ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ በህወሓት አመራር መካከል ያለው ፍጥጫ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል?
ባለፈው ሳምንት ህወሓት 14ኛ ጉባኤውን ውጥረት በተሞላ ሁኔታ በመቀለ ከተማ አካሂዷል።
በዚሁ ጉባኤ ላይም አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ ካድሬዎችን ከአመራርነት አንስቷል።
በተጨማሪም ዶክተር ደብረፂዮንን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ በድጋሚ የሾመ ሲሆን አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮሚሽኖች አባላትም መርጧል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ውሳኔን ወደ ጎን ብሎ የተካሄደውና ‘ሕጋዊነቱ’ ላይ ጥያቄ የተነሳበት ይህ ጉባኤ ከፍተኛ ሽኩቻን አስከትሏል።
የፓርቲ እና የሕዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ የጣለው ክፍፍሉ ገና የጦርነት ጠባሳው ያልሻረውን ክልልና በአጠቃላይ አካባቢውን ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይመልሰው በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ሁኔታው ለምን አሳሳቢ ሆነ?
በሰማዕታት ሃውልት ከተካሄደው ጉባኤ ጎን ለጎን በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን በክልሉ ምክር ቤት ጽ/ቤት የፓርቲውን ጉባኤ አካሄዷል።
በዚህ አንድ ቀን የፈጀ ጉባኤ ላይም ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። ከነጥቦቹ መካከል አንዱ በዋናነት የጸጥታ አካላት ከፖለቲካ ክፍፍሉ ራሳቸውን እንዲያገልሉ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚጠይቅ ነው።
በተለይ አፍሪካ ውስጥ ገዢ ፓርቲ የጸጥታ ኃይሎችን ተጠቅሞ የውስጥ እና የውጭ ተቃውሞዎችን እና ልዩነቶችን ማፈኑ የተለመደ ነው። የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች (ቲዲኤፍ) አንዱን ጥግ መያዝ የለባቸውም ካለ በኋላ ኃይሎቹ ከየትኛው ወገን እንደቆሙ ሲያነጋግር ሰንብቷል።
ህወሓት ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል ዝግ ስብሰባ በማካሄድ ከፍተኛ አመራሮችን ከስልጣን ለማንሳት ጥረት አድርጎ እንደነበር ይነገራል።
በወቅቱ ወደ ደም አፋሳሹ ጦርነት ያመራውን ምክንያትና ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመው የማዕከላዊ ኮሚቴው፣ ዶክተር ደብረፂዮንን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከወሰነ በኋላ በስብሰባው ላይ በታዛቢነት የተገኙት የጦር አዛዦች እንዳስቆሙት የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ።
ለቢቢሲ ትግርኛ ቃላቸውን የሰጡት የህወሓት አመራርና የጸጥታ አባል ነበር አቶ ብስራት “ከ8/9 ወራት በፊት አንዳንድ የጦር አዛዦች በህወሓት ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ገብተው ነበር። ማዕከላዊ ኮሚቴው ደብረፂዮንን ከሊቀመንበርነት አንስቶ ነበር። ፈትለወርቅንም ለማንሳት እየተዘጋጀ እያለ ሽምግልና በሚመስል መልኩ በኃይል እንዲቆዩ አድርጓል” ይላሉ።
"ይህ አደገኛ እና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል። የዚህ ዋናው ችግር የትግራይን ሕዝብ ደህንነትና ጸጥታ ለመጠበቅ የተመደበ አካል በጉዳዩ ላይ እጁን ሲያስገባ ስናይ ተበሳጭተናል አዝነናልም” ሲሉም ያክላሉ።
