የአፍሪካ አገራት ቱርክ ሠራሹን ባይራክታር ቲቢ2 ድሮን ለምን ይገዛሉ?

እንደ ዛሬው የአውሮፓ አገራት ዩክሬንን በከባድ የጦር መሣሪያ መደገፍ ከመጀመራቸው በፊት፣ ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ወረራ ለመከላከል በስፋት ትጠቀም የነበረው አንድ መሣሪያ ነበር።

ባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) ይባላል። ቱርክ ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ነው።

ይህ መሣሪያ የጠቀመው ዩክሬንን ብቻ አይደለም።

ከሁለት ዓመት በፊት አዘርባጃን የአርሜንያን ኃይሎች ድል ነስታ ግዛቷን ያስመለሰችው በዚህ ሰው አልባ አውሮፕላን ነበር።

ይህ ድሮን በአህጉረ አፍሪካም ፈላጊዎች አሉት።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ምዕራብ አፍሪካዊቷ ቶጎ ድሮኑን ገዝታለች።

ቶጎ ከቡርኪና ፋሶ ሰርገው ከሚገቡ ጂሀዲስቶች ጋር ውጊያ ገጥማለች።

ያለፈው ግንቦት ኒጀር ግማሽ ደርዘን ባይራክታር ቲቢ2 ሸምታለች።

ኒጀር በሰሀል ቀጠና ከሽምቅ ተዋጊዎች ጋር እየተዋጋች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና አንጎላም ይህንን ድሮን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል።

ከሌሎች አገራት ቀድሞ ይህንን ድሮን ጥቅም ላይ ያዋለው የመንግሥታቱ ድርጅት ዕውቅና የሰጠው የሊቢያ መንግሥት ነበር።

እአአ በ2019 ነበር ይህ ሰው አልባ አውሮፕላን በሊቢያ የታየው።

የትሪፖሊ መንግሥት የምሥራቁን አማጽያን መቋቋም የቻለው በዚህ መሣሪያ ድጋፍ እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም የግዢ አቅማቸው ውስን የሆኑ ድሃ የአፍሪካ አገራት ድሮን የሚመርጡት ያለ ምክንያት አይደለም።

ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የጦር መሣሪያዎችን ከመሸመት ይልቅ፣ ድሮን ገዝቶ የአየር ላይ የጦር የበላይነት መቀዳጀት ይመርጣሉ።

ሌሎች እንደ ጦር ጀት ያሉ የአየር መሣሪያዎች ለዓመታት የሠለጠኑ አብራሪዎችን ይሻሉ።

ድሮን ግን እንደዚያ አይደለም።

እስላማዊ ታጣቂዎች የፈተኗቸው ኒጀር እና ቶጎ ድሮን የመረጡትም ለዚሁ ነው።

ታጣቂዎቹ ጫካ ውስጥ በፍጥነት ስለሚዘዋወሩና በሳሀል በረሃ በሞተር እየተጓዙ ድንገተኛ ጥቃት ስለሚሰነዝሩም ለመቆጣጠር ያስቸግራሉ።

በአንድ አካባቢ ተነጥለው በሚገኙ ወታደሮችን እንዲሁም ንጹሃን ዜጎችንም ያጠቃሉ።

ኒጀር፣ ከቡርኪና ፋሶ እና ከማሊ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ታጣቂዎችን ትዋጋለች።

አካባቢው ከመዲናዋ ኒያሚ አቅራቢያ ነው።

በደቡባዊ ክልሏ ደግሞ ከናይጄሪያው እስላማዊ ታጣቂው ቡድን ከቦኮ ሀራም ጋር ትፋለማለች።

ላለፉት ዓመታት ታጣቂዎቹ በስፋት የሚንቀሳቀሱት በማሊ፣ በቡርኪና ፋሶ እና በኒጀር ነበር።

አሁን ግን ቶጎም ገብተዋል።

እአአ 2029 ማገባደጃ ላይ በሰሜን ቶጎ የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ መታየት ጀምሯል።

