የሩሲያ ጦር ሠራዊት ቁጥር በ10 በመቶ እንዲጨምር ፑቲን አዘዙ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጪዎቹ ወራት 137,000 አዲስ ወታደሮች ወደ አገሪቱ ጦር ኃይል እንዲቀላቀሉ የሚያስችል አዋጅ ፈረሙ።

ሩሲያ ጦር ሠራዊቷ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች እና ወደ 900,000 የሚጠጉ ሲቪል ሠራተኞች እንዲኖሩት የሚያደርግ ገደብ አላት።

የቭላድሚር ፑቲን አዋጅ በመላ አገሪቱ በከፍተኛ የገንዘብ ማበረታቻዎች ቅጥር በሚፈጸምበት ጊዜ የመጣ ነው።

ሩሲያ ከስድስት ወራት በፊት ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከ70 አስከ 80 ሺህ ወታደሮቿ መገደላቸውን ወይም መቁሰላቸውን ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኃላፊዎች እስር ቤቶችን በመጎብኘት ታራሚዎች ጦሩን ከተቀላቀሉ በነጻ እንደሚወጡ እና ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል መግባታቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንታት በፊት በሰጠው መግለጫ በበርካታ የሩሲያ ክልሎች ከበጎ ፈቃደኞች የተወጣጣ አዲስ የጦር ሠራዊት ክፍል ሊመሰርት እንደሚችል ገልጸዋል።

"በዩክሬን ለሚደረገው ጦርነት በፈቃደኛነት የሚዘምት ሰው ቁጥር በጣም ውስን" ነው በማለትም የሚፈለገውን ወታደር ቁጥር ማግኘት አስቸጋሪ ነው ብሏል።

ሩሲያ በየካቲት ወር ዩክሬንን በወረረችበት ጊዜ አጭር እና ወሳኝ ዘመቻ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር። ከዩክሬን በኩል የገጠማት ከፍተኛ መከላከል ግስጋሴዋን ያገደው ሲሆን በቅርብ ሳምንታትም እንቅስቃሴዋ እምብዛም ነው።

በሩሲያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የጸደቀው ድንጋጌ "የሩሲያ ፌዴሬሽን የጦር ኃይል ቁጥር 2,039,758 እንዲሆን ተወስኗል። 1,150,628 ያህሉ ወታደራዊ ሠራተኞች ይሆናሉ" ይላል።

በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ በ1,013,628 ወታደሮች ተወስኗል። ወረራው ከመጀመሩ በፊት ትክክለኛው ቁጥር 900,000 ይጠጋል ነበር ተብሎ ይገመታል።

የሠራዊቱን ቁጥር ከፍ ለማድረግ አሁን የጸደቀው አዋጅ መንግሥት ለዚህ ዓላማ ከፌዴራል በጀት ገንዘብ እንዲሰጥ ይጠይቃል። ይህም በሚመጠው ዓመት ጥር ወር ላይ ተግባራዊ ይሆናል።

ቁጥሩ በጎ ፈቃደኞችን በመመልመል ወይም በግዳጅ እንዲጨምር ስለመደረጉ ምንም ግልጽ አይደለም።

ከ18 እስከ 27 ዓመት የሆኑ ሩሲያውያን ወንዶች ጥሪው ይመለከታቸዋል። ብዙዎቹ የአገልግሎት ጊዜውን በሕክምና ወይም በከፍተኛ ትምህርት በማሳበብ ያስቀራሉ ወይም ወደ አንድ ዓመት ይቀንሱታል።