ህወሓት በድርጅታዊ ቀውስ ውስጥ፡ ከትላንት እስከ ዛሬ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በአመራሩ መካከል ውዝግብ የፈጠረውን 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ መቀለ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እያካሄደ ነው።

አዳራሹ የህወሓትን ስብሰባ አሊያም ጉባኤ ሲያካሂድ የመጀመሪያው አይደለም። ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ተካሂደውበታል። የአሁኑ ግን ለየት ይላል።

“የመዳን ጉባኤ” የሚል መሪ ቃል የተሰጠው ጉባኤ ሚካሄደው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለሁለት በተከፈሉበት ወቅት ነው። በዚህ ጉባኤ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸው ተገልጿል።

ይህ በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል እና መካሰስ ፓርቲው ወደ ሌላ ድርጅታዊ ቀውስ ውስጥ መግባቱን ማሳያ ነው።

ነገር ግን ህወሓት ቀውስ ውስጥ ሲገባ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከደደቢት በረሃ እስከ አራት ኪሎ በተዘረጋው የፓርቲው ታሪክ ህወሓት ተደጋጋሚ ድርጅታዊ ቀውሶች አጋጥመውታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ድርጅቱ ለተደጋጋሚ ቀውስ መጋለጥ “ከሚከተለው ፖለቲካ እና ርዕዮተ ዓለም የሚመነጭ ነው” ይላሉ።

ከእነዚህ ቀድሞ አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት፤ “ይኼ ጉዳይ የአስተዳደር ችግር ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም ድርጅቱ የተከተለው ግልጽነት የተጓደለበት ተጠያቂነት የሌለበት ፖለቲካ በግንኙነት ላይ የተመሠረተ መጠቃቀም ያለበት ነው” መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ ፖለቲካ “በወዳጅ እና ጠላት ፍረጃ” ላይ የተመሠረተ መሆኑን በማንሳት፤ ቀውሱ ከዚህ የሚነሳ መሆኑን አንስተዋል።

“ይህ የፖለቲካ አመለካከቱ እና አቅጣጫው ርዕዮተ ዓለሙ በአጠቃላይ ሥርዓቱን ካላሻሻለ በስተቀር [ፓርቲው] ይሻሻላል ብዬ አላምንም” የሚሉት አቶ ገብሩ፤ “[ህወሓት] በመሠረታዊ ተፈጥሮው እና የሚከተለው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ነው ለዚህ ሁሉ ቀውስ የዳረገው” ይላሉ።

ሌላኛዋ የህወሓት የቀድሞ አመራር ወይዘሮ አረጋሽ አዳነም በተመሳሳይ “ዋና ችግሩ የሚመስለኝ አስተሳሰቡ ነው፤ ርዕዮተ ዓለሙ ነው። ህወሓት ርዕዮተ ዓለሙ አስሮ የያዘው ድርጅት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ወይዘሮ አረጋሽ አክለውም፤ “[ህወሓት] ጠላት እና ወዳጅ ይለያል። ወዳጁን በተቻለ መጠን እያቀፈ አብሮት እያሰለፈ ይሄዳል ጠላቱን ደግሞ ጠላት ስለሆነ ይመታል የሚል አስተሳሰብ ነው የነበረው” ይላሉ።

ህወሓት ከዚህ በፊት ከአንዴም ሦስት ጊዜ ድርጅታዊ ቀውሶችን አይቷል።

የህወሓት የመጀመሪያው ድርጅታዊ ቀውስ፡ 1967

እርፍ እና ብዕር የጨበጡ እጆች ቃታ ለመሳብ ወደ በርሃ የወረዱት ገበሬዎች እና ተማሪዎች ጠላተ ብዙ ነበሩ። በተለይ በመጀመሪያዎቹ የትግል ዓመታት ከደርግ፣ ከኢዲዩ፣ ከጀብሃ እና ከኢህአሠ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ) ጋር ተከታታይ ውጊያዎችን አድርገዋል።

