የይለፍ ቃሎችን ጨምሮ የግል መረጃዎችን ለአጭበርባሪዎች የሚሸጠው ድረገጽ ተዘጋ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የይለፍ ቃሎችን ጨምሮ የግል መረጃዎችን ለአጭበርባሪዎች በመሸጥ የሚታወቀው ድረ-ገጽ በአለም አቀፍ ፖሊስ ትብብር ተዘጋ።
ድረገጹ በኢንተርኔት ላይ የማጭበርበር ስራ የሚፈጽሙ ግለሰቦች መረጃዎችን የሚሸምቱበት የዓለማችን ትልቁ የመረጃ መረብ ወንጀል ጣቢያ ሆኖም ቆይቷል።
ጄኔሲስ ማርኬት የተሰኘው ድረገጽ የግለሰቦችን ዲጂታል የጣት አሻራዎችን ጨምሮ፣ አድራሻዎችን እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን ለወንጀለኞች ሲሸጥ ነበር።
ከዚህ ድረገጽ የተገኙ የግል መረጃዎችና የይለፍ ቃሎች የግለሰቦችን የባንክ አካውንትና የኢንተርኔት ግዢዎችን በቀላሉ ወንጀለኞች እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ድረገጹ እነዚህንም መረጃዎች አብዛኛውን ጊዜም ከአንድ ዶላር ባነሰ ዋጋ ሲሸጥም ቆይቷል።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ የፖሊስና ደህንነትም በመቀናጀት ነው ይህንን የሳይበር የወንጀል ጣቢያ መዝጋት የተቻለው።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ (ኤንሲኤ) በተከታታይ ባደረገው ክትትልና ፍተሻ ድረገጹን ሲጠቀሙ ነበር የተባሉ 24 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል። ከነዚህም መካከል ድረ-ገጹን በመጠቀም የማጭበርበር ስራ እየፈጸሙ ነበር የተባሉ ግለሰቦችም ተካትተውበታል።
ማክሰኞ ረፋድ ላይ በተጀመረው ክትትልና ፍተሻ ከ17 አገራት የተውጣጡ ፖሊሶችና የደህንነት አባላት በቅንጅት ተሳትፈዋል።
ዘመቻው በአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ እና በኔዘርላንድ ብሄራዊ ፖሊስ የተመራ ሲሆን የዩኬው ኤንሲኤ፣ የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ እና በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ተጣምረውበታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ 200 ያህል ፍተሻዎች የተከናወኑ ሲሆን በዚህም 120 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ረቡዕ ዕለት ወደ ጀነሲስ ድረገጽ የገባ ማንኛውም ሰው ‘ኦፐሬሽን ኩኪ ሞንስተር’ የሚል ማስጠንቀቂያና ድረገጹም መቆሙን የሚያሳይ መልዕክት አግኝተዋል።
የጄኔሲስ ድረገጽ 80 ሚሊዮን የሚሆኑ የዲጂታል አሻራዎችና የግል መረጃዎችን ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የማጭበርበር ገበያ የተፈጸመበት እንደሆነም ተጠቅሷል።












