የቻይና አምራቾች ወደ አሜሪካ ገበያ ለመግባት ጎረቤት ሜክሲኮን ለምን መረጡ?

የቻይና አምራቾች ወደ አሜሪካ ገበያ ለመግባት ጎረቤት ሜክሲኮን ለምን መረጡ

በሞንቴሬይ የሚገኘው ማን ዋህ የቤት ዕቃዎች ፋብሪካ ወንበሮች እና የቆዳ ሶፋዎች ያመርታል። ያውም መቶ በመቶ “በሜክሲኮ የተሠሩ [ሜዲን ኢን ሜክሲኮ]” የሆኑ ዕቃዎች ናቸው።

እንደ ካስኮ እና ዎልማርት ላሉ ለትላልቅ ቸርቻሪዎች የተመረቱ ናቸው። ኩባንያው ግን የቻይና ነው። በቻይና ገንዘብ የተቋቋመ ፋብሪካ ነው።

በሜክሲኮ የንግድ ማኅበረሰብ ውስጥ ካሉት መነጋገሪያ ጉዳዮች አንዱ በአሜሪካ፣ በቻይና እና በሜክሲኮ መካከል ያለው የሦስትዮሽ ግንኙነት ነው።

ማን ዋህ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ ለማቅረብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰሜናዊ ሜክሲኮ ወደሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተዛወሩ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች አንዱ ነው።

በማጓጓዣ ወጪ ከመቆጠብ በተጨማሪ ምርቱም "በሜክሲኮ የተሠራ” ነው ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ምክንያት በቻይና እና በአሜሪካ መካከል በቀጠለው የንግድ ጦርነት ምክንያት በቻይና ምርቶች ላይ የተጣለው የአሜሪካ ታሪፍ እና ማዕቀብ ሜክሲኮ ያሉትን የቻይና ኩባንያዎች አያገኛቸውም።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዩ ኬን ዌይ ሰፊ ማምረቻ ቦታ በማሳየት ወደ ሜክሲኮ መዘዋወራቸው ከኢኮኖሚ ባሻገር የሎጅስቲክስ ትርጉምም ያለው ነው ይላል።

“እዚህ ምርታችንን በሦስት ወይም በአራት እጥፍ እንደምናሳድግ ተስፋ እናደርጋለን። በሜክሲኮ ያለው ፋብሪካ ዕቅድ በቬትናም ካለው ጋር እኩል እንዲሁን ማድርግ ነው” ብሏል።

ዋናው ሥራ አስኪያጅ ዩ ኬን ዊ
የምስሉ መግለጫ, ዋናው ሥራ አስኪያጅ ዩ ኬን ዊ በሜክሲኮ ያላቸውን ምርት በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አቅደዋል

በ2022 ሞንቴሬይ ከተማ የደረሰው ፋብሪካ በሜክሲኮ 450 ሰዎችን ቀጥሯል። ዩ ኬን ዌይ እንደሚለው ከሆነ በመጪዎቹ ዓመታት ፋብሪካውን በማስፋፋት ከአንድ ሺህ 200 በላይ ሠራተኞችን የመቀጠር ተስፋ እንዳላቸው ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“በሜክሲኮ ያሉ ሰዎች በጣም ታታሪ እና ፈጣን ተማሪዎች ናቸው። ጥሩ ሠራተኞች አሉን። የምርት መጠናቸውም ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ በሰው ጉልበት በኩልም ሜክሲኮ በጣም ጥሩ ነች ብዬ አስባለሁ” ብሏል።

ወደ አሜሪካ ጠጋ ብሎ መሥራት ለሜክሲኮ መዋዕለ ነዋይ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የሜክሲኮ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ከዓመት በፊት ከነበረበት 52.9 ቢሊዮን ዶላር በ5.8 በመቶ አድጓል።

ዕድገቱ የመቀነስ ምልክቶችን አላሳየም። በዚህ ዓመት ሁለት ወራት ውስጥ ተመዘገበው ካፒታል በ2020 ሙሉ ዓመት ከተመዘገበው ግማሽ ያህሉን ሆኗል።

ማን ዋህ የሶፋ ፋብሪካ በሆፉሳን በቻይና-ሜክሲኮ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይገኛል። የፓርኩ ተፈላጊነት ጣራ ነክቷል። አሁንም ምንም ክፍት ቦታ የለም።

የሜክሲኮ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማኅበር በበኩሉ እአአ 2027 በአገሪቱ ሊገነቡ የታቀዱ ፓርኮችም ከወዲሁ ተሽጠው አልቀዋል ብሏል።

የሜክሲኮ የወጭ ንግድ ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ሁዋን ካርሎስ ቤከር ፒኔዳ “ወደ ሜክሲኮ ገንዘባቸው እያመጡ ያሉት እዚሁ ለመቆየት ነው። በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት በቅርቡ እንደሚረግብ ምንም ፍንጭ የለም” ብለዋል።

