ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሴቶችን የፊት ቅርጽ የሚያሳምሩ ዘዴዎች አሉ? በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩት መረጃዎችስ ትክክለኛ ናቸው?
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ውበትን ለመጠበቅ ፊትን በበረዳ የተሞላ ውሃ ውስጥ ከመንከር አንስቶ ቀዝቃዛ ነገር ፊት ላይ እስከማስቀመጥ ያሉ መንገዶችን መጠቀም ይመክራል።
እነዚህ መንገዶች ሲመለከቷቸው የሚሰሩ ቢመስሉም የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ግን በርካቶች በሚገባ እንዳልተረዷቸው እና ያለምንም ጥያቄ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ መፍትሄ ተብሎ የሚቀርበውም ጊዜያዊ መሆኑን ያብራራሉ።
የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አይዛ ጃሚል የፊት እብጠት የሚከሰተው ፈሳሽ ሲኖር፣ ከፍተኛ የሆነ ጨው እና አልኮል በመውሰድ እንዲሁም እንቅልፍ በማጣት የተነሳ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሌላኛዋ የቆዳ ስፔሻሊስት ዶ/ር ቲና ቲያን በበኩላቸው በኦንላየን የሚታዩት የፊት ስብ እንዲቀንስ ያደርጋል የሚባሉት መንገዶች በሦስት ሊከፈሉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ይህንንም ሲያስረዱ ለቅዝቀዜ መጋለጥ፣ ማሳጅ እና ጊዜያዊ የማጠንከር ውጤቶች መሆናቸውን ይዘረዝራሉ።
"የሚታየውን እብጠት በትክክል በመቀነስ እፎይታ መስጠት ይችላሉ፤ ነገር ግን እዚህ ላይ ቁልፉ ነገር ጊዜያዊ መሆኑ ነው፤ የፊት መዋቅርን በቋሚነት አይለውጡም።"
ታዲያ የፊት እብጠትን ለማስተካከል የሚረዳው ምንድን ነው?
1. የቅዝቃዜ ሕክምና
ፊትን በበረዶ ማሸት ወይንም በቀዝቃዛ ውሃ መንከር በማኅበራዊ ሚዲያ በተደጋጋሚ የሚነገር ውበት መጠበቂያ መንገድ ነው።
ቲና ይህ የውበት መጠበቂያ በስፋት የሚነገረው "ለቅዝቃዜ መጋለጥ የደም ስር እንዲጨማደድ በማድረግ እብጠትን ስለሚቀንስ ነው" ይላሉ።
ፊትን በበረዶ ማሸት ወይም በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ የመንከር መፍትሄ ምሥጢሩ ይህ ነው።
የፊት እብጠት እንዲቀንስ ፎጣን በፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ፣ በበረዶ ማሸት ወይንም በበረዶ መጫን አያስፈልግም፤ ቀዝቃዛ ውሃ ፊት ላይ ማፍሰስ የሚፈለገውን ተግባር ማከናወን ይችላል።
ዶ/ር አይዛ አክለውም "ትንሽ ጠበቅ የማለት እና የመነቃቃት ስሜት ይፈጥራል። በተለይ በጠዋት ከሆነ" ይላሉ።
ነገር ግን ይህ ውጤቱ ጊዜያዊ ሲሆን፣ ቆይታውም "ለቀናት ሳይሆን ለሰዓታት ነው" ብለዋል።
ቲና በተጨማሪም ከማነቃቃት በዘለለ ይህንን በተደጋጋሚ ማድረግ ስላለው ጉዳት ሲያስረዱ "በተደጋጋሚ ፊትን ለበረዶ ማጋለጥ ስሱ የሆነ ቆዳን ሊያስቆጣ ወይም ሽፍታን ሊቀሰቅስ ይችላል፤ ስለዚህ በጥንቃቄ መያዝ ተገቢ ነው።"
2. ፊት መዳመጫ
በአንድ ወቅት ልዩ የስፓ መሳሪያዎች፣ የፊት መጠቅለያዎች እና የመታሻ ድንጋዮች የነበሩት አሁን በብዙዎቻችን የመታጠቢያ ቤት የሚገኙ ዋና ቁሳቁሶች ሆነዋል።
የቅርጻ ቅርጽ መሳሪያዎች ተብለው የሚተዋወቁት እነዚህ መታሻዎች ፊትን በመወጠር እና በማስተካከል ዝናን አትርፈዋል።
ዶ/ር አይዛ ግን "ቆዳን ለዘለቄታው አያጥብቁም፣ የቆዳ መዋቅርን አይቀይሩም ወይም ስብን አያስወግዱም" ይላሉ።
