ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ወደ አውሮፓ ጋዝ የሚያስተላልፈው ቧንቧ እንደተዘጋ ይቆያል አለች
ሩሲያ ወደ ጀርመን ጋዝ የምታስተላልፍበትን ቧንቧ፣ በዕቅዷ ይዛው እንደነበረው ዛሬ ቅዳሜ እንደማትከፍት የሩሲያ መንግሥት የኃይል አምራች ኩባንያ የሆነው ጋዝፕሮም አስታወቀ።
ኩባንያው እንዳለው ሮርድስትሪም 1 በመባል በሚታወቀው የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ላይ የዘይት መፍሰስ ማግኘቱንና እሱንም ለመጠገን ላልተወሰነ ጊዜ ቧንቧው ዝግ ይሆናል።
ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ላለፉት ሦስት ቀናት ጋዝፕሮም ጥገና አካሂዳለው በማለት ዝግ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ በአውሮፓ እየገባ ባለው ከባዱ የክረምት ወቅት ቤቶችን ለማሞቅ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የጋዝ አቅርቦት የሚያስተጓጉል ሲሆን፣ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ስጋት ፈጥሯል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የኃይል አቅርቦት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን፣ ከሩሲያ በኩል ይቀርብ የነበረው ጋዝ የሚቋረጥ ከሆነ ደግሞ የሚፈጠረው እጥረት ዋጋውን የበለጠ ያንረዋል።
አውሮፓ ከሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ጥገኝነት እራሷን በማላቀቅ ሩሲያ ጦርነቱን ለማካሄድ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ለማሳጣት ጥረት ብታደርግም በቀላሉ ሊሳካላት አልቻለም።
ሞስኮ በዩክሬን ላይ ለፈጸመችው ወረራ በምዕራብ አገራት ለተጣሉባት ማዕቀቦች ምላሽ የኃይል አቅርቦቷን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ብትባልም፣ ሐሰት ነው ስትል ታስተባብላለች።
ሩሲያ የተጣሉባት ማዕቀቦች በጋዝ ማስተላላፊያ ቧንቧዎቿ ላይ በመደበኝነት የምታደርገውን የጥገና ሥራ በማስተጓጎሉ አቅርቦት ላይ ችግር ፈጥሯል ብትልም፣ አውሮፓውያኑ ግን ይህንን ሰበብ ነው ሲሉ አይቀበሉትም።
የጀርመን ባለሥልጣናት ግን የሩሲያ የጋዝ አቅርቦት የሚቋረጥ ከሆነ አገሪቱ በተሻለ ሁኔታ ዝግጅት አድርጋለች ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን አሁንም ዜጎች እና ተቋማት የጋዝ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ መክረዋል።
ይህ የጋዝፕሮም የጋዝ አቅርቦት መቋረጥ የተገለጸው የቡድን ሰባት አገራት ዩክሬንን በመደገፍ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ገደብ ለማስቀመጥ መስማማታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
የቡድን ሰባት አገራት የሚባሉት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ካናዳ ናቸው።
ይህ በሩሲያ የነዳጅ ምርት ላይ የተጣለው የዋጋ ገደብ ተግባራዊ ሲሆን፣ የቡድኑ አባል አገራት እና በዚህ የሚስማሙ ሌሎችም የሩሲያን ነዳጅ ሲገዙ በባሕር የተጓጓዘና በተቀመጠለት ዋጋ ወይም ከዚያ በታች ይሆናል።
ነገር ግን በምላሹ ሩሲያ በዚህ ስምምነት ውስጥ ለሚካተቱ አገራት የነዳጅ ምርቷን እንደማትሸጥ አሳውቃለች።
አውሮፓ ከሩሲያ በጣም የምትፈልገውን የጋዝ ምርት የሚያስተላለፈው ግዙፍ ቧንቧ ከሴንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ ካለው የሩሲያ ወደብ ተነስቶ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ጀርመን የተዘረጋ ሲሆን፣ በየቀኑ 170 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ጋዝ ይቀርብበታል።