ቤከር ፒኔዳ የአዲሱ የሰሜን አሜሪካ የነፃ ንግድ ስምምነት ዩኤስኤምሲኤ የሜክሲኮ ተደራዳሪ አባል ነበሩ።

“ወደ ሜክሲኮ የሚመጣው ካፒታል እና የቻይና አመጣጥ ለአንዳንድ አገራት ፖሊሲዎች የማይመች ሊሆን ይችላል። በዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ መሠረት እነዚህ ምርቶች የሜክሲኮ ናቸው” ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ሜክሲኮ በሁለቱ ልዕለ ኃያላን አገራት መካከል ግልጽ የሆነ ስልታዊ መሠረት እንዲኖራት አድርጓታል። በቅርቡ ሜክሲኮ ቻይናን በመብለጥ የአሜሪካ ዋና የንግድ አጋር መሆኗ ጉልህ እና ተምሳሌታዊ ለውጥ ነው።

ሠራተኞች

በሜክሲኮ በአሜሪካ መካከል የጨመረው የንግድ ልውውጥ ያደገው በቻይና ምክንያት ብቻ አይደለም። አሜሪካ ኩባንያዎችም ወደ እስያ ያዘዋወሯቸውን ፋብሪካዎቻቸውን በሜክሲኮ አቋቁመዋል።

ምናልባትም ትልቅ የሚባለው ዜና የተሰማው ከሞንቴሬይ ውጭ የሚቋቋመው አዲሱ ቴስላ ግዙፍ ፋብሪካ ዕቅድ ባለፈው ፈረንጆች ዓመት በኤሎን መስክ ይፋ በተደረገበት ወቅት ነው። የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ በ10 ቢሊዮን ዶላር የሚያቋቁመውን ፋብሪካ መገንባት እስካሁን አልጀመረም።

ቴስላ አሁንም ለፕሮጀክቱ ቁርጠኛ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና እያከናወነ የሚገኘው የሠራተኞች ቅነሳ ፕሮጀክቱን አቀዛቅዞታል።

የቻይና ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ግን አንዳንዶች ሜክሲኮ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ወዳለው ሰፊ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ እንዳትገባ ሲሉ ስጋታቸውን ያነሳሉ።

በሜክሲኮ በሚገኘው ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የቻይና-ሜክሲኮ ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ኤንሪኬ ዱሰል “በሜክሲኮ የሚገኘው ነባሩ ሐብታም አሜሪካ ከአዲሱ ሐብታም ቻይና ችግር ገጥሞታል። ሜክሲኮ በቀደሙት አስተዳደሮችም ሆነ በአሁነኛው መንግሥት ስለሦስቱ አገራት ግንኙነት ግልጽ ስትራቴጂ የለውም” ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ እና በሜክሲኮ ምርጫዎች በመቃረባቸው ምክንያት ወደፊት አዳዲስ ፖለቲካዊ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ዋይት ሐውስ የሚገቡት ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ ጆ ባይደን በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ይኖራል ብለው የሚጠብቁ ጥቂቶች ናቸው።

ዋሽንግተን ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ዋናው መሆኑን አስቀምጣለች። ሜክሲኮ በዚህ መሐል እንዳትያዝ መጠንቀቅ አለባት ሲል ዱሰል ይሞግታሉ።

ዱሰል አክለውም በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ “ሜክሲኮ ቻይናን 'እንኳን ወደ ሜክሲኮ ደህና መጣሽ' የሚል ትልቅ ምልክት እያሳየች ነው። በሁለቱ አገራት መካከል ላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ጥሩ እንደማይሆን ለማወቅ ምሑር መሆን አይጠበቅም” ብለዋል።

የቻይና አምራቾች የምርት ቦታቸውን በፍጥነት እያስፋፉ ነው
የምስሉ መግለጫ, የቻይና አምራቾች የምርት ቦታቸውን በፍጥነት እያስፋፉ ነው

ሌሎች ደግሞ ተስፋ ሰንቀዋል። “በእኔ አስተሳሰብ ጥያቄው መሆን ያለበት ይህ አካሄድ በዚሁ ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለው አይደለም። ከዚህ ምን ያህል ልንጠቀምበት እንችላለን የሚለው ነው” ይላሉ የቀድሞ የሜክሲኮ የንግድ ሥራ ኃላፊ ሁዋን ካርሎስ ቤከር ፒኔዳ።

“በኮሎምቢያ፣ በቬትናም እና በኮስታሪካም ተመሳሳይ ውይይቶችን እያደረጉ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ይህንን ለረዥም ጊዜ ለማስቀጠል በሜክሲኮ ውስጥ እነዚህ ሁኔታዎች በራሳቸው መንገድ ተጣጥመው ከድርጅት እና ከመንግሥት ውሳኔዎች ጋር አብረው እንደሚሄዱ ማረጋገጥ አለብን።”

ሞንቴሬይ በሚገኘው በማን ዋህ ፈርኒቸር ያሉ ባለሙያዎች የጀመሯቸው ሶፋ ወደ አሜሪካ ከመላካቸው በፊት የመጨረሻ ሥራዎችን እያጠናቀቁ ነው።

አንድ አሜሪካዊ በአቅራቢያው ከሚገኝ ዎልማርት ሶፋውን ሲገዛ ምርቱ ስላለፈበት ውስብስብ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳይ ብዙም ግንዛቤ ላይኖረው ይችላል።

ለአሜሪካ ገበያ መቅረብ በኃያላኑ መካከል በሚደረገው ጦርነት ምክንያት ጠቃሚ ወይንም ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ሜክሲኮ እየተጠቀመችበት ነው።