሕብተረሰብ ውስጥም ጣልቃ ገቡ" ሲሉም አክለዋል።
ትራምፕ የሳዑዲ አረቢያ መዲና የሆነችውን ሪያድ በጎበኙበት ወቅት ነበር ይህንን ተናገሩት። ቢያንስ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ጣል ቃገብነት አይኖርም የሚል አስተያየት በአንዳንድ ተንታኞች እንዲሰጥም ምክንያት ሆኗል።
ነገር ግን እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ከእስራኤል ጎን በመሆን ጥቃት መፈጸሟ በዚህ አቋማቸው ላይ ጥያቄ ፈጥሯል።
ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን በሚገኙ በሦስት የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ፈጸመች። ይህም ኢራን እና እስራኤልን ለሁለት ሳምንታት ያህል ወደቆዩበት ግጭት ዋሽንግተንን አስገብቷታል።
ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል ዓላማቸው የኢራንን የኒውክሌር ህልም ማጨናገፍ ነው።
"ዓላማችን የኢራንን የኒውክሌር የማበልፀግ አቅም ማውደም እና በዓለም ደረጃ አሸባሪነትን የምትደግፈውን አገር የኒውክሌር ባለቤትነት መግታት ነበር" ሲሉ ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ ተናግረዋል።
ታሪክ እንደሚያሳየው ግን ምዕራባውያን አንዳንድ ነገሮችን "ለመፍታት" በቀጠናው ጣልቃ ሲገቡ ሁሉም ነገር ሰምሮ በዕቅዱ መሠረት አልተሳካላቸውም።
ከ1940ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ቀጥሏል ሲሉ በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ሊባኖሳዊ አሜሪካዊው ፋዋዝ ጌርጌስ ተናግረዋል።
"የሰሞኑ የኢራን ጥቃትም አንድ ማሳያ ነው" ሲሉ ምዕራባውያን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያላቸው ሚና እና የገጠማቸውን ፈተና በሚመለከት "ዋት ሪሊ ዌንት ሮንግ፡ ዘ ዌስት ኤንድ ዘ ፌይለር ኦፍ ዲሞክራሲ ኢን ዘ ሚድል ኢስት" የሚል መጽሐፍ ደራሲው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ጽሑፍ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረገቻቸውን አራት ጣልቃ ገብነቶችን በመውሰድ ግምገማ እናደርጋለን።
1 - የኢራን መፈንቅለ መንግሥት (1953)
በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሞሳዴቅ እአአ በ1953 በኢራን ጦር መሪነት እና በዩናይትድ ስቴትስ እና በዩናይትድ ኪንግደም ድጋፍ በተፈጸመባቸው መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተነስተዋል።
ሞሳዴቅ ወደ ሥልጣን የመጡት ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን፣ የኢራንን ነዳጅ ከባለሃብቶች በመንጠቅ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ለማስገባት ቃል ገብተው ነበር።
ኢኮኖሚያቸው በኢራን ነዳጅ ላይ የተንጠለጠለው ለንደን እና ዋሽንግተን ከውሳኔው በተጨማሪ ኢራን ወደ ኮሚኒስታዊ ሥርዓት እያደላች መሆኑ ስጋት አሳድሮባቸዋል።
መጀመሪያ ላይ ሻህ መሐመድ ሬዛ ፓህላቪን የሚደገፍ ሕዝባዊ አመጽ ሆኖ ቢቀርብም ከአመጹ ጀርባ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ነበሩ።
በአውሮፓውያኑ 2000 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ማድሊን ኦልብራይት ዩናይትድ ስቴትስ በመፈንቅለ መንግሥቱ ውስጥ ስለነበራት ሚና በግልጽ ተናግረዋል።
እአአ በ2009 በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማም በካይሮ ንግግራቸው የዋሽንግተንን ሚና አምነዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱ ከ60 ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2013 ደግሞ ሲአይኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በመፈንቅለ መንግሥቱ ውስጥ የነበረውን ሚና የሚያመለክቱ ሰነዶች አሳትሟል።
"ወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥት. . . በሲአይኤ መሪነት የተፈጸመው በዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ፖሊሲ ምክንያት ነው" በማለት በብሔራዊ ደኅንነት መዝገብ ቤት በታተሙት ሰነዶች ላይ ሰፍሯል።
