"70 ዓመት በትዳር የመቆየታችን ምሥጢሩ ተራርቀን መኖራችን ነው"

ቶሚ ባጅ፣ ቴልማ ባጅ፣ ቫዮሌት ፍሌት እና ሌዝሊ ፍሌት በሰርጋቸው ቀን

የፎቶው ባለመብት, Flett family

የምስሉ መግለጫ, ቶሚ ባጅ፣ ቴልማ ባጅ፣ ቫዮሌት ፍሌት እና ሌዝሊ ፍሌት በሰርጋቸው ቀን

የዛሬ 70 ዓመት በስኮትላንዷ ኪርክዋል እጥር ምጥን ባለ ሰርግ ነው የተጋቡት።

ለእነሱ ሰርግ ተብሎ የተደለቀ አታሞ፣ ወይንም የተወዘወዘ ትከሻ አልነበረም።

ጥድፍ ባለ ሰርግ አራት ጥንዶች የቃል ኪዳን ቀለበታቸውን አስረው፣ በክፉ በደግ፣ በማግኘት በማጣት፣ በጤና በህመም አብረው ለመሆን ቃል ገቡ።

በአውሮፓውያኑ 1955 የተጋቡት ሁለቱ ጥንዶች ለ70 ዓመታት በትዳር ለመዝለቃቸው ምክንያቱ ለበርካታ ጊዜያት ተራርቀው መቆየታቸው መሆኑን በቀልድ ሸላልመው ያወሳሉ።

ቶሚ ባጅ እና ቴልማ ብሩስ ከቶሚ ታላቅ እህት ቫዮሌት ባጅ እና ሌዝሊ ፍሌት ጋር በኪርክዋል፣ ኦርክኒ በጋራ ኬክ ቆርሰዋል፤ አንድ የወሳኝ ኩነት ባልደረባ አፈራርሟቸዋል።

ለሰርጋቸው የተገኙት ሰዎች ብዛት እጅግ በጣም ትንሽ ነበር። ለእድምተኛው የተዘጋጀው ምግብ እና መጠጥም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

ግን ትዳራቸው ሰባት አስር ዓመታትን ተሻግሯል::

አራቱ የፕላቲኒየም የጋብቻ ክብረ በዓላቸውን ከልጆቻቸው፣ ከልጅ ልጆቻቸው እና ከልጅ ልጅ ልጆቻቸው ጋር በአንድነት በመሆን አክብረዋል።

ቀደም ሲል አብረው ስላሳለፉት ጊዜ ሲናገሩ ከስልክ ወይም ከዘመናዊ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ይልቅ፣ የሚለጠፉ አጫጭር ማስታወሻዎችን በመለዋወጥ እንደነበር በፈገግታ ይናገራሉ።

ተራርቀው የቆዩባቸው ጊዜያት ረዥም ጊዜ ለመቆየት ምክንያት እንደሆናቸው እየቀለዱ ያስታውሳሉ።

አዛውንቶቹ አሁን ዕድሜያቸው ከ87 እስከ 94 ባለው ክልል ውስጥ ነው።

ቴልማ አሁን 87 ሆኗቸዋል። ቶሚ 89፣ ቫዮሌት 91፣ ሌዝሊ ደግሞ 94 ዓመታቸው ነው።

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 9/1955 የተደረገው የጋራ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ቶሚ ለብሔራዊ አገልግሎት በመጠራቱ ምክንያት ነው።

ቫዮሌት እና ሌዝሊ ለጋብቻቸው አስቀድመው ቀን ቆርጠው ነበር።

ቶሚ ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፍበት ጊዜ ውስን በመሆኑ ሁሉም የጋብቻ ቀናቸውን ለማጣመር ወሰኑ።

ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በዚያን ጊዜ አፈራራሚ ሆኖ በከተማዋ ሆስፒታል፣ ባልፎር፣ ይሰራ በነበረ አንድ የቤተሰብ ወዳጅ ነው።

ቴልማ እና ቶሚ በጅ ጋብቻቸውን የፈጸሙት በ1955 (እአአ) ነበር

የፎቶው ባለመብት, Budge family

የምስሉ መግለጫ, ቴልማ እና ቶሚ በጅ ጋብቻቸውን የፈጸሙት በ1955 (እአአ) ነበር

ቴልማ ለቶሚ ኑሮ ለጉብኝት መጥቶ እንደመመለስ ነበር ይላሉ።

"አርብ ወደ ቤት መጣ፤ ቅዳሜ ተጋባን እና ሰኞ ላይ እንደገና ተመልሶ ሄዷል" በማለት ያስታውሳሉ።

ቫዮሌት በዕለቱ የነበረውን ድርብ ሰርጋቸውን በአንጻራዊ ቀላል ያለ እንደነበር ያስታውሳሉ።

"ሁለታችንም ተነስተን ተጋባን፤ ከዚያ ቦታ ቀይረን ቀጣዮቹ ሁለቱ ተጋቡ" ብለዋል።

"እኔ እና ሌዝ መሰለኝ መጀመሪያ ሄደን ጋብቻችንን የፈጸምነው።"

የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓቱ ተከናወነ በኋላ ፎቶግራፎች ተነሳን። ከዚያ በኋላ ሁሉም ወደ ሌዝሊ ወላጆች ቤት አመሩ።

ቫዮሌት ሻምፓኝ ለመጠጣት የሞከረችው ያኔ ነበር።

"ሻምፓኝን ለመጀመሪያም ለመጨረሻ ጊዜ የቀመስኩት ያኔ ነው ብዬ ተናግሬ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

