ከታይታኒክ መርከብ አደጋ የተረፉ ግለሰብ የጻፉት ደብዳቤ በ400 ሺህ ዶላር ተሸጠ

ኮሎኔል ግራሴ የጻፉት ደብዳቤ

የፎቶው ባለመብት, Henry Aldridge & Son Ltd

የምስሉ መግለጫ, ደብዳቤው ታይታኒክ መርከብ ከመስጠሟ ከአምስት ቀናት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ በሚያዝያ 10/1912 የተጻፈ ነው

ታይታኒክ መርከብ ከመስጠሟ ሁለት ቀን በፊት በአንድ ተሳፋሪ የተጻፈው ደብዳቤ በዩናይትድ ኪንግደም በተካሄደ ጨረታ ክብረ ወሰን በሰበረ ሁኔታ በ400 ሺህ ዶላር ተሸጠ።

እሑድ ዕለት በዊልትሻየር በተካሄደው ጨረታ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ገዥ የኮሎኔል አርክባልድ ግራሴን ደብዳቤ ይሸጣል ተብሎ ከታሰበው 80 ሺህ ዶላር በአምስት እጥፍ ዋጋ ገዝቶታል።

ደብዳቤው 'ትንቢታዊ' እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኮሎኔል ግራሴ ለሚያውቁት ሰው በጻፉት በዚህ ደብዳቤ ላይ መርከቧ ላይ ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር አስቀድሞ "የጉዞዬን መጨረሻ እጠብቃለሁ" ብለዋል።

ደብዳቤው እንደ አውሮፓውያኑ ሚያዝያ 10/ 1912 የተጻፈ ነው። ይህ ቀን ኮሎኔል ግራሴ ከሳውዝሃምፕተን ታይታኒክ ላይ የተሳፈሩበት ዕለት ሲሆን መርከቧ በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ከግግር በረዶ ጋር ተላትማ ከመስጠሟ ከአምስት ቀናት በፊት ማለት ነው።

ኮሎኔል ግራሴ ወደ ኒውዮርክ እያቀናች በነበረችው መርከብ ላይ ከተሳፈሩ 2 ሺህ 200 የመርከቧ ሠራተኞች እና መንገደኞች መካከል አንዱ ነበሩ።በአደጋው ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው አልፏል።

የመጀመሪያ ደረጃ [ ቢዝነስ ክላስ] ውስጥ የተሳፈሩት መንገደኛው ደብዳቤውን የጻፉት ከሲ51 ክፍል ነበር።

መርከቧ እንደ አውሮፓውያኑ ሚያዝያ 11/ 1912 በአየርላንድ ኪውንታውን በደረሰችበት ወቅት ደብዳቤው በፖስታ ቤት የተላከ ሲሆን በሚያዝያ 12 በለንደን ፖስታ አገልግሎት ማህተም ተደርጎበታል።

የደብዳቤው አጫራች እንዳሉት ደብዳቤው ከሌሎች በታይታኒክ ላይ ከተጻፉ ማስታወሻዎች ከፍተኛ ዋጋ ማግኘት ችሏል።

ኮሎኔል ግራሴ ስለመርከቧ መስጠም ምስክርነታቸውን ከሰጡት መካከል ይበልጥ ከሚታወቁት አንዱ ነበሩ።

ኮሎኔሉ በኋላ ላይ በመርከቧ ላይ ተሳፍረው በነበሩበት ወቅት የገጠማቸውን በማስታወስ 'ዘ ትሩዝ አባውት ዘ ታይታኒክ' የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል።

በመጽሐፋቸው ላይ በበረዷማው ውቅያኖስ በአንዲት ሕይወት አድን ጀልባ ላይ በመሳፈር እንዴት መትረፍ እንደቻሉ ተርከዋል።

በነፍስ አድን ጀልባ ላይ መሳፈር ከቻሉት ወንዶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በድካም ወይም በቅዝቃዜ መሞታቸውንም ኮሎኔሉ ጽፈዋል።

ኮሎኔል ግራሴ ምንም እንኳን ከአሰቃቂው አደጋ በሕይወት ቢተርፉም በዝቅተኛ የሰውነት ሙቀት [ሃይፖተርሚያ] እና በአካል ጉዳት ተሰቃይተዋል።

በአውሮፓውያኑ ታኅሳስ 2/1912 ራሳቸውን የሳቱ ሲሆን፣ ከስኳር ሕመም ጋር የተያያዘ ውስብስብ የጤና ችግር ካጋጠማቸው ከሁለት ቀናት በኋላ ሕይታቸው አልፏል።