ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓ ወንዶች የማይገረዙት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የሚገረዙት ለምንድን ነው?
የወንድ ልጅ ግርዛት በአውሮፓ አገራት ውስጥ የተለመደ አይደለም።
በአፍሪካ እና በአሜሪካ እንዲሁም የእስልምና እምነት በሚከተሉ አገራት ውስጥ ደግሞ የወንድ ልጅ ግርዛት ከባሕልና ከእምነት ጋር የተቆራኘ ነው።
ለምሳሌ በጋዛ ሰርጥ ያሉ 99.9 በመቶ ወንዶች ተገርዘዋል። በሞሮኮና በአፍጋኒስታንም እንዲሁ ከ99 በመቶ በላይ ወንዶች የተገረዙ ናቸው።
ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው የተሰኘው ገፅ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ ከ92 በመቶ በላይ ወንዶች የተገረዙ ናቸው። በኤርትራ ደግሞ ቁጥሩ ከ97 በመቶ በላይ ነው።
በተቃራኒው በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ አገራት የወንድ ልጅ ግርዛት በመቶኛ ሲሰላ ከዜሮ በታች ነው።
ግርዛት ከወንድ ልጅ ብልት ላይ ሸለፈት አሊያም በእንግሊዝኛ ፍርስኪን የተሰኘው ቆዳ የሚለይበት ዘዴ ነው።
ለመሆኑ ይህ የሆነበት ምክንያት እና የግርዛት ጥቅሙ ምንድነው? ጉዳትስ ይኖረው ይሆን?
የሕክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
ዶክተር በዕደ ለማ በአዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል የሽንት ቧንቧ እንዲሁም የወንዶች የመራቢያ አካላት ስፔሻሊስት [ዩሮሎጂስት] ናቸው።
ስፔሻሊስቱ ወደ ግርዛት ጥቅምና ጉዳት ከማምራታችን በፊት አጀማመሩን እንመለከት ዘንድ ግድ እንደሆነ ይገልጣሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት የወንድ ልጅ ግርዛት አጀማመር ከሕክምና ጋር ሳይሆን ከሃይማኖትና ከባሕል ጋር ቁርኝት ያለው ነው ያላሉ።
ዶክተሩ እንደሚያስረዱት ግርዛት ጥቅም እንዳለው የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ጥናት ከኤችአይቪ ሥርጭት ጋር የተገናኘ ነው።
የተገረዙ ወንዶች ካልተገረዙት ጋር ሲነፃፀር ለኤችአይቪ የመጋለጥ ዕድላቸው ከ50 አስከ 60 በመቶ ቀንሶ መታየቱን ያወሳሉ።
ይህን ጥናት ተከትሎ ያልተገረዙ ወንዶች እንዲገረዙ ምክር መሰጠት እንደተጀመረ ዶክተር በዕደ ይናገራሉ።
የግርዛት ጥቅሙ ምን ይሆን? ዶክተር በዕደ እንዲመልሱ ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነው።
"ምንድነው ጥቅሙ? በተለይ ንፅሕናን በሚገባ መጠበቅ በማይችል ማኅበረሰብ ውስጥ የተገረዙ ወንዶች እስከ ካንሰር ድረስ ከሚያደርስ ‘ኢንፌክሽን’ ለመከላከል ሊጠቅማቸው ይችላል።"
ዋናው የግርዛት ጥቅሙ ይህ ነው ይላሉ ዶክተሩ። በተለይ ከሸለፈት ጋር በተያያዘ ለሚመጡ በሽታዎች ግርዛት አንዱ መከላከያ ነው።
ዶክተር በዕደ ግርዛት በምዕራቡ ዓለም ብዙ ተቀባይነት የሌለው ከሃይማኖት እና ከባሕል ተፅዕኖ ወጣ ያለ በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ቫቲካን ከዓለም አገራት በጣም ዝቅተኛው የተገረዙ ወንዶች ያሉባት እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ።
በሕክምናው ዓለም እንደምሳሌ በምትነሳው ደቡብ አሜሪካዊቷ ኩባ የወንድ ልጅ ግርዛት ከመቶኛ ሲታይ 0.10 ነው።
በፖርቹጋል 0.6%፣ በጃፓን 9%፣ ፈረንሳይ 14%፣ በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 20 በመቶ ነው።
በዚህ የአገራት ደረጃ ምደባ ላይ ብዙ የተገረዙ ወንዶች ያሉባቸው ሰፊ እስልምና እምነት ተከታይ የሚገኝባቸው አገራት ናቸው።
ከዚያ ባለፈ እንደ ኤርትራ እና ናይጄሪያ እንዲሁም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ከ90 በመቶ በላይ ወንዶች የተገረዙባቸው ናቸው።