"ኧረ እኔ አልወደድኩትም፤ የምመርጠው መጠጥ አልነበረም" ሲሉ ሳቁ።

ከዚያም 30 ለሚሆኑ የሰርጉ እድምተኞች ከዶሮ እና ከድንች የተዘጋጀ ምግብ በቫዮሌት እና በቶሚ ወላጆች ተሰናድቶ ቀረበ።

ሁለቱም ጥንዶች በሥራቸው ባህሪ የተነሳ ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ማሳለፍ ነበረባቸው።

ይህ ምናልባት ለረዥም ጊዜ በትዳር ለመቆየታቸው ምክንያት ይሆን እያሉ በመቀለድ ይሳሳቃሉ።

ቶሚ መርከቦች አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የተተከለ ማማን ለመጠበቅ ይጓዛል፤ ቫዮሌት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች በምሽት ፈረቃ ላይ ትሠራለች።

ቫዮሌት እና ሌዝሊ ፍሌት

የፎቶው ባለመብት, Flett family

የምስሉ መግለጫ, ቫዮሌት እና ሌዝሊ ፍሌት

ቫዮሌት "በምሽት ፈረቃ ነበር የምሠራው፤ ቀን ቀን ቤት ነበርኩ፤ እና ሁልጊዜ ማታ ማታ ቤት አልኖርም።

"እና የእኔ ባለቤት ቀን ቀን ይሠራ ነበር፣ እናም በየምሽቱ ቤት ነበር የሚገኘው። ያ ነው ምሥጢሩ - ላለመገናኘታችን።"

አክለውም "መልዕክቶችን በትንሹ በሚጣበቁ ወረቀቶች ላይ ጽፌ መስታወቱ ላይ እለጥፈዋለሁ። እርሱ አይቶ ካነበበ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ ይመልስልኝ። በዚህ መልክ ነው መልዕክት እየተለዋወጥን የኖርነው።"

ቴልማ መርከቦች አቅጣጫ እንዳይስቱ በተተከለው ማማ ላይ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ለሦስት ዓመታት በጦር ሠራዊቱ ውስጥ አገልግለዋል።

እርሳቸውም ከቶሚ ጋር መልዕከት የሚለዋወጡት በተመሳሳይ መልኩ እንደነበር ይናገራሉ።

ሌዝሊ፣ ቫዮሌት፣ ቴልማ እና ቶሚ የጋብቻ በዓላቸውን በጋራ ሲያከብሩ

የፎቶው ባለመብት, Evie McGowan

የምስሉ መግለጫ, ሌዝሊ፣ ቫዮሌት፣ ቴልማ እና ቶሚ የጋብቻ በዓላቸውን በጋራ ሲያከብሩ

"ከተጋባን 70 ዓመት ሞልቶናል፤ አብረን ያሳለፍነው ምናልባት 35 ዓመት ቢሆን ነው" ይላሉ በፈገግታ።

ቀጥለውም "በመጀመሪያ ለ18 ወራት አካባቢ ሥልጠና ላይ ስለነበረ አላየሁትም። ከዚያም ሁለት ወር ውጪ፣ ሁለት ሳምንት ደግሞ በቤቱ ያሳልፍ ነበር።

"በኋላ ላይ ነው ከወር ወር አንድ ላይ ማሳለፍ የጀመርነው።"

አራቱ ጥንዶች ኑሯቸውን የመሠረቱት በኦርክኔይ፣ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ነው።

60ኛ እና 65ኛ የጋብቻ በዓላቸውን ሲያከብሩ ከንግሥት ኤልዛቤት፣ ከንጉሥ ቻርልስ እና ንግሥት ካሚላ የመልካም ምኞት መግለጫ ያዘ የፖስት ካርድ ተልኮላቸዋል።

ቫዮሌት "የመጀመሪያው ካርድ ሲደርሰን፣ አምላኬ ሆይ፣ ከንግሥቲቱ ካርድ ተላከልን፤ የማይታመን ነው ነበር ያልኩት።

"ከዚያ በመቀጠል ከንግሥቲቱ ሌላ ካርድ ተላከ። እና ንጉሥ ቻርለስ ዙፋኑን ሲረከብ ብንገኝ ብለን አሰብን።

"በሌላ ቀን ፖስተኛው ሌላ መልዕክት ይዞ መጣ እና 'ኦህ እንዴት ውብ ነው' ብዬ አሰብኩ።"

በጠረጴዛው ዙሪያ የተሰበሰቡ ሰዎች ጽዋቸውን ሲያነሱ
የምስሉ መግለጫ, በጠረጴዛው ዙሪያ የተሰበሰቡ ሰዎች ጽዋቸውን ሲያነሱ

'እያንዳንዱን ቀን እንደ አመጣጡ ማስተናገድ'

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከ20 ዓመታት በፊት ሚያዝያ 9 ከተጋቡት ከንጉሡ እና ንግሥቲቱ ጋር የጋብቻ በዓላቸው የገጠመ ነው።

ቫዮሌት "ለዚህ ቀን መቼም መቼም እንደርሳለን ብዬ አላሰብኩም። እኔ እንደማስበው ማንም ከሚጠበቀው በላይ ነው። በተለይ አራታችንም እዚህ መገኘት እና መሳተፍ መቻላችን የማይታመን ነው።"

እና ቫዮሌት ለሌሎች ባለትዳሮች የሚሰጡት ምክር ምንድን ነው?

"እያንዳንዱን ቀን እንደአመጣጡ አስተናግዱት።"