ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ5 ሜትር በላይ የሚረዝም ዘንዶ ሰው ቤት ለመግባት መሞከሩ ድንጋጤን ፈጠረ
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 5.5 ሜትር ወይም 18 ጫማ የሚረዝም ዘንዶ ወደ አንድ ግለሰብ ቤት በመስኮት በኩል ሊገባ ሲሞክር መታየቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ድንጋጤን ፈጠረ።
በኢንግላንድ ቻንድለርስ ፎርድ በተባለ መንደር የሚኖሩ ሰዎች ግዙፉ ዘንዶ ፎቅ ላይ ወደ ሚገኝ ቤት ሊገባ ሲል ነው የተመለከቱት።
በርሚዝ የተባለው የዘንዶ ዓይነት ከአንድ ሰው ቤት አምልጦ ነበር ወደ ሌላ ሰው ቤት በመስኮት ለመግባት የሞከረው።
ሊንዳ ኤልመር የተባለች የአካባቢው ነዋሪ ዘንዶውን ለባለቤቱ እንዲመለስ አድርጋለች።
“አንደኛ ፎቅ ላይ ባለው መስኮት ወደ ቤት ለመግባት ሲሞክር ሰዎቹ በእንጨት ሲገፉት መኪናቸው ላይ ወድቋል። ዘንዶው ግዙፍ ነው። በሰፈሩ እያለፉ የነበሩ ሰዎች ዐይናቸውን ማመን አቅቷቸው ተደናግጠው ነበር” ብላለች።
የሰፈሩ ነዋሪዎች የዘንዶውን ባለቤት እንድትፈልግ ጠይቀዋታል።
“ከዚያም ዘንዶውን አነሳሁት። በጣም ግዙፍ ዘንዶ ስለሆነ ለመሸከም ከብዶኝ ነበር። ግን ማንም ሊረዳኝ አልፈቀደም። 18 ጫማ የሚረዝመው ዘንዶ ሰውነቴ ላይ ተጠምጥሞ ወደ ዘንዶው ባለቤት መኖሪያ ሄድኩ” ስትል ክስተቱን አብራርታለች።
ከዚህ ቀደም የአካባቢው የእንስሳት ተቆጣጣሪ አካል፣ እባብ ያላቸው ነዋሪዎች በጥንቃቄ ጠብቀው እንዲይዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
አሁን ባለው የአውሮፓ ሙቀት ምክንያት እባቦች ከቤታቸው አምልጠው የሚወጡበት ዕድል እንደሚሰፋ ማስጠንቀቂያው ያክላል።
ዘንዶውን ለባለቤቱ የመለሰችው ሊንዳ ኤልመር፣ “በርሚዝ ዘንዶ በጣም ለማዳና ቆንጆ ነው። ቁጡ አይደለም። እኔም አንድ ዘንዶ ነበረኝ። እና ይሄኛውን ዘንዶ ሳቅፈው ምቾት አልነሳኝም” ብላለች።