አውሮፓውያን አገራት ምንም እንኳ የክርስትና እምነት ቢከተሉም ግርዛት ሃይማኖታዊ ግዴታ ተደርጎ አይወሰድም ይላሉ ዶክተር በዕደ።
"በሃይማኖትም በሳይንስም ድጋፍ ስሌለው ብዙዎቹ አይገረዙም። እንዲያውም አንዳንድ ቦታዎች ግርዛት ክልክል ነው።"
ሃይማኖታዊ ቅኝት
በአብዛኛዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሚገኙባቸው አገራት ወንዶች በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይገረዛሉ።
ይህ በአብዛኛው ማኅበረሰብ፣ በልምድ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ባሕላዊ ሥርዓት የሚከወነው የልምድ አሊያም የባሕል ሐኪም በሚባሉ ግለሰቦች ነው።
ባሕላዊ የወንዶች ግርዛት አብዛኛው ጊዜ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው ሲሆን፣ ባለንበት ዘመን አብዛኞቹ የእስልምና እና የአይሁድ እምነት ተከታይ ወንዶች ልጆቻቸውን ያስረግዛሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በዓለም 30 በመቶ ወንዶች ይገረዛሉ፤ ከእነዚህ መካከል ሁለት ሦስተኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።
በእስልምና እምነት ይህ ልምድ ‘ታሄራ’ ተብሎ ይጠራል።
በአይሁድ እምነት ደግሞ አንድ ወንድ ልጅ በተወለደ በአምስተኛው ቀን መገረዝ አለበት።
በሂንዱና ቡድሃ እምነት ተከታዮች ዘንድም ግርዛት ይፈጸማል።
በግብፅ የኮፕቲክ ቤተ-ክርስቲያን አማኞች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናንም ይህንን ይከተላሉ።
በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ፀሐፊ ሊቀ ስዩማን የሆኑት ቀሲስ አክሊሉ ገብረሥላሴ በክርስትና ተከታዮች የወንድ ልጅ ግርዛት ግድ የነበረበት ወቅት ነበር ይላሉ።
ይህም በብሉይ ኪዳን "ያልተገረዘ ሰው አይድንም፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሳይሆን አህዛብ ነው" ይባል ስለነበር ነው ይላሉ።
እስራኤላውያን፤ ያልተገረዘ የአብርሃም ልጅ ስለማይባልና ያንን ማድረግ ግድ ስለነበረባቸው አሁንም ሥርዓቱን እንደሚፈፅሙ ቀሲስ አክሊሉ ያስረዳሉ።
ከክርስቶስ ልደት በኋላ ግን ይህ በብሉይ ኪዳን ከቀሩ ሥርዓቶች መካከል አንዱ በመሆኑ አሁን በሃይማኖታዊ ሥርዓት የወንድ ልጅ ግርዛት መፈጸም ግዴታ እንዳልሆነ ቀሲስ አክሊሉ ያብራራሉ።
ከግሪክ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ ክርስትናን ተቀብለው ወደ እስራኤል የሚመጡ ሰዎች አይገረዙም ነበር።
በዚህ ምክንያት እናንተ አልተገረዛችሁም፤ አትድኑም፤ ብለው አይሁዶች ይወቅሷቸው ስለነበረ፣ ቅዱስ ጳውሎስ "መገዘርም አለመገዘርም አይጠቅምም፤ በክርስቶስ ያመነ ይድናል" ብሎ ማስተማሩን ቤተክርስቲያኒቷ ትጠቅሳለች።
"አሁን ምልክቱ በክርስቶስ ማመንና መጠመቅ ነው። ስለዚህ ወንድ ልጅ ባይገረዝም በእምነቱ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም። እኛ አገር ግን ያንን አለማድረግ [አለመገረዝ] እንደ ነውር ይቆጠራል። ይህ እኛም ብሉይ ኪዳን የምንቀበል ሰዎች ስለነበርን ባሕሉን ለማስቀረት ይከብደናል እንጂ ከክርስትና ጋር የሚያይዘው የለም።"
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድ ደግሞ የወንድ ልጅ ግርዛት ወደ አቅመ አዳም መሸጋገሪያ ምልክት ነው።
ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት፣ በአሜሪካ፣ በፓስፊክ እና በፖሊኔዢያ ደሴቶች ያሉ ማኅበረሰቦች ባሕላዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በሚል ለበርካታ ሺህ ዓመታት የወንድ ልጅ ግርዛት ሲተገብሩ ቆይቷል።