የአሁኑ የአሜሪካ እና የኢራን እሰጣ አገባ አንድም ካለፈው ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ፋዋዝ ጌርግስ ተናግረዋል።
"ኢራናውያን በሕጋዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ጠቅላይ ሚኒስትርን ከሥልጣን በማውረድ ጨካኝ እና አምባገነኑን ሻህ የአገሪቱ ገዥ አድርገው በመሾማቸው ዩናይትድ ስቴትስን ይቅር ብለው አያውቁም" ሲሉ አብራርተዋል።
"በኢራን እስካሁን ለዘለቀው የፀረ አሜሪካ ስሜት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዩናይትድ ስቴትስ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞን እስከወዲያኛው በመቀየሯ መሆኑን ይናገራሉ።"
ገርጌስ አክለውም በግብፅ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በጋማል አብደል ናስር ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና የብሔራዊ ፕሮጄክቱን አቅጣጫ ለመቀየር አሜሪካ ሞክራለች። ነገር ግን ብዙም አልተሳካላትም።
2 - አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኘውን ታሊባንን መደገፏ
እአአ በ1979 በአፍጋኒስታን መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ የሶቪየት ኅብረት ጦር የኮሚኒስቱን መንግሥት በመደገፍ ከሙጃሂዲን ጋር ለመዋጋት አገሪቱን ወረረ።
የአፍጋኒስታንን ኮሚኒስት መንግስት በሚቃወሙ አክራሪ እስላማዊ ጂሃዲስኖች የተቋቋመው ይህ ቡድን የአሜሪካ፣ የፓኪስታን፣ የቻይና እና የሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የሌሎች አገራት ድጋፍ ነበረው።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካ የሶቪየትን ዓላማዎች ለማደናቀፍ በማለም መሳሪያ እና ገንዘብ ከሚሰጡ አገራት ግንባር ቀደሟ ነበረች።
ከዓመታት በኋላ የወጡ ሰነዶች፣ የጋዜጠኞች የምርመራ ዘገባ ውጤቶች እና ምስክርነቶች እንደሚያሳዩት አሜሪካ በአፍጋኒስታን ውስጥ ሶቪየት ኅብረትን ለማጥመድ ፈልጋ ነበር።
ይህም የአሜሪካ ወታደሮች በቬትናም ጦርነት ውስጥ ከቆዩበት ሁኔታ እና ከደረሰባቸው የሕይወት እና የሀብት ውድመት ጋር የሚስተካከል እንዲሆን ነበር ፍላጎቷ።
ተልዕኮው "ዘመቻ ሳይክሎን" ተብሎ የሚጠራ የነበረ ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃን "በሲአይኤ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ድብቅ ተልዕኮ" በማለት ገልጸውታል።
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን የጂሃዲስት መሪዎችን ልዑካንን በጽህፈት ቤታቸው (ኦቫል ኦፊስ) እስከመቀበል ደርሰዋል።
ከዘጠኝ ዓመታት ጣልቃ ገብነት በኋላ እአአ መስከረም 1988 የሶቪየት ኅብረት መሪው ሚኻይል ጎርባቾቭ የሶቪየት ኃይሎች ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ አዘዙ።
አገሪቱ በተለያዩ አንጃዎች ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስትገባ የሶቪየት ኅበረት ድጋፍ የተቋረጠበት መንግሥትም ወደቀ።
ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት በአውሮፓውያኑ 1994 ታሊባን በደቡባዊ ካንዳሃር ከተማ ብቅ አለ። ቡድኑ በወጣቶች የተሞላ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ከፓሽቱን ጎሳ ተገኙ ናቸው። ተቀባይነቱም ከፍ አለ።
ብዙዎቹ መሪዎች በሶቪየት ወረራ ወቅት የሙጃሂዲን እንቅስቃሴን ወግነው የተዋጉ ሲሆን፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አገራት የጦር መሳሪያ ድጋፍ አግኝተዋል።
እአአ በ1996 ታሊባን ካቡልን ተቆጣጠረ። ጥብቅ እስላማዊ አገዛዝን በመተግበር በሰብዓዊ መብት ረገጣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተችበትን አገዛዝ ተግባራዊ አደረገ።
የሸሪዓ ሕግን በጥብቅ በማስተግበርም ቅጣቶችን ይፋ አደረጉ።
ነፍሰ ገዳዮች እና አመንዛሪዎች በአደባባይ እንዲገደሉ፣ ሌቦች እጃቸው እንዲቆረጥ፣ ወንዶች ፂም እንዲያሳድጉ እና ሴቶችም ከራስ እስከ እግር ድረስ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ቡርቃ ለብሰው ዓይናቸውን እንዲሸፍኑ ተወሰነ።
