በአዲስ አበባ ንግድ ፈቃድ መስጠትን ጨምሮ 46 የመንግሥት አገልግሎቶች ለግል ተቋማት በውክልና ሊሰጡ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa

የምስሉ መግለጫ, የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ፈቃድ መስጠት፣ መመዝገብ እና ማደስን ጨምሮ 46 የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን በውክልና ለሦስተኛ ወገን ሰጥቶ ሊያሰራ ነው።

ትላንት ሰኞ ኅዳር 10/2016 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ የአስተዳደሩ ተቋማትን አገልግሎቶችን ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ የሚለው ይገኝበታል።

በካቢኔው ስብሰባ ላይ የተወሰኑ አገልግሎቶቻቸውን በውክልና ለግል ተቋማት እንዲያስተላልፉ ውሳኔ ላይ የተደረሰባቸው የከተማ አስተዳደሩ አምስት መሥሪያ ቤቶች እና ሆስፒታሎች መሆናቸውን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከእነዚህ የከተማ አስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የንግድ፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮዎች ይገኙበታል።

የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲሁም አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣንም አገልግሎቶቻቸውን በከፊል ለግሉ ዘርፍ ከሚያስተላልፉት ውስጥ ተካትተዋል።

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር የሚገኙት የካቲት 12 እና የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታሎችም የዚህ ዕቅድ አካል ናቸው።

የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊዋ እንደሚያስረዱት ተቋማቱ ለግሉ ዘርፍ እንዲያስተላልፏቸው የተመረጡት የመንግሥት አገልግሎቶች 46 ናቸው። ከእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ፣ ፈቃድ እና እድሳት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩን የግብይት ማዕከላት የማስተዳደር አገልግሎቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa City admin

የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን

የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ባለፈው ዓመት ባስጠናው ጥናት ላይ ለሦስተኛ ወገን ከሚተላለፉ አገልግሎቶች መካከል በትራንስፖርት ቢሮ የሚከናወነውን የሕዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት የአሽከርካሪዎች ቅጣት ክፍያን አካትቶ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በከተማ አስተዳደሩ ሆስፒታሎች የሚከናወኑት የኩላሊት ንቅለ ተከላ እና ሌሎች “ወረፋ ያላቸው” ሕክምናዎች በጥናቱ ላይ ተጠቅሰዋል። ይሁንና በካቢኔው ስብሰባ ላይ እነዚህ አገልግሎቶች ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

እንደ ወ/ሮ ሂክማ ገለጻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡ አገልግሎቶችን ለግል ተቋማት ለማስተላለፍ የወሰነው “የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ፍጥነት፣ ጥራት እና ውጤታማነት የተሻለ ለማድረግ” ሲባል ነው።

“ሕብረተሰቡ ከአገልግሎት ውጤታማነት፣ ከአገልግሎት ተደራሽነት ጋር የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን የአገልግሎት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አንዱ መፍትሄ አውትሶርስ አድርገን የግሉ ዘርፍ [እንዲሰራቸው ማድረግ ነው]። ይሄንን ሥራ የሚወስደው የግል ዘርፍ ለትርፍ የሚሰራ አካል ነው። ለትርፉ ሲል ሕብረተሰቡ ጋር የበለጠ ተደራሽ ይሆናል” ሲሉም የውሳኔውን ጥቅም አብራርተዋል።

በተጨማሪም “መንግሥት ሁሉም ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ላይሰራ ይችላል” የሚሉት ኃላፊዋ እነዚህ አገልግሎቶች ወደ ግል ተቋማት ሲተላለፉ “የመንግሥትን የመቆጣጠር እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓትን ተግባራዊ የማድረግ አቅምን” ጠንካራ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ሂክማ እንደሚገልጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡ አገልግሎቶች ከሚተላለፍላቸው አካላት መካከል የግል ባለሀብቶች ይገኙበታል። ባለሀብቶች አገልግሎቱን ተረክበው እንዲሰሩ የሚመረጡት በጨረታ መሆኑንም አስረድተዋል።

“[በተጨማሪም] ተደራጅተው የሚሰሩ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት፤ የተለያዩ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱም ሥራውን ወስደው መሥራት የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። ከዚያ ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ለሚሳተፉም ዕድል [አለ]” ሲሉም ሦስተኛ ወገንነት ተብለው የሚጠሩትን አካላት ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡትን አገልግሎቶች ለእነዚህ አካላት የሚያስተላልፍ ቢሆንም አገልግሎት አሰጣጡን እንደሚቆጣጠር የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።

“ለምሳሌ የንግድ ፈቃድ ስታንዳርዶችን የሚያወጣው መንግሥት ነው። የግሉ ዘርፍ ይህንን ስታንዳርድ አሟልቶ ለመጣ ሰው ፈቃዱን ይሰጣል። አውትሶርስ አድርገው አገልግሎቱን ለመስጠት የወሰዱ ተቋማት በስታንዳርዱ መሠረት ‘ሰሩ አልሰሩም’ የሚለውን ቁጥጥር የሚያደርገው እና ፈቃዶችን ቼክ የሚያደርገው መንግሥት ነው” ሲሉ ሊፈጠሩ የሚችሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የታቀደበትን መንገድ አስረድተዋል።