ከአስራ ሰባት የውጊያ ዓመታት በኋላ ህወሓት ከተጸነሰባት ፒያሳ ብዙም ሳይርቅ አራት ኪሎ ተገኘ። ከሌሎች ብሔርን መሠረት አድርገው ከተመሠረቱ ድርጅቶች ጋር ህወሓት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት አስተዳድሯል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ህወሓት የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የአገር ውስጥ ፖሊሲ በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የህወሓት የ17 ዓመታት ትግል ውጫዊ ብቻ አልነበረም። በመጀመሪያዎቹ የህወሓት የትግል ዓመታት ውስጥ ተከታታይ ድርጅታዊ ቀውሶች አጋጥመውታል።

ዶ/ር ሙሉጌታ ገብረሕይወት “Laying the past to rest” በተሰኘ መጽሐፋቸው የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ቀውስ “የደደቢት ቀውስ” ሲሉ ይጠሩታል።

ይህ ቀውስ ዋና መነሻው ትግሉን የተቀላቀሉት ገበሬዎች ከመሐል አገር ወደ በርሃ በወረዱት የተማሪ ታጋዮች መካከል የተከሰተ ቅራኔ ነው።

ከህወሓት መሥራቾች አንዱ የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ማሟያ በጻፉት ጥናት፤ “ገበሬዎቹ ከተማሪዎቹ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ወቅት ተማሪዎቹ ለትጥቅ ትግል ብቁ ያልሆኑ በወረቀት ብቻ መጫወት የሚችሉ የትጥቅ ትግልን መሸከም የሚችል ጫንቃ የሌላቸው አድርገው ይመለከቷቸዋል” ይላሉ።

እነዚህ ገበሬዎች ትግሉን የተቃለቀሉት ከህወሓት መሥራቾች አንዱ በሆኑት ስሁል (ገሰሰው) አየለ ላይ ባለቸው እምነት መሆኑን ደግሞ ዶ/ር ሙሉጌታ በመጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ስሁል አየለ ከህወሓት በፊት የተቋቋመውን የብሔረ ትግራይ ተራማጆች ድርጅት ከመሠረቱን መካከል አንዱ መሆናቸውን ዶ/ር አረጋዊ በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ህወሓት ከተመሠረተ በኋላ ድርጅቱን ለአንድ ዓመት ያህል መርተውታል።

እንደ ዶ/ር ሙሉጌታ ገለጻ ለገበሬዎቹ ታጋዮች “ከእሱ በላይ የሆነ መሪ አልነበረም”። በዚህም የመጀመሪያው ድርጅታዊ ቀውስ የተከሰተው በእነዚህ ገበሬዎች መካከል “በተፈጠረው ውዠንብር ነው” ይላሉ።

የስሁል አየለ አመራር አደጋ እንደተጋረጠበት የተሰማቸው ገበሬዎቹ ይህ ወደፊት እነሱ በድርጅቱ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና አደጋ ላይ እንደጣለው ተሰምቷቸው ነበር።

እንዚህ ገበሬዎች የስሁል አየለ መሪነትን ለማዳከም ሞክረዋል የሚሏቸው አመራሮች ላይ ጥቃት ለማድረስ ማሴራቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ በመጽሃፋቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ህወሓት የጦር ሰፈሩን ከደደቢት ወደ መሐል ትግራይ ለማዘዋወር ሲያቀድ “ከእዚያ [ከደደቢት] አካባቢ የመጡ ገበሬዎች ተቃውመውታል” ይላሉ።

እነዚህ ገበሬዎች ውሳኔውን የተቃወሙት “የሚያውቁትን አካባቢ ለቅቀው ከወጡ ሚናቸው እና በዚህም የሚኖራቸው ተጽዕኖ ይቀንሳል ብለው ስለሰጉ” መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ ይገልጻሉ።