ይህ ወታደራዊ ኃይል በድርጊቱ እንደተጸጸተና አሁን አቅም እንደሌለው መረጃ አለኝ የሚሉት አቶ ብስራት ስጋቱ ግን እንደቀጠለ መሆኑን ያምናሉ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ ኃላፊ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የክልሉን ፀጥታ ለማስጠበቅ ሁሉም አካል “ቀይ መስመር’ እንዳይሻገሩ አስጠንቅቀዋል።
ይህም ‘የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ ገለልተኛ ሆነው ይቀጥላሉ’ የሚለውን አቋማቸውን የሚያጠናክር ነው።
"የጸጥታ ኃይል እንደመሆናችን አሁን ትልቁ ተግባራችን እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ሁኔታዎችን በኃይል ወይም በአስተዳደራዊ መንገድ እንዳይፈታ" መሆኑን ጀነራሉ አስምረዋል።
“አለመግባባቱ በሰለጠነ መንገድ ይፈታል ብለን እናምናለን።”
የትግራይን እና የፓርቲውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ሌላው የውጭ ምሁር ፕሮፌሰር ሼትላንድ ትሮንቮል የጸጥታ ኃይሎችን ከፖለቲካዊ ውዥንብር ለይቶ ማየት አይቻልም ይላሉ።
“አዎ፣ ጣልቃ የመግባት እድል አለ። የጄኔራል ታደሰ ወረደ መግለጫን ለማመን እና ለመቀበል ይከብደኛል። በትግራይ ያሉ የጸጥታ ኃይሎች ራሳቸውን የቻሉ አይደሉም። በፖለቲካ ስልጣን ስር ናቸው። በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የፖለቲካ ስልጣን ስር ነው የሚገኙት። የጸጥታ ኃላፊው ጄኔራል ታደሰ ራሳቸው ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፤ ይህ ማለት ወደ ከባድ ሁኔታ ሊመራ ይችላል" በማለት የህወሓት አመራርን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የከተተና ለመወሰን የሚያስቸግር እንደሆነ ያብራራሉ።
"ከጊዜያዊ አስተዳደር የሚመጡ ትዕዛዞችን እና ውሳኔዎችን ወደ መቀበል ወይም አለመቀበል ሊያመራ ይችላል። ይህ ማለት ከሁለቱ ወገኖች መካከል ለአንዱ ማድላት ማለት ነው። የፖለቲካ አመራሩ ካልተስማማ የጸጥታ አካላት ገለልተኛ ሆነው መቀጠል አይችሉም።”
የፕሪቶሪያ ስምምነት ለምን ጥያቄ ውስጥ ገባ?
የሁለቱም ወገኖች ሁሉም አመራሮች ማለት ይቻላል “የህወሓት መፍረስ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ባለቤትነት ያሳጣዋል” ይላሉ።
ሆኖም ‘የጋራ ጊዜያዊ መንግሥት ይቋቋም’ የሚለው ግልጽነት የጎደለው የስምምነቱ አንቀጽ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተሹመዋል። ይህም የሆነው ዶክተር ደብረጽዮን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቀባይነት ማጣታቸው ተከትሎ ነው።
በህወሓት ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባለው አካል በሂደቱ ደስተኛ እንዳልነበረ ይነገራል። የፓርቲው ፅህፈት ቤት በአቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ስምምነት አልቀበልም ሲል መግለጫ አውጥቷል።
በተጨማሪም ውሉን የፈረመው ህወሓት ‘ሕጋዊነት’ አለማግኘቱ የፓርቲው ዋና አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።
አቶ ጌታቸው ምርጫ ቦርድ የሰጠው 'አዲሱ የምዝገባ ውሳኔ' የማዕከላዊ ኮሚቴውን ውሳኔ የጣሰ የአራት ሰዎች ሴራ እንደሆነ እና ፓርቲውን ጥርስ ውስጥ እንደሚያስገባ ይከሳሉ።
አክለውም ጉዳዩ በመጀመሪያ በፕሪቶሪያ ውል እልባት አግኝቶ ወደ ፓናል አደራዳሪነት መመለስ ነበረበት በማለት ይከራከራሉ።
የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ለመመስረት ያቀደው ‘የሽግግር መንግሥት’ ግልጽነት የጎደለው ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ትሮንቮል ቢሆንም “በዋነኛነት በህወሓት የተመራ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል” ሲሉ ይገልጻሉ።