ከዚያ ነው ወደ አራት አጎራባች አገራት መስፋፋት የቀጠሉት።

የቶጎ ጎረቤት አይቮሪ ኮስት እአአ በ2026 በግራንድ ማሳም 19 ሰዎች የገደለ የሽብር ጥቃት ደርሶባታል።

በ2020 ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲጋጩም ነበር።

ታጣቂዎቹ ሁለት ፈረንሳያውያን ቱሪስቶችን ባገቱ ወቅት አንድ የዱር እንስሳት አስጎብኚን ተገድሏል።

ባለፈው ጥቅምት በቶጎ በሚገኘው ሳንሎንጋ ቀጥተኛ ጥቃት ተሰንዝሯል።

ግንቦት ላይ ደግሞ ቡርኪና ፋሶ አቅራቢያ በሚገኘው ክፒክ-ፓክንዲ ባሉ ወታደሮች ላይ ታጣቂዎች ጥቃት አድርሰዋል።

በዚህም ስምንት ወታደሮች ሲሞቱ 13 ቆስለዋል።

ወታደሮቹ በመልሶ ማጥቃት የተወሰኑ ታጣቂዎችን ገድለዋል።

በቀጣዩ ወር በቶጎ ሰሜናዊ ክልሏ ሳቫንስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።

ሆኖም ግን ጂሀዲስቶቹን ለመግታት አልተቻለም።

አሁን ታጣቂዎቹ ማሊ ከሚገኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን 'ጃማ ኑስራት ኡልኢስላም ዋ አልሙስሊሚን' ጋር ትስስር ፈጥረዋል።

ሐምሌ ላይ ሁለት ወታደሮች የተገደሉበት ጥቃት ተፈጽሟል።

ፕሬዝዳንት ፋውሬ ጋሲንግቤ የዜጎችን ሥነ ልቦና ለማጎልበት አካባቢውን ጎብኝተዋል።

በጥቃቱ የተደናገጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ከቀጠናው ሸሽተው እየወጡ ነው።

በሌሎችም የሳሀል አካባቢዎች የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ተከትሎ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየሸሹ ይገኛሉ።

ለብቻው ለዓመታት ፖለቲካውን የተቆጣጠረው መንግሥት፣ ተቃዋሚዎችን በማሳተፍ ስለ ብሔራዊ ደኅንነት ዕቅድ መንደፍ ጀምሯል።

ነገር ግን ጉልህ ለውጥ የሚያመጣው ወታደራዊ እርምጃ ነው።

የቱርክ ድሮን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለገውም ለዚህ ነው።

ልክ እንደ ኒጀር ሁሉ ቶጎም በድሮን የአየር ላይ ቁጥጥር ታደርጋለች።

ታጣቂዎችን ለመምታትም ታውለዋለች።

ከዚህ ቀደም በሳሀል ቀጠና ፈረንሳይና አሜሪካ በድሮን የታገዘ የደኅንነት ቅኝት ያካሂዱ ነበር።

በኢትዮጵያም በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት ድሮን የወታደራዊ አቅም ለውጥ ምክንያት ሆኖ ታይቷል።

ድሮኖች በተለያዩ አገራት ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አደጋ ማስከተላቸው አይዘነጋም።

በጥር ወር የእርዳታ ሠራተኞች በድሮን 300 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

የቶጎ መከላከያም በስህተት ሰባት ወጣቶችን ሐምሌ ላይ መግደሉን አምኗል።

በተለይም የጂሀዲስቶች ጥቃት ድንጋጤ በሚፈጥርበት ወቅት እንዲህ ያሉ ስህተቶች ይሠራሉ።

ቶጎ እና ኒጀር ከቱርክ ድሮን መግዛታቸው ፖለቲካዊ አንድምታም አለው።

ከቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ርቆ ወደሌሎች አገራት የመጠጋት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን “የድሮን ዲፕሎማሲ” ከሌሎች አገራት ጋር የሚደረግ የውጭ ግንኙነት አካል ነው።

በሰሀራ ቀጠና አውሮፕላን ማረፊያ መገንባትን ጨምሮ ሌሎችም ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋትንም ያካትታል።

የባይራክታር ቲቢ2 ድሮን አምራች ድርጅት መሪዎች ወንድማማቾቹ ሀሉክ ባይራክታር እና ሴሉክ ባይራክታር ናቸው።

ሴሉክ ዋና የቴክኖሎጂ ኃላፊ ሲሆን፣ ያገባውም የኤርዶዋንን ልጅ ሱምዬን ነው።