ዶ/ር አረጋዊ ከዚህ ውሳኔ በኋላ እነዚህ ገበሬዎች “የምሥጢር ሥራ ላይ ተጠመዱ” ሲሉ ያክላሉ።

የገበሬዎቹ ዕቅድ ከኮሌጅ ወደ በርሃ የወረዱት ተማሪ የድርጅቱን አመራሮች መግደል እንደነበር ዶ/ር አረጋዊ እና ዶ/ር ሙሉጌታ በጥናቶቻቸው ላይ አስፍረዋል።

ነገር ግን ገበሬዎቹ ዕቅዳቸው አልሰመረም። ያሰቡትን ወደ መሬት ከማውረዳቸው በፊት ትልማቸው ከሸፈ።

ከዚህ ክስተት በኋላ በትግል ሜዳው ስጋት አረበበ። እንደ ዶ/ር አረጋዊ ገለጻ ወትሮም እንቅልፍ የማይጠጋቸው ታጋዮች ዐይናቸው ፈጦ አደረ። አሃ... ከግድያ ሙከራ በኋላ ማን ማንን ያምናል?

“ለጠላት” የተቀባበሉ ቃታዎች ለጓድ ቢሳቡስ?

በማግስቱ ይህን የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ቀውስ ለመፍታት ህወሓት አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ። ታጋዮች ሂስ እና ግለ ሂስ አወረዱ።

ዶ/ር አረጋዊ “በቀኑ መገባደጃ ላይ ሁሉም የገበሬ ተዋጊዎች ሁለተኛ ዕድል እንዲሰጣቸው ተወሰነ” ሲሉ ያስታውሳሉ። ዶ/ር አረጋዊ ይህን ቢሉም ዶ/ር ሙሉጌታ ግን በድርጅቱ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉት “ከልባቸው ግለ ሂስ ያወረዱት” መሆናቸውን በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።

የችግሩ ዋና ፈጣሪዎች ግን ከድርጅቱ ገሸሽ” መደረጋቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ አክለዋል።

ዶ/ር አረጋዊ በበኩላቸው “ጠንካራ አብዮታዊ ዲሲፕሊን መቋቋም ያልቻሉ ጥቂቶች ግን የግንባሩን ንብረት ሁሉ ትተው ድርጅቱን መልቀቃቻውን” ይገለጻሉ።

“አውነተኛ ግለ ሂስ” ያወረዱ ታጋዮች በበኩላቸው ልባቸው ከፈቀደ በትግሉ ውስጥ እንዲቆዩ ካልሆነም ደግሞ ትግሉን እንዲተዉ ከድርጅቱ ይሁንታ እንዳገኙ ሁለቱ ጸሃፊዎች በጥናቶቻቸው ጽፈዋል።

የቀድሞው የህወሓት አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በ1967 ዓ.ም. ክረምት መግቢያ የተከሰተው ይህ ድርጅታዊ ቀውስ “አውራጃዊነት ተብሎ ተሰይሟል” ይላሉ።

ሁለተኛው “ሕንፍሽፍሽ”፡ 1969

1969 ዓ.ም. ህወሓት እጅግ የተፈተነበት ዓመት እንደነበር የፓርቲውን ታሪክ የጻፉ ግለሰቦች ያሰነሳሉ። አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው 1969 ዓ.ም. ለህወሓት “ፈታኝ ዓመት ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር ሙሉጌታ በበኩላቸው “ከኢዲዩ ጋር ለአስር ወራት በዘለቀው ግጭት ምክንያት በደረሰው ሞት እና ችግር ተባብሶ የነበረው ቀውስ ህወሓትን ወደ ውድቀት አፋፍ ወሰደው” ሲሉ አስፍረዋል።

ከኢዲዩ ጋር በነበረው ውጊያ ህወሓት “በርካታ የጦር መሪዎቹን እና ጠንካራ ታጋዮቹን” ማጣቱን የሚገልጹት አቶ ገብሩ፤ ከኢዲዩ በተጨማሪ ድርጅቱ ከኢህአፓ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ግበቶ ነበር። ኤርትራ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ከሻቢያ እና ከጀብሃ ጋርም ዐይን እና ናጫ መሆንም ጀምሮ ነበር።