ቴሌቪዥን፣ ሙዚቃ እና ፊልም ታገዱ። ከ10 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ትምህርት አንዳይማሩም ወሰኑ።
ልክ ከሶቪየት-አፍጋኒስታን ጦርነት በኋላ እንደተደረገው ሁሉ ከአፍጋኒስታን አልፎ እስላማዊ ትግልን የሚያስፋፋው አልቃይዳ ተፈጠረ።
ታሊባን ይህንን ድርጅት እና መሪው ኦሳማ ቢን ላደንን መጠጊያ ሰጠው። በዚህምም በአውሮፓውያኑ መስከረም 1 ቀን 2001 የተፈጸሙ ዓይነት ጥቃቶችን የሚያቅዱበት መሸሸጊያ ሆናቸው።
በአላባማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዋሌድ ሀዝቡን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አብዛኛው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በቀጣናው "ሚዛናዊ" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ጥረት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
"የአሜሪካንን እና አጋሮቿን ጥቅም የሚቃወም ማንኛውንም ፖለቲካዊ ኃይል ለመቋቋም ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሊባኖሱ የፖለቲካ ሳይነቲስት አክለውም በባሕረ ሰላጤው ጦርነት (1990-1991 እአአ) በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጣልቃ ገብነት ምሳሌ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
"ኢራቅ ኩዌትን ለመውረር ያደረገችውን ዕቅድ ለመመከት ሙከራ አደርጓል። የኩዌትን ሉዓላዊነት ለማስመለስ ተችሏል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በፖለቲካ መሪዎች እና በአካባቢው ያሉ መሪዎች በአካባቢው ያለውን የጋራ የደኅንነት ስጋቶች ለመፍታት ውይይቶች ነበሩ።"
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን አስተዳደር ወቅት ደግሞ ሌላ አካሄድ እንደተጀመረ ሀዝቡን አስገንዝበዋል።
"ዓላማው የአሜሪካን ጥቅምና ህልም የሚያስጠብቁ የደኅንነት ቡድን ማቋቋም ነው" ብለዋል።
"ይህም በአንድ በኩል በሰላሙ ሂደት እና በአረብ እና በእስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ እንዲሆን በማድረግ ሁሉም የአረብ አገራት ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር እንዲሠሩ ማድረግን ያካትታል። ኢራን እና ኢራቅን ደግሞ በወታደራዊ እና በዕቀባ ዘዴዎች መያዝን ያካትታል።"
አንዳንድ ጊዜ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ከእስራኤል ድጋፍ ጋር አብሮ ይሄዳል። የሁለቱ አገራት ግንኙነት በአሜሪካ መሪዎች "ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው እና የማይናወጥ" ተብሎ ይገለጻል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እስራኤል በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን በወታደራዊ ዕርዳታ ታገኛለች። ይህም ቀዳሚዋ የአሜሪካ ዕርዳታ ተቀባይ ያደርጋታል።
ከ1951 እስከ 2022 ባለው ጊዜ እስራኤል ከአሜሪካ ያገኘችው ወታደራዊ ዕርዳታ ወደ 225.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ከመከላከያ እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የተገኘው መረጃ ያሳያል።
3 - የአፍጋኒስታን ወረራ (2001)
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2001 ዩናይትድ ስቴትስ ታሊባኖችን ከሥልጣን ለማስወገድ አዲስ ወረራ በአፍጋኒስታን ፈጸመች።
አሜሪካ የመስከረም 11 ጥቃትን ተከትሎ ዲሞክራሲን ለመደገፍ እና የአል ቃኢዳ የሽብር ስጋትን ለማስወገድ ቃል ገባች።
ዋሽንግተን የአገሪቱን ዋና ከተማ ካቡልን በፍጥነት በመቆጣጠር ታሊባን ሥልጣኑን እንዲያስረክብ አስገደደች።
ይህንንም ተከትሎ በምዕራባውያን ድጋፍ ከሦስት ዓመታት በኋላ አዲስ የአፍጋኒስታን መንግሥት ሥራ ጀመረ።
የታሊባን ደም አፋሳሽ ጥቃት ግን ቀጠለ።
እአአ በ2009 የወቅቱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ታሊባንን ለማዳከም የሚረዳ የወታደር ቁጥር እንደሚጨምሩ ቢያሳውቁም ነገር ግን ብዙም የቆየ አልነበረም።
