ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ትምህርት ቤት መኪና እያሽከረከረ ሲሄድ የተያዘው የ9 ዓመቱ ታዳጊ አባት ታሰረ
አንድ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ተማሪ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሱን እንደለበሰ የአባቱን መኪና እያሽከረከረ ሲሄድ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በፖሊስ ተያዘ።
ታዳጊው በናይሮቢ ውስጥ ከሚገኙ በአንደኛው አውራ ጎዳና ላይ የአባቱን መኪና በፍጥነት እያሽከረከረ የነበረው አባቱን ከጎኑ አስቀምጦ ነበር ብሏል ፖሊስ።
ታዳጊው መኪናውን በሚያሽከረክርበት ጊዜ ከአባቱ በተጨማሪ አብራው ወደ ትምህርት ቤት የምትሄደው የሰባት ዓመት ታናሽ እህቱም ከኋላ ተቀምጣ ነበር።
ይህ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎችን ከሚያስተናግዱ ጎዳናዎች ቀዳሚ በሆነው፣ ዋና ከተማዋ ናይሮቢን ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ጋር በሚያገናኘው አውራ ጎዳና ላይ በፍጥነት ሲያሽከረክር ነበር ተብሏል።
አነስ ያለችውን የቤት መኪና እያሽከረከረ የነበረው ታዳጊ በሌሎች አሽከርካሪዎች ከታየ በኋላ ለፖሊሶች በደረሰ ጥቆማ ክትትል ተደርጎበት መያዙን ኮማንደር ሜሪ ንጆኪ ተናግረዋል።
ታዳጊው ፖሊስ እየተከታተለው መሆኑን ሲያውቅ ፍጥነቱን ጨምሮ በማምለጥ ወደ ትምህርት ቤቱ ለመግባት ሲሞክርም ከፖሊሶች እጅ ለማምለጥ ሳይችል እንዲቆም ተደርጓል።
አሰቃቂ የመኪና አደጋ በሚያጋጥምባት ናይሮቢ ውስጥ በአባቱ ፈቃድ መሪ እንዲጨብጥ የተደረገው የዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ እንዲሁም እህቱ በፖሊስ ሲያዙ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው ነበር።
እንደ በርካታ አገራት ሁሉ በኬንያም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች መኪና እንዲያሽከረክሩ በሕግ አይፈቀድላቸውም።
ፖሊስ መኪናውን ተከታትሎ ካስቆመው በኋላ ታዳጊዎቹን ወደ ትምህርት ቤታቸው ያደረሰ ሲሆን፣ “ግዴለሽ” የተባለውን አባታቸውን ደግሞ ወደ እስር ቤት ወስዷል።
የታዳጊውን አባት ከሶ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርበው የገለጸው ፖሊስ “ይህ ድርጊት ኃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፣ ታዳጊዎቹን እንዲሁም ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ የሕግ ጥሰት ነው” ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ጽፏል።
ጨምሮም “ተጠርጣሪው አባት ሕጻናትን ከጉዳትና ከአደጋ የመጠበቅ የወላጅን ቀዳሚ ኃላፊነት በጣሰ ሁኔታ ልጆቹን ለአደጋ አጋልጧል” ብለወል ፖሊስ።
በአገሪቱ ሕግ መሠረት አባት ይህ ድርጊቱ የመጀመሪያው ከሆነ 200 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ወይም ከሦስት ወር ያልበለጠ የእስር ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።