ሩሲያ ሁለት የኒውክሌር ማብላያዎችን በሃንጋሪ ልትገነባ ነው

የሩሲያው ግዙፍ ኒውክሌር አምራች ሮሳቶም በቀጣይ ሳምንታት ሃንጋሪ ውስጥ ሁለት የኒውክሌር ማብላያዎችን እንደሚገነባ የሃንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።

የኒውክሌር ማብላያ ኒውክሌር ሲመረት የኤሌክሪክ ኃይል በማመንጨት የሚረዳ ሲሆን፣ ኒውክሌሩን በማንቀሳቀስም ከፍተኛ ሚና አለው።

እአአ በ2014 ሩሲያ እና ሀንጋሪ ፓክስ የተባለውን የሃንጋሪ የኒውክሌር ማብላያ ፋብሪካ ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ብትፈጽምም የኒውክሌር ኢንዱስትሪዋ ላይ በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ አልተጣለም።

በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በሩሲያ የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ሃንጋሪ አልደገፈችም።

ፓክስ የተባለው ኒውክሌር ማብላይ የሃንጋሪን 40 በመቶ የኤሌክተሪክ ፍጆታ ይሸፍናል።

የሃንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ስጃርቶ “ግንባታው ይጀመር” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል።

“በዚህ ግንባታ አማካይነት ሃንጋሪ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ይኖራታል። የሃንጋሪ ዜጎችን ዘለግ ላለ ጊዜ ከውድ የነዳጅ ዋጋም ይታደጋል” ብለዋል።

ኒውክሌር ማብላያው በአውሮኣፓውያኔ 2030 ላይ ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አወዛጋቢው ይህ ፕሮጀክት 12.4 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣበት ሲሆን፣ ለግንባታው የሚያስፈለግውን አብላጫውን ገንዘብ የምትሸፍነው ሩሲያ ናት።

የዩክሬን ጦርነት የተጀመረ ጊዜ ብዙ የአውሮፓ አገራት በኃይል አቅርቦት ረገድ ሩሲያ ላይ ካላቸው ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥረት አድርገዋል።