ህወሓት ከኢዲዩ ጋር ባደረጋቸው ውጊያዎች የደረሰበት ውድመት እና ጉዳት በምዕራብ ትግራይ ይቆጣጠራቸው የነበሩ ቦታዎችን እንዲያጣ አድርጎታል። አንዳንድ ተዋጊዎች የአመራሩ ጦርነቱን የመምራት አቅም ላይ ጥያቄ ማንሳት መጀመራቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ ይገልረጻሉ። ከዚህ አልፎም፤ “በአመራሩ ችሎታ ላይ ቅሬታዎች እየጨመሩ መጡ” ሲሉ ያክላሉ።

ህወሓት ከጦርነቱ የሚደርስበት ተከታታይ ጫና እና በድብቅ የሚካሄዱት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተደማምረው ሞራላዊ ውድቀትን ማስከተላቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ ይገልጻሉ።

ይህ በበኩሉ “ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተዋጊዎች ድርጅቱን እንዲከዱ በመድርግ ህወሓትን ወደ ውድቀት አፋፍ አድርሶት ነበር” ይላሉ።

“ከኢዲዩ ጋር የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረው የውስጥ ቀውስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላቶቹ ድርጅቱን ለቀው እንደወጡ” ዶ/ር ሙሉጌታ በመጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ “ኃላፊነት አሰጣጥን፣ የፖሊሲዎች አወጣጥን እና መረጃ ማግኘትን በተመለከተ ብዙዎች ቅሬታ ነበራቸው” ይላሉ።

ይህ ድርጅታዊ ቀውስ በተባባሳበት ወቅት የህወሓት አመራር ቀውሱን ለመፍታት ስብሰባ ጠራ። ይህ ስብሰባ የተካሄደው የድርጅቱ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በነበረው ባድመ አካባቢ በሚገኘው ቡምበነት በተባለው አካባቢ ነበር።

በዚህ ስብሰባ ላይ በተዋጊዎች ቀረቡት ቅሬታዎች በድርጅቱ ውስጥ ከፋፋይነት፣ የአመራር ፈላጭ ቆራጭ አሰራር፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ባህል፣ የህወሓትን ሕግ እና ሥርዓት በመተግበር ረገድ የአመራሩ ክልላዊ አድሎአዊነት አለ የሚሉ ነበሩ።

ህወሓት ከዚህ ድርጅታዊ ቀውስ ለመውጣት ችግሮችን በመመርመር መፍትሔ ለማግኘት ወታደራዊ ሸንጎ መጥራቱን አቶ ገብሩ አስራት ያስታውሳሉ።

ከዚህ ወታደራዊ ሸንጎ በኋላ ድርጅታዊ ቀውሱን የተመለከተ ምርመራ መደረጉን ዶ/ር አረጋዊ ይገልጻሉ።

ህወሓት ይህን ድርጅታዊ ቀውስ የፈታበት መንገድ በድርጅቱ መሪዎች እና አባላት መካከል ያለውን ግንኙነት እንደቀየረው የሚጠቅሱት ዶ/ር ሙሉጌታ “የድርጅቱ አመራሮች ተገዳዳሪ የሌለው የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን ያሳየ ነው” ሲሉ ያክላሉ።

እንደ ዶ/ር ሙሉጌታ ገለጻ፤ ቀውሱ የተፈታበት መንገድ “የአመራሮችን የተጠያቂነት ጉዳይን ማንሳት ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል እና በትግሉ መቀጠል ለሚፈልግ ሰው የማይሄድበት ቦታ መሆኑን ለአባላቱ ጠቁሟል” ይላሉ።

ህወሓት ከተመሠረተ ከአስር ዓመታት በኋላም እንዲሁ የውስጥ መከፋፈል ገጥሞት ነበር። በማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ምሥረታ ወቅት የአመራር ሹም ሽር ተደርጓል።