ከእአአ 2001 ጀምሮ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ እጅግ ደም አፋሳሽ ዓመት ሆኖ በተጠናቀቀው በ2014 የኔቶ ኃይሎች ተልዕኳቸውን አቋርጠው የፀጥታ ኃላፊነታቸውን ለአፍጋኒስታን ጦር አስረከቡ።
ይህ እርምጃ ታሊባን ብዙ ግዛቶችን እንዲቆጣጠር በር ከፈተለት።
በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ቡድኑ ጥንካሬን ማግኘቱን ቀጥሎ ተከታታይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶችን ፈጸመ። በካቡል በሚገኘው የፓርላማ ሕንጻ እና በዋና ከተማዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ለተፈጸሙ ጥቃቶችም ሃላፊነቱን ወስዷል።
አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን ሠራዊቷን ካሰማራች ከ20 ዓመታት በኋላ የጆ ባይደን አስተዳደር ወታደሮቹን ከአገሪቱ ለማስውጣት እአአ ሚያዝያ 2021 ውሳኔ አሳለፈ።
ይህ በጥድፊያ ተከናወነው ለቆ የመውጣት እርምጃ የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በፍጥነት በታሊባን እጅ እንድትወድቅ ያደረገ አወዛጋቢ ውሳኔ ነበር።
የካቡል ውድቀት ከደቡብ ቬትናም ክስተቶች ጋር ተነጻጽሯል።
በአሜሪካ ምክር ቤት የሪፐብሊካን ተወካይ የሆኑት ኤሊሴ ስቴፋኒክ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ይህ የጆ ባይደን ሳይጎን (ሳይጎን የቬይትናም ከተማ ናት) ነው" ብለዋል።
"በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ፈጽሞ የማይረሳ አስከፊ ውድቀት ነው" ሲሉም አክለዋል።
ታሊባን እአአ በ2021 አፍጋኒስታንን እንደገና ሲቆጣጠር ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የጦር መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን አግኝቷል።
አብዛኞቹ በዩናይትድ ስቴትስ የተገዙ መሆናቸውን አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የቀድሞ የአፍጋኒስታን ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እአአ በ2023 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳመለከተው ታሊባን የየአካባቢው አዛዦች ከተቆጣጠሩት የአሜሪካ ጦር መሳሪያዎች 20 በመቶውን እንዲወስዱ በመፍቀዱ ምክንያት ጥቁር ገበያው ተስፋፍቷል።
በታሊባን ከተወሰዱት የቅርብ ጊዜ እርምጃዎች መካከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመከታተል የሚያገለግሉ 90 ሺህ ካሜራዎች መተከላቸው ይገኝበታል።
የታሊባን ባለሥልጣናት ካሜራዎቹ ወንጀልን ለመዋጋት ክትትል አስፈላጊ ናቸው ቢሉም፤ ተቺዎች ግን ተቃውሞን ለማፈን እና በታሊባን የተጫነውን ጥብቅ የሥነ ምግባር ደንብ ለማስከበር ጥቅም ላይ ይውላል ሲሉ ገልጸዋል።
4 - የኢራቅ ወረራ (2003)
የኢራቅን ወረራ ታሪክ እአአ ከ1990 ይጀምራል። በወቅቱ በፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴን የሚመራው የኢራቅ ጦር ድንበር ጥሶ ወደ ኩዌት በመግባት ወረራውን የተቃወሙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድል፤ የኩዌትን መንግሥት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲሰደድ ያደረገበት ወቅት ነው።
ይህ "ከሳዳም ሁሴን ትልቅ ስህተቶች አንዱ ነው" ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለብዙዎችም ይህ ቀን በመካከለኛው ምሥራቅ ታሪክ ውስጥ ረዥም እና የሁከት ጊዜ የተፈጠረበት ነበር።
ከበርካታ ማስጠንቀቂያዎች እና ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በኋላ፣ በአሜሪካ የሚመራ እና በዋናነት በሳዑዲ አረቢያ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚደገፍ ጥምረት የኢራቅ ጦርን ከኩዌት የማባረር ተልዕኮ ጥር 17/1991 ጀመረ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔ 687 አጸደቀ። ውሳኔው ኢራቅ ሁሉንም ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች እንድታወድም የሚጠይቅ ሲሆን፣ በዚህም የኒውክሌር፣ የባዮሎጂካል እና የኬሚካላዊ መሳሪያዎችን እንዲሁም የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎችን የሚገልጽ ነው።
