ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ራፐር ዲዲ የ50 ወራት እስራት ተፈረደበት
አሜሪካዊው ራፐር ሻን "ዲዲ" ኮምብስ አራት ዓመት ከሁለት ወር እንዲታሰር ፍርድ ቤት ወሰነ።
ዲዲ በሁለት የቀድሞ ፍቅረኞቹ በቀረበቡት ከወሲብ ንግድ ጋር የተያያዙ ክሶች ለ50 ወራት እንዲታሰር ብይን ተሰጥቷል።
የዲዲ ጠበቃ የ14 ወራት እስራት ብቻ እንዲፈረድበት ጠይቀዋል። ደንበኛቸው በኒው ዮርክ ለ13 ወራት ታስሮ በቆየበት ጊዜ "መለወጡን" በመግለጽ ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ዲዲ የቤት ውስጥ ጥቃት የማድረስ ታሪኩ ከግምት ውስጥ ገብቶ 11 ዓመታት እንዲታሰር ጠይቋል።
የዲዲ ልጆች በፍርድ ቤት እያለቀሱ አባታቸውን ደግፈው ቃል ቢሰጡም ዳኛ አሩን ሰብራማኒያን ጠንካራ ፍርድ መሰጠት አለበት ብለዋል።
ትናንት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ዲዲ "ይቅርታ" ቢጠይቅም ዳኛ አሩን ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጠንካራ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆን አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።
ዲዲ የቀድሞ ፍቅረኞቹን "ድርጊቴ አስጸያሪም አሳፋሪም ነበር። በአደንዛዥ ዕፅ እና ለራሴ ባለኝ የተጋነነ ምልከታ መንገዴን ስቼ ነበር" ሲል ይቅርታ ጠይቋል።
የዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛ ካሳንድራ ቬንቱራ አንደኛዋ ተጎጂ ስትሆን፣ 'ጄን' በሚል ምሥጢራዊ ስም የምትጠራ ሌላ የዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛም በክሱ ተካታለች።
ዲዲ እናቱን እና ሰባት ልጆቹንም ይቅርታ ጠይቋል።
"ከኔ የተሻለ ነገር ማግኘት ነበረባቸው፤ አዝናለሁ" ብሏል።
"ክቡር ዳኛ ይቅር ይበሉኝ። ተቀጥቻለሁ፤ ተምሬያለሁ። ከራሴው ውጭ ማንንም አልወቅስም" ሲልም ተማጽኗል።
ዲዲ ዝናውን ተጠቅሞ የወንጀል ቡድኖች ማደራጀቱን እንዲሁም የቀድሞ ፍቅረኞቹን በግዳጅ ወደ የወሲብ ንግድ ማስገባቱን ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ዲዲ በሚያዘጋጃቸው "freak-offs" በተባሉ ድግሶች ላይ የቀድሞ ፍቅረኞቹ ከሌሎች ወንዶች ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ በማስገደድ ድርጊቱን በቪድዮ ይቀርጽ እንደነበር ተገልጿል።
ራፐሩ አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም እና አካላዊ ጥቃት በመፈጸም ፍቅረኞቹ ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማስገደዱን ክሱ ያመለክታል።
የ55 ዓመቱ ዲዲ ሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ እና የተደራጀ የወንጀል ቡድን ማቋቋም ጨምሮ ሌሎችም ጠንካራ ክሶች ቢቀርቡበትም፤ ነሐሴ ላይ የዋለው ችሎት በክሶቹ ጥፋተኛ አይደለም ማለቱ ይታወሳል።
በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ዐቃቤ ሕግ ክርስቲ ሳልቪክ "ፍትሕ እና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ቀን ዛሬ ነው" ብለዋል።
"ጠንካራ ብይን ነው የሚያስፈልገው። የሚታሰረው ለአጭር ጊዜ ብቻ ከሆነ ለዓመታት ላደረሰው ብዝበዛ እና የቤት ውስጥ ቅጣት ሳይቀጣ ይቀራል" ሲሉም አክለዋል።
ዲዲ በሁለቱ የቀድሞ ፍቅረኞቹ ላይ ያደረሰውን አካላዊ ጥቃት የሚያሳዩ ምሥሎች በማስረጃነት ቀርበዋል።
"ድርጊቱን የፈጸመው ለገንዘብ ሳይሆን እነሱን ለመቆጣጠር ነው። በየትኛውም ዕድሜ ላይ ሆኖ አደገኛ ሰው ነው" ሲሉ ዐቃቤ ሕግ ተናግረዋል።
የዲዲ ጠበቃ ግን ደንበኛቸው "ገንዘብ እያገኘ ስላልነበረ" የወሲብ ንግድ ውስጥ ነበር ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
ጠበቃው ዲዲ "ያልታከመ ሕመም እና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ነበር" ብለው እስር ቤት በቆየባቸው ወራት ግን "መለወጡን" ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
ከዲዲ ልጆች መካከል አንዱ "አባቴ ተለውጧል" ሲል ሌላኛው "ሁለተኛ ዕድል ይሰጠው" በማለት ተማጽኗል።
ዲዲ "ከእናንተ ፊት ቆሞ የምታዩት ሰው ተለውጧል፤ አድጓል፤ በ15 ዓመታት ያልታየ ለውጥ አሳይቷል" በማለት ይቅርታ ጠይቋል።
ራፐሩ ከ50 ወራት እስራት በተጨማሪ 500,000 ዶላር እንዲቀጣም ተወስኗል።
ጠበቃው ይግባኝ እንደሚሉ ገልጸዋል።
ከቀድሞ ፍቅረኞቹ ጋር የነበረው ግንኙነት "በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ነው" በሚል ጠበቃው ቢከራከሩም ዳኛ አሩን ግን ውድቅ አድርገውታል።
ዳኛ አሩን "እነዚህ ሴቶች ላይ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ፈጽመሀል። ዕድሜ ልካቸውን አብሯቸው የሚኖር ጠባሳ ጥለህባቸዋል። ገንዘብ እና ዝና ስላለህ ድርጊትህን መቀጠል ችለሀል። በግዳጅ በቁጥጥርህ ሥር አውለሀቸው ቆይተሀል" ብለዋል።