በተጨማሪም "እንደ ማለስለሻ መሳሪያ" ማየት ጥሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሆኖም ግን ለጊዜው የፊት እብጠትን ለመቀነስ ይረዳሉ።
ዶ/ር ቲና በበኩላቸው "ለስላሳ ማሳጅ ከቆዳ ስር ያለ ፍሳሽን ያበረታታል ነገር ግን አዘውትሮ ጥቅም ላይ ከዋለ የፈሳሽ ክምችትን ይቀንሳል" ይላሉ።
እነዚህን ምርቶች በቆዳ ላይ ሲያንከባለሉ ወይም ሲያንሸራትቱ፣ የቆመው ፈሳሽ ከፊት ወደ ከቆዳ ስር ወዳሉ ዕጢዎች (ሊምፍ ኖዶስ) እንዲሄድ እየረዱ ነው።
ቲና መሳሪያዎቹን ማቀዝቀዝ ውጤቱን ከፍ ሊያደርግ ስለሚችል አንዳንድ ሰዎች በማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥን ይመርጣሉ ብለዋል።
በአግባቡ ከተሠራ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ይላሉ ዶ/ር ቲና "ከመጠን በላይ የሆነ ግፊት መቁሰል ወይም የደም ሥሮች መበጣጠስ ሊያስከትል ስለሚችል ረጋ ይበሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
3. ካፌይን ያለባቸው ክሬሞች
ካፌይን ያለበት የዐይን ክሬም ስላለው ጥቅም በተጽእኖ ፈጣሪዎች በስፋት ይወራል።
በዐይኖች ዙሪያ ያለው ቆዳ በተለይ ለማበጥ የተጋለጠ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ፈሳሽ በቀላሉ በአካባቢው ስለሚከማች መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
ከብዙዎቹ የውበት መጠበቂያዎች በተለየ መልኩ ዶ/ር ቲና ይህ የውበት መጠበቂያ ከበስተጀርባው የተወሰነ እውነት እንዳለው ይናገራሉ።
"ካፌይን የደም ሥሮችን ያጠባል፤ ስለዚህ ካፌይን የያዙ የዐይን ክሬሞች እብጠትን ሊቀንሱ ይችላሉ" ብለዋል።
ካፌይን የደም ሥሮችን እብጠት ለጊዜው ይቀንሳል፣ እና አነስተኛ እብጠት ማለት ብዙም የማይታይ እብጠት ማለት ነው።
ዶ/ር አይዛ ደግሞ "ከዓይን በታች የሚከሰት መጥቆርን ለመቀነስ" ይረዳል ሲሉ ያስረዳሉ።
የዐይን ክሬም ለመጠቀም ካሰቡ ዶ/ር ቲና ከካፌይን ጋር እርጥበት አዘል ንጥረ ነገሮችን የያዘ ክሬም እንዲፈልጉ ይመክራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የቆዳ ጥራትን መደገፉ ነው።
ክሬሙን በማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ ወይም "በቀዝቃዛ ማንኪያ ጀርባ መቀባት" እንደሚችሉ ጨምረው ገልፀዋል።
ዶ/ር አይዛ እንደ ቀዝቃዛ ማንኪያ ወይም የቀዘቀዘ የሻይ ከረጢት መጠቀም "እብጠትን ለጊዜው በመቀነስ እና ቆዳን በማረጋጋት በተመሳሳይ መልኩ ያገለግላሉ" ብለዋል።
ዶ/ር ቲና በዚህ ሃሳብ ተስማምተው እነዚህ ዘዴዎች ተመሳሳይ መርኅን ይከተላሉ "ነገር ግን አነስተኛ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ" ብለዋል።
የካፌይን የዐይን ክሬም እብጠትን ለመቀነስ ቢረዳም፣ ቲና በምክንያቱ ላይ ማተኮር የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ።
"አልኮልን ይቀንሱ፣ አለርጂዎችን በአግባቡ ያክሙ፣ በቂ እንቅልፍ ያግኙ እና ጭንቅላትዎን በትንሹ ከፍ አድርገው ይተኙ።"
አብዛኛው እብጠት የሕክምና ጉዳይ አይደለም እና በራሱ ይቀንሰል የሚሉት ዶ/ር ቲና "እብጠቱ ከቀጠለ፣ እየተባባሰ ከሄደ፣ ሕመም የሚሰማዎ ወይም እንደ ትንፋሽ ማጣት ወይም በሰውነት ውስጥ በሌላ ቦታ እብጠት ካለ ከሌሎች ምልክቶች ጋር የተያያዘ ከሆነ ሐኪም ሊያማክሩ ይገባል" ብለዋል።