እአአ በ1998 ኢራቅ ከተባበሩት መንግሥታት የጦር መሳሪያ ተቆጣጣሪዎች ጋር ትብብሯን አቋረጠች። በኒው ዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል እና በፔንታጎን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ኢራቅን ለመውረር ማቀድ ጀመሩ።
ሳዳም የጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎችን ማከማቸት እና ማምረት ቀጥለዋል ሲሉ ቡሽ ከሰሱ። ኢራቅ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር የዓለም አቀፍ "የክፋት መረብ" አካል ነች ሲሉም ተናገሩ።
የወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓውል እአአ በ2003 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተናገሩት ከሆነ ኢራቅ ባዮሎጂካል የጦር መሳሪያዎችን ለማምረት "ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪዎችን" አዘጋጅታለች።
ነገር ግን በ2004 ማስረጃው "ያን ያህል ጠንካራ አይመስልም" ሲሉ ገልጸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ እና ፖላንድ በወረራው ተሳትፈዋል። ጀርመን፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ እና ሜክሲኮን ጨምሮ በርካታ አገራት ደግሞ ወረራውን ተቃውመዋል።
የወቅቱ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ዴ ቪሌፒን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት "ከሁሉ የከፋው መፍትሄ ይሆናል" ብለው ነበር። የኢራቅ ጎረቤት እና የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ በበኩሏ አሜሪካ እና አጋሮቿ የአየር ሰፈሮቿን እንዲጠቀሙ አልፈቀደችም።
በአላባማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የመካከለኛው ምሥራቅ አጥኚው ፕሮፌሰር ዋሌድ ሀዝቡን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በወረራው አሜሪካ በኢራቅ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት እና በአካባቢው የራሷን የፀጥታ ፍላጎት ለመጫን ፍላጎት ነበራት።
የቢቢሲ ኢንተርናሽናል ኤዲተር እና የመካከለኛው ምሥራቅ ዘጋቢ ጄሬሚ ቦዌን በበኩሉ ወረራው በኢራቅ እና በሕዝቧ ላይ ትልቅ ጥፋት ሲሆን፣ አገሪቱንም ለአስርት ዓመታት ወደዘለቀ ትርምስ ውስጥ ከቷታል።
ሌላው የወረራው መዘዝ በአሜሪካውያን እና በሱኒ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ጥምረት ለጊዜው የተከፋፈለው አል ቃኢዳ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ለሚጠራው ቡድን እንዲፈጠር ዕድል ማመቻቸቱ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2003ቱ ወረራ ምክንያት ምን ያህል ኢራቃውያን እንደሞቱ በትክክል አይታወቅም።
ከኢራቅ የቆጠራ ፕሮጀክት (አይቢሲ) የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ወረራውን ተከትሎ የዜጎችን ሞት ለመመዝገብ በተደረገው ሙከራ፣ 209 ሺህ 982 የኢራቅ ሲቪሎች ከ2003 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ተገድለዋል።
ዋልድ ሀዝቡን እንደሚሉት የቀጣናውን የጉዞ አቅጣጫ ለመቀየር እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ደኅንነት ለማስፈን አሜሪካ ክልላዊ ጥረቶችን እንድትደግፍ ማድረግ ነው ሲሉ ይመክራሉ።
"ክልሉ የራሱን ግጭቶች ለመፍታት እንዲሞክር ድጋፍ ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።
"የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ ጥቅሞች ሊከበሩ የሚችሉት በእራሷ እና በአጋሮቿ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል ጫና ሳይሆን የአካባቢው አገራት ስለ ቀጣናዊው ደኅንነት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ሲሠራ የተሻለ ሊሆን ይችላል።"