የካፍ ሽልማት: ቪክተር ኦሲምሄን የዘንድሮው ሽልማት ያመልጠው ይሆን?

ኦሲምሄን፣ ሐኪሚ እና ሳላህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የናፖሊው አጥቂ ኦሲምሄን ከሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ እና ከፓሪ ሳን ዠርማው አሽራፍ ሐኪሚ ፉክክር ይጠብቀዋል

ናይጄሪያዊው አጥቂ ሰኞ ዕለት የሚካሄደውን የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ መካከል ነው።

ነገር ግን የናፖሊው አጥቂ ከሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ እና ከፓሪ ሳን ዠርማው አሽራፍ ሐኪሚ ፉክክር ይጠብቀዋል።

ግብፃዊው አምበል ሞሐመድ ሳላህ የካፋ ሽልማትን በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2018 ወስዷል። በ2019 እና 2022 ደግሞ ሳዲዮ ማኔን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል።

የቀኝ ተመላላሹ አሽራፍ ሐኪሚ ደግሞ በ2022 የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ታሪካዊ ጉዞ ስታደርግ ትልቅ ሚና ከተጫወቱ መካከል አንዱ ነው።

ቢሆንም ኦሲምሄን በ2023 ባለን ደ ኦር ሽልማት ትልቅ ነጥብ ካመጡ አፍሪካውያን የእግር ኳስ ከዋክብት መካከል ቀዳሚው ነው።

ባለፈው የውድድር ዘመን ናፖሊ ከ33 ዓመታት በኋላ የጣሊያን ሴሪ አ ዋንጫን ሲያነሳ 23 ጎሎች ያስቆጠረው ኦሲምሄን በባለን ደ ኦር ሽልማት ስምንተኛ ወጥቷል።

ነገር ግን የዘንድሮውን ሽልማት ማንሳት ካልቻለ በአህጉሪቱ ትልቁን ሽልማት ካላነሱ ታላላቅ ተጫዋቾች መካከል ሊመደብ ግድ ይለዋል።

ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ከዚህ ቀደም የካፍ ሽልማትን ያላገኙ ታላላቅ ተጫዋቾችን እንዲህ ያወሳል።

ጄይ-ጄይ ኦኮቻ [ናይጄሪያ]

በእግር ኳስ ጨዋታ እጅግ ማራኪ ኳስ ከሚጫወቱ መካከል ይመደባል፤ የንስሮቹ የመሐል ሜዳ ሞተር ኦኮቻ።

ኦኮቻ ሦስት ጊዜ የካፍ ሽልማትን ለማግኘት ቢታጭም አንድም ጊዜ ሽልማቱን በእጁ ማስገባት አልቻለም።

በአውሮፓውያኑ 1998 የአፍሪካ ዋንጫን ካነሳው የናይጄሪያ ወርቃማው ትውልድ መካከል የሆነው ኦኮቻ በ1996 የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ሜዳሊያ ማንሳቱ ይታወሳል።

ኦኮቻ እጅግ ጎልቶ የወጣው በ1998 የፈረንሳይ የዓም ዋንጫ ላይ ነው። ኳስ በማንሸራተት ክህሎቱ የሚደነቀው ኦኮቻ፤ አገሩ ከዙር 16 ባታልፍም በሞሮኮው ሙስጠፋ ሐጂ ተበልጦ የካፍ ዋንጫን ሳያነሳ ቀርቷል።

ድጋሚ በአውሮፓውያኑ 2003 እና 2004 ቢታጭም በሁለቱም ወቅቶች በሳሙዔል ኤቶ ተበልጦ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል።

የቀድሞው የቼልሲ አማካይ ጆን ኦቢ ሚኬል በ2013 ሁለተኛ ሲወጣ፣ የቀድሞው የኤቨርተን አጥቂ ዳንኤል አሞካቺ ደግሞ በ95 እና 96 መታጨት ችሏል።

ማይክል ኢሲየን [ጋና]

ማይክል ኢሲየን (ከቀኝ) እና አሳሞሃ ጊያን (ከግራ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማይክል ኢሲየን (ከቀኝ) እና አሳሞሃ ጊያን (ከግራ)

ሌላኛው ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የተገኘው አማካይ ኢሲየን አስደናቂ ጎሎች ቢያስቆጥርም፤ ዋንጫዎች ቢያነሳም የካፍ ሽልማትን ለማግኘት ካልታደሉት መካከል ነው።

ኢሲየን ከሊዮን ጋር የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋንጫን ሁለት ጊዜ በተከታታይ አንስቷል። በ2005 የፈረንሳይ ሊግ 1 ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ኢሲየን፤ የአፍሪካ ክብረ-ወሰን በሆነ 24.4 ሚሊዮን ፓውንድ ነው ቼልሲን የተቀላቀለው።