“የህወሓት ጉባኤ አቶ ጌታቸውን ከፓርቲ ኃላፊነታቸው አግዷል። አቶ ጌታቸውን በጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት አላውቃቸውም የሚል ሊያስከትል ይችላል። ይህ ሂደት ደግሞ መሬት ላይ ያለውን የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር ሊፈታተን ይችላል።”
ፕሮፌሰር ትሮንቮል እንደሚሉት፥ ዶክተር ደብረጽዮን ‘‘አቶ ጌታቸው ከእኛ የተመደበ ሰው አይደለም ማለት እንችላለን” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል። አመራሩን ከስልጣን ማንሳት ደግሞ ቀስ በቀስ ተግባራዊ እንደሚሆን ከወዲሁ አመልክተዋል።
“ይህ ግን በጣም አከራካሪ ጉዳይ ነው። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ኃላፊነት ያለው በአዲስ አበባ ያለው መንግሥት ነው። በይፋ የሾመው እሱ ነው። እናም የአስተዳደሩ ህጋዊ መዋቅር የሚቆጣጠረው የአውሮፓ ህብረት ፌዴሬሽን ነው። ስለዚህ ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ከፌዴራል መንግሥት ፍቃድ ውጪ በቀጥታ ከስልጣን ለማንሳት ምንም አይነት የሕግ መሰረት የለውም” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
በዚህ ምክንያት የስልጣን ጥያቄው አከራካሪ መሆኑንና በጊዜ ሂደት ማየቱ የተሻለ እንደሆነ ፕሮፌሰር ትሮንቮል ያምናሉ። “ጠብቀን ብናይ እመርጣለሁ።”
“ሆኖም ግን ምርጫው ሙሉ በሙሉ በፌዴራል መንግሥት እጅ ወድቋል።”
ህወሓትን እንደአዲስ መመዝገቡን ያሳወቀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ጉባኤው ቅደመ-ሁኔታዎችን አላሟላም በማለት እውቅና እንደማይሰጥ ስለገለጸ የፌደራል መንግሥት ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ መተንበይ አይቻልም።
የውጭ የጸጥታ ጣልቃገብነትን ሊያስከትል ይችላል?
ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር በተያያዘ ከአማራ ክልል ጋር በሚያስቡ አካባቢዎች፥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ እና ትጥቅ መፍታትን የመሳሰሉ ያልተፈቱ ጉዳዮች አሉ።
በዚህም ምክንያት ትግራይ ውስጥ እየታየ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ፥ በፕሪቶርያው ስምምነት ላይ አደጋ እንደሚኖረው ብዙዎች ያምናሉ።
የፌደራል መንግሥት ሁለቱም የህወሓት ወገኖች እርስ በራሳቸውን እስኪደክሙ ‘በጸጥታ ይመለከታል’ የሚሉም አሉ። ሌሎች ደግሞ እንደተለመደው ‘ሕጉን ለማስከበር’ ኃይል ሊጠቀም እንደሚችል ይገምታሉ።
"ወደ አውዳሚው ጦርነት መመለስ የሚፈልግ ያለ አይመስልም። ሆኖም የፖለቲካ ልዩነቶቹ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝበት እና በር የሚከፍትበት ሰፊ እድል አለ” ይላሉ ፕሮፌሰር ትሮንቮል።
በተለይም የዶክተር ደብረፂዮን ቡድን ‘በውጭ ኃይሎች በመተማመን’ ስልጣን በመሻት ላይ ነው የሚለው የአቶ ጌታቸው ረዳ ክስ ሁኔታውን ይበልጥ ያወሳሰበው ይመስላል።
ከዚህ ቀደም በህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት መካከል ሚስጥራዊ ግንኙነት እየተደረገ ነው የሚሉ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል። እስካሁን ከኤርትራ መንግሥት የተሰጠ መረጃ ግን የለም።