የወንድ ልጅ ግርዛት ካለው ሃይማኖታዊ ዳራ ባሻገር በአንድ አገር ውስጥ ከባሕል ባሕል እንደሚለያይም የዓለም ጤና ድርጅት ይጠቅሳል።
ለምሳሌ 84 በመቶ ኬንያውያን ወንዶች የተገረዙ ቢሆኑም፤ የወንድ ልጅ ግርዛት በሉዎ እና ቱርካና ማኅበረሰብ ዘንድ ዝቅተኛ ነው።
በተጨማሪም የሉዎ ማኅበረሰብ አባላት በሚኖሩባቸው የኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን አካባቢዎች የሚገኙ ወንዶች አይገረዙም።
በምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ ባሉ አገራት ደግሞ ግርዛት የኤችአይቪ ሥርጭት ለመቀነስ ያግዛል በሚል አንድ የማኅበረሰብ ጤና መንገድ ተደርጎ ትልቅ ቅስቀሳ ይደረግበታል።
ሳይንሳዊ ምክር
"እኔ ግርዛት አልመክርም" ይላሉ ዶክተር በዕደ።
ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፤ "በሕክምናው ግርዛት ግዴታ ስላልሆነ ተገረዙ አልልም። ነገር ግን እንደ ማኅበረሰቡ ሁኔታ ወንዶች ቢገረዙ ተቃውሞ የለኝም።"
ስለወንድ ልጅ ግርዛት ጥቅም በሰፊው ቃኘን። ጉዳትስ ይኖረው ይሆን?
"አዎ! ጉዳት ይኖረዋል" ይላሉ ስፔሻሊስቱ።
ዶክተር በዕደ እንደሚሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የወንድ ልጅ ግርዛት በአብዛኛው የሚከናወነው የሕክምና ባለሙያ ባልሆኑ ሰዎች ነው።
"በዚህ መልኩ ሲከናወን [የወንድ ልጅ ብልት] ሊደማ ይችላል፤ ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል። አልፎም ተገቢ ያልሆነ ቦታ ላይ ተገርዞም ሊሆን ይችላል። ሸለፈቱን ከሚገባው በላይ ስበወት የመሸማቀቅ አደጋ ሊደርስበትም ይችላል።"
በባሕላዊ መንገድ የሚደረግ ግርዛት በርካታ መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ባለሙያው ያስረዳሉ።
በተለይ ደግሞ ይላሉ ዶክተር በዕደ፤ ጨቅላ ሕፃናት ሲገረዙ ለመሰል አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
ነገር ግን በሕክምና ተቋም የሚሰጥ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ከ5 በመቶ በታች ነው ይላሉ።
"መገረዝ የሌለባቸው ማለትም በሕክምና ታይተው እንዳይገረዙ የሚባሉ ሕፃናት አሉ። ለምሳሌ ‘ሂመፐፊሊያ’ የሚባል ሕመም አለ። በዘርም ሊመጣ ስለሚችል ሕፃናትን የማጥቃት ዕድል አለው፤ ይህ ያለባቸው ሰዎች እንዲገረዙ አይመከርም። ባሕላዊው መንገድ ይህንን ከግምት አያስገባም።"
ስፔሻሊስቱ ምንም እንኳ በሥራቸው ባያጋጥማቸው ካነበቧቸው የሕክምና ዘገባዎች በመነሳት ግርዛት ወሲባዊ እርካታን ሊቀንስ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
ግርዛት በሁለቱም ጾታዎች የሚፈጸም ሥርዓት ነው። ሆኖም የሴት ልጅ ግርዛት አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጥ የተባበሩት መንግሥታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም ያሳስባል።
ድርጅቱ በ2019 ባወጣው መረጃ በዓለማችን ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ ግርዛት ተግባራት ተፈፅሟል ይላል።
የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ ያለው ወደ 30 በሚጠጉ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሲሆን፤በእስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አገራትም የሴት ልጅ ግርዛት ይፈጸማል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሆነ በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ የሚኖሩ ስደተኞች ሕግን በመተላለፍ ሴት ልጆቻቸውን ያስገርዛሉ።
የሴት ልጅ ግርዛት ሆነ ተብሎ የሴት ልጅን የመራቢያ ክፍል አካል መቁረጥ ማለት ነው።