ጋናዊው አማካይ 10 ዓመት ለመሆን ጊዜ ስታምፈርድ ብሪጅ ሲቆይ ሁለት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ አራት ኤፍ ኤ ዋንጫ ቻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ከቡድኑ ጋር ተጋርቷል።

በ2005 እና 2009 (እአአ) የአፍሪካ ምርጡ ሽልማት ዕጩ ነበር፤ በ2007 ደግሞ ፍሬድሪክ ካኖቴን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል።

ኢሲየን ብቻ ሳይሆን የጋና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አሳሞዋህ ጂያንም እንዲሁ የአፍሪካ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት ካላገኙት መካከል ነው።

ሞሐመድ አቡታሪካ [ግብፅ]

ግብፅ በአውሮፓውያኑ 2006 እና 2010 የማይደፈር ብሔራዊ ቡድን ሠርታለች። ሦስት ጊዜ በተከታታይ የአህጉሪቱን ዋንጫ አንስታለች።

ይህ ሁሉ ሲሆን የግብፅ ብሔራዊ ቡድን መመኪያ ከነበሩ መካከል አንዱ አቡታሪካ ነው።

ዐይኑ ለግብ ቅርብ የሆነው አማካይ ለአገሩ ካስገኘው ክብር ባለፈ ለክለቡ አል አህሊ አምስት ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና የካፍ ሱፐር ዋንጫ አስገኝቷል።

አቡታሪካ አገሩ እና አህጉሩን ለቆ ወደ ሌላ ክፍለ ዓለም ሄዶ መጫወት አለመፈለጉ ምናልባት የካፍ ዋንጫን እንዳያነሳ አድርጎት ይሆናል።

አቡታሪካ ወደ አፍሪካ ምርጡ ተጫዋች ሽልማት በዕጩነት የቀረበው አንድ ጊዜ ሲሆን፣ በ2008 (እአአ) በኢማኑኤል አዴባዮር ተቀድሞ ሁለተኛ ወጥቷል።

ሌላኛው ግብፃዊ ሆሳም ሐሰንም እንዲሁ የአፍሪካ ምርጡ መባል ከሚገባቸው ተብሎ ይመደባል።

ቤኒ ማካርቲ [ደቡብ አፍሪካ]

ማካርቲ (ከግራ) በአውሮፓውያን 2004 ከፖርቱጋሉ ፖርቶ ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ባነሳበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማካርቲ (ከግራ) በአውሮፓውያን 2004 ከፖርቱጋሉ ፖርቶ ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ባነሳበት ጊዜ

በአውሮፓውያኑ 1998 የአፍሪካ ዋንጫ በሰባት ጎሎች ከሆሳም ሐሰን ጋር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።

በ2004 ከጆዜ ሞሪንሆኖው ፖርቶ ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል።

አፍሪካ ካየቻቸው ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ነው። የደቡብ አፍሪካ የፊት መስመር ተጫዋች ቤኒ ማካርቲ።

በ1998 እና 2002 ደቡብ አፍሪካን ይዞ በዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፏል።

ነገር ግን በ1996 አገሩ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫን ስታሰናዳ እንዲሁም በ2010 የዓለም ዋንጫን ስታዘጋጅ ቤኒ ማካርቲ አልተካተተም።

ምንም እንኳ በፖርቹጋል እና በኔዘርላንድስ በርካታ ዋንጫዎችን ማንሳት ቢችልም፣ የካፍ ምርጡ የሚል ሽልማት መደርደሪያው ላይ የለም።

ሰይዶ ኬይታ [ማሊ]

የፔፕ ጉዋርዲዮላ ባርሴሎና ቁልፍ ተጫዋች ነበር። ሦስት ጊዜ በተከታታይ የላ ሊጋ ዋንጫን አንስቷል።

በ2008 ከሴቪያ ወደ ባርሴሎና ሲያቀና ለካታላኑ ክለብ የተጫወተ የመጀመሪያው የማሊ ዜጋ ሆኗል።

በ2009 አና 2011 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የአውሮፓ ሱፐር ዋንጫ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫን አንስቷል።

በ2011 ያያ ቱሬን ተከትሎ የአፍሪካ ምርጡ ሽልማት ሁለተኛ ሆኗል። ከዚያ በኋላ የማሊ ብሔራዊ ቡድን ይዞ በ2012 እና 2013 በአፍሪካ ዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ወጥቷል።

ካሊዱ ኩሊባሊ ሌላኛው የአፍሪካ ምርጡ ሽልማትን ያላገኘ ምዕራብ አፍሪካ ተጫዋች ነው።