በዚህ ጊዜ ከድርጅቱ አመራርነት የተሰናበቱት አረጋዊ በርሄ እና ግደይ ዘርዓጽዮን ናቸው።

ዶ/ር አረጋዊ ከድርጅቱ የተባረሩት፤ “በርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች ላይ ፖሊት ቢሮውን ሲሞግቱ የነበሩት” ግደይ ዘርዓጽዮን እና እርሳቸው ከፖሊት ቢሮ አባልነታቸው መነሳታቸውን ጽፈዋል።

አቶ ገብሩ አስራት ይህ ቀውስ “እስከዚህም ከባድ አልነበረም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አቶ ገብሩ አክለውም “ውይይቱ በርዕዮተ ዓለም ዙሪያ ነው የተካሄደው በአንዳንድ መሠረታዊ የሥልጣን ጥያቄዎች ነው ልዩነቱ የተነሳው” ይላሉ።

የ1993ቱ ድርጅታዊ ቀውስ

ህወሓት ከበርሃ ወደ አራት ኪሎ ሲገባ፣ ከአማጺነት ወደ መንግሥትነት ሲሸጋገርም ድርጅታዊ ቀውሱ አልተወውም።

ከሌሎች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ጋር ሆኖ አገር ማስተዳደር በጀመረ በ12ኛው ዓመት ህወሓት ሌላ ድርጅታዊ ቀውስ ገጠመው።

ዶ/ር መድኃኔ ታደሰ እና ጆን ያንግ ከ21 ዓመት “TPLF: Reform or Decline?” በሚል ርዕስ በጻፉት መጣጥፍ፤ “ለህወሓት ቀውስ ምክንያት ሆነው ዘር የተዘራው ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት ነው” ይላሉ።

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እስኪጀመር ድረስ በህወሓት አመራሮች መካከል በአደባባይ የሚታይ ልዩነት አልነበረም።

አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው ከጦርነቱ መጀመር በኋላ “የኢትዮጵያ ሠራዊት የመጨረሻ መዳረሻ አሥመራ መሆን እንዳለበት በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስምምነት ላይ ተደረሰ” ይላሉ።

ይህ አሥመራ ድረስ ዘልቆ የመግባት ውሳኔ ኋላ በህወሓት አመራሮች መካከል ለተከሰተው ልዩነት ዋና ምክንያት ሆኗል።

አቶ ገብሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ውሳኔ ላይ “ብርቱ ክርክር” ማድረጉንም ያነሳሉ። የክርክሩ መነሻ “ሻዕቢያን ለመምታት አሥመራ ድረስ ዘልቆ መግባት አገርን መውረር ስለሚሆን ተገቢ አይደለም” የሚል መሆኑንም ያስረዳሉ።

ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የጦርነቱ ዓላማ የኤርትራን ጦር መደምሰስ” እንጂ ኤርትራን መልሶ መያዝ አለመሆኑን” በማንሳት ተከራክረዋል።

የጦርነቱ ሰሞን የተጀመረው ይህ ልዩነት እየሰፋ ሂዶ ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ ገሃድ ወጣ።

በዚህ ጊዜ “ከኤርትራ ጋር የነበረው ጦርነት እንዴት ተቋጨ? ለምን እንደዚያ ሆነ? ለምን ተወረርን? ከተወረርንስ በኋላ አጸፋው እንደዚያ መሆን ነበረበት ወይ? ጦርነቱ ለምን ቆመ? የጦርነቱ ዓላማ ተሳክቷል ወይ? የመከላከል ዓላማችን ተሳክቷል ወይ?” በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ልዩነቶች መፈጠራቸውን አቶ ገብሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ገብሩ አክለውም፤ “አመራሩን የሚያስጠይቅ ጉዳይ እያለ [አመራሩ] ይኼን ትቶ [ከጦርነቱ ጋር] ምንም የማይያያዝ የቦናፓርቲዝም ጉዳይን ነው ያነሳው። ዋናው የጦርነቱ መነሻ እና ውጤት እያለ ሌላ አጀንዳ ነው የተተከለው። በዚያም ከፍተኛ ቁጣ ያላቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመቱ” ይላሉ።