አቶ ብስራት አማረ ግን “አቶ ጌታቸው አስተማማኝ ማስረጃ ሳይኖረው አይቀርም፤ ከ [ፕሬዚዳንት] ኢሳያስ ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል፣ ጌታቸው አሰፋ የሚገኝበት የጸጥታ አባላት ከኤርትራ ኃይሎች ጋር ሲገናኙ ቆይተዋል” የሚል መረጃ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰር ትሮንቮል ግን በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን የውጭ ኃይሎችን ተጠቅሞ ወደ ስልጣን ለመመለስ እየጣረ ነው የሚለውን የአቶ ጌታቸው ረዳ ውንጀላ እንደማይቀበሉት ይናገራሉ።
“አንዳንዶች ህወሓት ከአሥመራ ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ብለው ያምናሉ። እኔ ግን የዚህን ክስ ትክክለኛነት እጠራጠራለሁ።”
የህወሓት ቃል አቀባይ ክሱን ማስተባበላቸው ይታወሳል። ሆኖም ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል።
በደብረጽዮን ቡድን የተካሄደው ጉባኤ የተወያየበት የፀጥታ ፖሊሲ ሰነድ፣ ከሱዳን እና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሻሻል በቀጠናው መረጋጋትና ሰላም መፍጠርን ያካተተ እንደሆነ እንደሚያውቁ ፕሮፌሰር ትሮንቮል ይናገራሉ። “ይህም ችግር ያለው መስሎ አይታየኝም።”
አቶ ብስራት ግን በዚህ አይስማሙም፤ “የውጭ ግንኙነት ማድረግ የሚችለው መንግሥት ብቻ ነው። ይህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወይም የፌዴራል መንግሥት ነው። አስፈላጊ ከሆነም የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሰረት በማድረግ እንጂ እንደዚህ በቡድን የሚደረግ አካሄድ ችግር ይኖረዋል" ይላሉ።
በአንፃሩ ደግሞ የደብረጽዮን ቡድን አቶ ጌታቸው ረዳ ቡድን 'ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተሰልፏል' እና 'ክዶናል' በማለት የሚከስ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ነባሩ የህወሓት አመራር ግዜያዊ አስተዳደሩን የያዘው አዲስ ትውልድ 'አሳልፎ ይሰጠናል’ የሚል ስጋት እንዳላቸው ተዛቢዎች ይገልጻሉ። አቶ ብስራት በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
'መከፋፈሉ የማይቀር ነበር'
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለ30 ዓመታት ያህል የተቆጣጠረው ህወሓት በ2018 ከዶክተር አብይ አህመድ መምጣት ጋር በተያያዘ ተጽእኖው በመቀሌ ላይ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር የነበረው ፍጥጫም በመጨረሻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወደ አለቀበት ደም አፋሳሽ ጦርነት አምርቷል። ግን አሁንም ከዚህ የተማረ አይመስልም ሲሉ ታዛቢዎች ይተቻሉ።
በባህሪው ኮሚኒስታዊ ፓርቲ የሆነው ህወሓት ተቃውሞ፣ አዳዲስ አመለካከቶችንና ልዩነቶችን የሚታገስ እንዳልሆነ የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ይናገራሉ።
የትግራይን ጦርነት ተከትሎ ውስጣዊ መበስበስ ተሸፍኖና ተዳፍኖ ቢቆይም መከፋፈሉ የማይቀር እንደነበር አቶ ብስራት ይገልጻሉ።
የአቶ ጌታቸው ቡድን ‘በሕግ እና በአስተሳሰብ የትውልዱ ወራሽ’ ነው ያሉት አቶ ብስራት ከፓርቲው ያረጀ አስተሳሰብን የሚገላግል፥ ነገሮችን በሰላምና በውይይት መፍታት የሚፈልግ ‘የለውጥ ተራማጅ ሃይል’ መሆኑን እንደሚያምኑ አክለው ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር ትሮንቮል በበኩላቸው በደብረጽዮም ገብረሚካኤል ወገን የተካሄደው ጉባኤ ተከትለው የሚመጡ 'አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት' ፓርቲውን እንደሚያድሱትና እንደሚለውጡት ያላቸውን እምነት ይጠቅሳሉ።