ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር 'መንገዴን ስቼ ነበር' ሲል ከውሳኔው በፊት የዳኛውን ምህረት ጠየቀ
ታዋቂው አሜሪካዊ የራፕ ሙዚቀኛ ሾን "ዲዲ" ኮምብስ ያለፈውን ባህሪውን በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት መበላሸቱን በመግለጽ አርብ ከሚሰጠው ውሳኔ በፊት ምህረት እንዲደረግለት የወንጀል ችሎቱን ለሚከታተሉት ዳኛ ደብዳቤ መጻፉ ተነገረ።
አራት ገፅ ባለው ደብዳቤው ላይ "ላደረስኩት ጉዳት እና ስቃይ ሁሉ" በማለት ይቅርታ ጠይቋል። ለ13 ወራት በብሩክሊን እስር ቤት ማሳለፉን ተከትሎ ባህሪው መሻሻሉን ገልጿል።
ደብዳቤው የተጻፈው በጉዳዩ ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቀበት ሰዓት ነው።
በሐምሌ ወር በሁለት የዝሙት አዳሪነት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሲሆን እስከ 20 ዓመት እስራት ሊጠብቀው ይችላል። አቃቤ ሕግ ቢያንስ የ11 ዓመት እስራት ይገባዋል ያለ ቢሆንም የኮምብስ ጠበቆች ግን በዚህ ወር መጨረሻ እንዲፈታ እየጠየቁ ነው።
ኮምብስ ለዳኛ አሩን ሱብራማንያን በፃፈው ደብዳቤው ላይ ሙዚቀኛው የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ ቬንቱራ ላይ ጥቃት በማድረሱ "በእርግጥ አእምሮዬን ስቼ ነበር" ሲል ይቅርታ ጠይቋል።
"ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይቅርታዬ የሁልጊዜም ነው" ሲል ቀጥሏል። "የቤት ውስጥ ጥቃቱ ለዘለዓለም መሸከም ያለብኝ ከባድ ሸክም ይሆናል።"
በችሎቱ ወቅት "ጄን" በሚል ስም የመሰከረችውን ስሟ ያልተጠቀሰ ሴትንም ይቅርታ ጠይቋል። "በአደንዛዥ እጹ ከመጠን በላይ ጠፍቻለሁ" ብሏል።
"መንገድ ስቼ ነበር" ሲል ጽፏል። "የውድቀቴ መሠረቱ ራስ ወዳድነቴ ነው። ተዋርጃለሁ፤ እስከ ውስጤ ድረስ ተሰባብሬያለሁ።"
የኮምብ ከሳሾችም ኃይሉን እና ተጽዕኖውን እንዴት ተጠቅሞ ሕይወታቸውን እንደሚያበላሽ እና ነጻ ከወጣም ይበቀለናል የሚል ስጋት እንዳላቸው በመግለጽ ለዳኛው ደብዳቤ ጽፈዋል።
"ነፃ ከወጣ የመጀመሪያ ሥራው በእኔ እና ሌሎች በመሰከሩበት ላይ ፈጣን በቀል ይሆናል በሚል በጣም እፈራለሁ" በማለት ቬንቱራ ጽፋለች።
"ለመለወጥ ወይም ለመሻሻል ምንም ፍላጎት የለውም። እሱ ሁልጊዜም ጨካኝ፣ የሥልጣን ጥመኛ እና ተንኮለኛ ሰው ነው" በማለት ረጅም ቅጣት ይገባዋል ስትል አክላለች።
ኮምብስ በደብዳቤው ላይ "የተሳካ የንግድ ሰው ለመሆን ያደረግኩትን" ጉዞ ለታራሚዎች ማስተማሩን ገልጿል። ራሱን እንደለወጠ እና በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕጽ ነጻ ሆኖ መቆየቱን አስታውቋል።
"አሮጌው እኔ እስር ቤት ውስጥ ሞቶ አዲሱ እኔነቴ እንደገና ተወልዷል" ሲል ጽፏል።
ዳኛውን ምህረት ሲጠይቅም "ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለልጆቼም" ጭምር ነው ብሏል ኮምብስ።
ዳኛው ሰባት ልጆቹን እና በቅርቡ የአንጎል ቀዶ ህክምና ያደረጉትን የ84 ዓመቷን እናቱን ታሳቢ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
"አንድ ሰው ሁለተኛ ዕድል ከተሰጠው ምን ማድረግ ይችላል" ለሚለው ምሳሌ መሆን እንደሚችል ገልጿል።
ዳኛው የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት ኮምብስ በፍርድ ቤት ይናገራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከጠበቆቹ መካከል አራቱ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። የ15 ደቂቃ ቪዲዮ ለማሳየትም ታቅዷል። ቪዲዮው ምን ሊያካትት እንደሚችል ግልፅ አልተደረገም።