በቦናፓርቲዝም ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት የያኔው የህወሓት እና ኢህአዴግ ሊቀመንበር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው። መለሰ በዚህ ጽሁፋቸው የህወሓትን አመራር “በመበስበስ እና ከመሰረቱ በመራቅ” ከስሰዋል።

ይህ አቶ መለስ ዜናዊ በጽሑፋቸው ያቀረቡት ሃሳብ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ 15 ለ 13 በሆነ አብላጫ ድምጽ ጸደቀ።

ከዚያም ተቃውመው ድምጽ የሰጡ አባላት የማዕከላዊ ኮሚቴ ወጥተው በህወሓት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አለመግባባቱን ለመፍታት ብሔራዊ ጉባኤ እንዲጠራ እና በህወሓት አመራር የተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጠየቁ።

ይህ ውሳኔ ግን የ“አፈንጋጮቹ” እና የህወሓት ግንኙነት መጨረሻ ነበር። ይህ ድርጅታዊ ቀውስ አንጋፋ የነበሩት ድርጅቱን አመራሮች አቶ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራ፣ አረጋሽ አዳነ እና ተወልደ ወልደማሪያም ጨምሮ ሌሎችንም ከፓርቲው እና ከመንግሥታዊ ኃላፊነት እንዲባረሩ አድርጓል።

“በ50 ዓመት ታሪክ ከባዱ ፈተና”፡ 2016

ህወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ “ከባዱ ፈተና” እንዳጋጠመው ባለፈው ሐምሌ ወር አስታውቋል። ህወሓት ይህን ባስታወቀበት ወቅት የችግሩ ዋነኛ ምንጭ በካድሬዎች፣ በሰፊው ሕዝብ እና በተለያዩ የፓርቲው አመራሮች መካከል ያለው “ቡድንተኝነት፣ አካባቢያዊነት፣ ፀረ-ዴሞክራሲ፣ ህዝባዊነት እና ሙስና ነው” ብሏል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል እና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በሁለት የተለያዩ ጎራዎች ቆመዋል።

አቶ ጌታቸው ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ከድምጺ ወያነ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፤ አሁን ያለው የድርጅቱ መሠረታዊ ችግር ሥልጣን እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም “ሁሉም የነበረውን ለማስቀጠል፣ በሥልጣን ላይ እያሉ በተፈጸሙ ስህተቶች ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየተሯሯጡ ነው” በማለት ‘ያጡትን ሥልጣን ለማስመለስ፣ ሥልጣን ቀምቶኛል የሚሉትን ደግሞ ለማስወገድ’ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ወቅት ራሳቸውን ያገለሉበት እና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ መካሄድ የጀመረው የህወሓት 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ፤ በአመራሩ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚታረሙበት መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው ነበር።

አቶ ጌታቸው አክለውም ህወሓት “ጊዜው የሚጠይቀውን ሃሳብ ማመንጨት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው” ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።

ከአቶ ጌታቸው በተቃራኒ የቆመውን የህወሓት ቡድን የሚመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን በበኩላቸው የፓርቲውን አመራሮች ለሁለት በከፈለው 14ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ፤ “በውስጣችን የተፈለፈለ የጥፋት አንጃ/ቡድን የሚያካሄደው እንቅስቃሴ የፓርቲውን ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ እንዳሸጋገረው” ተናግረዋል።

ለዚህም ችግር “ጉባኤ ማካሄድ ብቸኛ መፍትሔ ነው” ሲሉ አክለዋል።

አቶ ገብሩ ግን ዶ/ር ደብረጽዮን እና ከእሳቸው ጋር በአንድ ጎራ የቆሙት አመራሮች፤ ጉባኤ አካሂደው የተወሰኑ አመራሮችን ከሥልጣን የማንሳት ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

አቶ ጌታቸው ረዳም ጉባኤው በተጀመረበት ቀን ባወጡት መግለጫ የጋራ መግባባት ሳይደረስ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ይህን ጉባኤ ለማካሄድ የተነሱት “ይቃወሙናል የሚሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ በማለም ነው” ብለዋል።

