የሱዳኑ ጦር መሪ ለሰላም ንግግር ዝግጁ ነኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ከተፋላሚያቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ የጦር መሪዎች ሃገሪቱን ለመቆጣጠር እየተፋለሙም ይገኛሉ።
ጄነራል አብዱል ፈታህ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪው መሃመድ ሃም ዳጋሎ ሄምቲ ጋር ተቀምጠው ለመነጋገር በመርህ ደረጃ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
ጎራ ለይተው ለወራት እየተፋለሙ ባለው የሱዳን ጦርነት ከ5 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ህይወት መቅጠፉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያስረዳል።
በጦርነቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የቆጣጠሩት ጄነራል ቡርሃን በኒውዮርክ ለተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ካደረጉም በኋላ ከቢቢሲ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቆይታ አድርገዋል።
የሱዳን ጦር ኃይልን የሚመሩት ጄነራሉ አለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት እና ለአመራራቸው እውቅና ለማግኘት በተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ላይ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጄነራሉ ቃል እንደተገባው ስልጣኑናቸው ለሲቪል የሽግግር መንግሥት ማስረከብ አልቻሉም።
ጄነራሉ ጦራቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽመዋል የሚለውንም አስተባብለዋል።
ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የተለያዩ ረድዔት ተቋማት ጦራቸው መኖሪያ ስፍራዎችን ባልለየ መልኩ ጥቃት እንደፈጸመ ማስረጃዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
ድልን እንደሚቀዳጁ እርግጠኛነታቸውን ያሳወቁት ጄነራሉ መቀመጫቸውን ወደ ፖርት ሱዳን ለማዛወር መገደዳቸውን አምነዋል።
በመዲናዋ ካርቱም በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ከተማዋ በመንግሥት መቀመጫነት እንድትቀጥል አላስቻላትም።
ጄነራል ቡርሃን ከተፋላሚያቸው ሄምቲ ጋር ለሰላም ንግግር የሚቀመጡት በጅዳ ሳዑዲ አረቢያ በሁለቱም ወገኖች የተደረሰውን ሰላማዊ ዜጎች ለመጠበቅ የገቡትን ስምምነት እስካከበሩ ድረስ መሆኑንም ተናግረዋል።
“በድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን” ሲሉም ጄነራል ቡርሃን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“የእነዚህ ጨፍጫፊ ኃይሎች አመራሮች ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ወታደሮቻቸውን ከመኖሪያ አካባቢዎች አስወጥተው ወደ ጦር ሰፈራቸው የሚመለሱ ከሆነ ለሰላም እንቀመጣለን። በጅዳ ስምምነት መሰረት የተቀመጠውን ካከበሩ ቀውሱን ለመፍታት እንነጋገራለን” ብለዋል።
ጄነራል ሄምቲ በዚህ ሳምንት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ለፖለቲካዊ ንግግሮች ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሁለቱም ጄነራሎች በተደጋጋሚ ተኩስ አቁም ስለማድረግ ቢናገሩም ውጊያውን አላቆሙም። ጄነራል ቡርሃን አገራቸው እንደ ሶማሊያ መንግሥት አልባ ወይም እንደ ሊቢያ ትከፋፈላለች የሚለውንም በጽኑ ተቃውመዋል።
“ሱዳን በአንድነቷ ትጸናለች። ሱዳን አትነካም። መንግሥት አልባ አትሆንም። በሌሎች በጠቀስኳቸው አገራት የሆነው በኛ እንዲሆን አንፈልግም። በአሁኑ ወቅት የሱዳን ህዝብ በአንድ አላማ ተሰባስበዋል። ይህንንም እኩይ ተግባር በሰላማዊ መንገድ ወይም በጦርነት ያከትማል” ብለዋል።