“አሁን የተገባበት ክፍፍል እና ውጥረት በጣም ሰፊ እና ጥልቀት ያለው እንዲሁም ከባድ ነው” የሚሉት ወይዘሮ አረጋሽ ይህ ድርጅታዊ ቀውስ “ከዚህ በፊት ከነበሩት የተለየ” መሆኑን ያነሳሉ።

“ይህ ውጥረት አሁን የተፈጠረው ችግር ከበፊቶቹ አንጻር ሲታይ በጣም የተለየ ይመስለኛል። ያኔ ህወሓት በአጠቃላይ ሲታይ ጠንካራ አቋም ውስጥ ሆኖ ሲንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው” ይላሉ።

ህወሓት ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ቀውሶች “ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፈትቷል ባይባልም [ችግሮቹ] በተፈቱባቸው መንገድ ተፈትተው የድርጅቱን ህልውና ግን ለመቀጠል ችሏል” ሲሉ ወይዘሮ አረጋሽ ያስታውሳሉ።

ከ1993ቱ ድርጅታዊ ቀውስ በኋላ፤ “አመራሩ በጣም እየተዳከመ መጥቷል” በማለትም፣ ከድርጅቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተጨማሪ ለሁለት ዓመት የቆየው የትግራይ ጦርነት የአሁኑን ቀውስ የተለየ እንደሚያደርገው ወይዘሮ አረጋሽ ገልጸዋል።

ህወሓት በተለየ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው አውድ ውስጥ የገጠመውን ይህን ቀውስ ለመፍታት እየሞከረ ያለው በቀደመው ዘዴ መሆኑን አቶ ገብሩ እና ወይዘሮ አረጋሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የተፈጠረውን ችግር በተለመደው መንገድ ነው ለመፍታት እየተሞከረ ያለው” የሚሉት ወይዘሮ አረጋሽ፤ ፓርቲው አሁንም “በስብሰናል፣ ጥገኝነት አለ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው ችግራችን የሚባሉ የማይተነተኑ ሃሳቦች እየደረደረ ነው” ይላሉ።

ይህ የወይዘሮ አረጋሽ ሃሳብ ባለፈው ሐምሌ አጋማሽ በወጣው የህወሓት መግለጫ ላይ ተንጸባርቋል። በመግለጫው የችግሩ ዋነኛ ምንጭ በካድሬዎች፣ በሰፊው ሕዝብ እና በተለያዩ የፓርቲው አመራሮች መካከል ያለው “ቡድንተኝነት፣ አካባቢያዊነት፣ ፀረ-ዴሞክራሲ፣ ሕዝባዊነት እና ሙስና ነው” ብሎ ነበር።

ህወሓት በ1967 ያጋጠመውን የደደቢት ቀውስ “አውራጃዊነት” ተብሎ መሰየሙን በቀውሱ የተሳተፉ ግለሰቦችም፤ “አውራጃዊነት የተጠናወታቸው የሥልጣን ጥመኞች” ተብለው መፈረጃቸውን ልብ ይሏል።

አሁኑ የህወሓት ድርጅታዊ ቀውስ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ቀውሶችን በተፈተቡት መንገድ ሊፈታ እንደሚችል የቀድሞ አመራሮች ይናገራሉ።

አቶ ገብሩ “የሥልጣን ሽግሽግ እንደሚኖር፤ አንዱ ቡድን ተመትቶ ሌላው ተጠናክሮ እንደሚወጣ አያጠራጥርም” ይላሉ።

ወይዘሮ አረጋሽ በበኩላቸው “በጉባኤው አመራሮች ሊቀያየሩ ይችላሉ። አንዱ ወርዶ አንዱ ሊመጣ ይችላል፤ ከዚያ በኋላ ግን ለትግራይ ሕዝብ እና አሁን ላለው ችግር መፍትሔ ይዞ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም። ክፍፍሉ እንደቀጠለ ቀውሱ እንደገና ጥልቀት ያለው ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።