ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በህወሓት ውስጥ መከፋፈልን የፈጠረው ጉባኤ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በዝግ እየተካሄደ የሚገኘው የህወሓት 14ኛ ጉባኤው ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ ሦስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፣ አነጋገሪነቱም ቀጥሏል።
ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከ17 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የሌሎች በርካታ የትግራይ አካባቢዎች ተወካዮች ከጉባኤው ራሳቸውን አግልለዋል።
ነገር ግን በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የፓርቲው አባላት የአዘጋጅ ኮሚቴውን ሪፖርት አዳምጠው ወደ ቀጣይ አጀንዳ ለመሄድ እየተሰናዱ እንደሚገኙ ህወሓት ረቡዕ ዕለት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
ለመሆኑ ህወሓት ይህንን ከከፍተኛ አመራሮቹ እና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ያላገኘውን ጠቅላላ ጉባኤን በችኮላ ለማካሄድ የተጣደፈው ለምንድን ነው? ቢቢሲ ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የሆኑ ነጥቦችን ከፓርቲው ውስጥ አዋቂዎች ጠይቆ መረጃ አግኝቷል።
ሕጋዊ እውቅና የሌለው ጉባኤ
በህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን እና በምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው ይህ ጉባኤ በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ነው።
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ያጣውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ ከአንድ ዓመት በላይ ከምርጫ ቦርድ እና ከፌደራል መንግሥት ጋር ሲነታረክ የቆየው ህወሓት፣ ባለፈው ሳምነት ‘በልዩ ሁኔታ እንደ አዲስ ፓርቲ መመዝገቡን’ ሳይቀበል ነው ወደ ጉባኤው ያመራው።
የህወሓትን “የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት የሚመልስበት ሕጋዊ መንገድ የለም” በማለት የሚከራከረው ምርጫ ቦርድ፣ የአሁኑን ጉባኤም ሆነ በመድረኩ የሚወሰነውን ውሳኔ ሕጋዊ ነው ብሎ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
ሆኖም ህወሓት ከውስጥም ሆነ ከውጭም የሚነሱትን ተቃዋሞዎች ችላ በማለት አጨቃጫቂውን ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ ወስኗል።
ሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው ህወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚ እንደመሆኑ የህወሓትን ሕጋዊነት መካድ ማለት ስምምነቱን መጣስ ማለት ነው፤ ይሄም የትግራይን ሕዝብ “ለበላተኛ አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል” ማለታቸው ተሰምቷል።
እሳቸው እንደሚሉት በፓርቲው ውስጥ ያለውን “መበስበስ ለመዋጋት እና ፓርቲውን ለማዳን” ጉባኤውን አሁኑኑ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው።
የሥልጣን ሽኩቻ
የህወሓት የገጠመው ፈተና ሕጋዊነቱን በተመለከተ ከውጭ እያጋጠመው ያለው ብቻ ሳይሆን፣ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እና መከፋፈል ሳያስተካክል ነው ወደ 14ኛ ጉባኤውን በጥድፊያ ያመራው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በህወሓት ጽሕፈት ቤት መካከል ያለው ሽኩቻ እየተባባሰ በመሄዱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረው አንጋፋ ፓርቲ “ሊፈርስ ተቃርቧል” የሚሉም አሉ።
የዚህ ሁሉ መነሻው ምን እንደሆነ ለአመራሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት በሁለቱ ወገኖች መካከል ልዩነት የፈጠረ አንዳችም “የሕዝብ አጀንዳ” የለም ብለዋል።
ልዩነቱ በዋናነት በድርጅቱ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዓለም ገብረዋህድ እና በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ እንደሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ውስጥ አዋቂ ያስረዳሉ።
አክለውም ፍጥጫው ባለፈው ዓመት አቶ ጌታቸው ረዳን በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት መሾማቸውን በተመለከተ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከፕሪቶርያው ስምምነት መፈረም ጀምሮ እየተንከባለለ የመጣ እንደሆን ይናገራሉ።
በጠባብ ልዩነት በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ በይፋ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳን በህወሓት ጽህፈት ቤት “የጠላቶቻችን አስፈጻሚ ነው፣ ተላላኪ ነው፣ ክዶናል፣ አሳልፎ ሰጥቶናል. . . ወዘተ የመሳሰሉት የስም ማጥፋት ዘመቻ” እንደተካሄደባቸው ውስጥ አዋቂው ይናገራሉ።
አቶ ጌታቸው ረዳ ራሳቸውም ቀደም ሲል “በታችኛው የፓርቲ መዋቅር ውስጥ በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ተደጋጋሚ የስም ማጥፋት እየተሰራጨብን ነው” በማለት ክስ ሰንዝረው፤ በተፈናቃዮች መመለስ እና ሌሎች የሕዝቡ አስቸኳይ ጉዳያችን ትኩረት አድርገው እንዳይሠሩ መደረጋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደራቸውን በክልሉ ውስጥ ወደ ወታችኛው የአስዳደር መዋቅር ማለትም ወደ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ ማውረድ እንደተሳናቸው ተናግረው ነበር።
የውስጥ አዋቂው እንደሚሉት አቶ ጌታቸው ረዳም በጊዜያዊ አስደዳሩ ያላቸውን የበላይነት እና የክልሉን የመንግሥት መዋቅር ተጠቅመው አቶ ዓለም ገብረዋህድን እና መዋቅሮቹን ለማዳከም ጥረት አድርገዋል።
ሆኖም እንደሌሎቹ የቀደሙ የህወሓት አመራሮች ስር የሰደደ ‘ኔትወርክና’ ድርጅታዊ መዋቅር ስለሌላቸው እምብዛም የሚፈልጉትን መፈጸም አልቻሉም ይላሉ የቢቢሲ ምንጮች።
ከዚህም በተጨማሪም ሌላኛዋ በአቶ ጌታቸው ላይ የሚዘምቱት ተብለው የሚታሙት የህወሓት የሥራ አስፈጻሚ አባሏ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ናቸው።
ፈትለወርቅ በአሁኑ ወቅት ከጉባዔው ራሳቸውን ካገለሉት እና የማዕካላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ በየነ ምክሩ ጋር የቆየ ጠብ እንዳላቸው ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
ያም ሆነ ይህ ስብሰባውን በጥድፊያ የጠራው በሊቀመንበሩ ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን፣ በአቶ ጌታቸው ቡድን ላይ ፍጹም የበላይነትን መያዙ ይነገራል።
የውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በዚሁ ቡድን እየተመራ ያለው ጉባኤ የአቶ ጌታቸው ረዳ ቡድንን በ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል ወቅት እንደታየው “አንጃ” በማለት ከድርጅቱ ገሸሽ በማድረግ “ህወሓትን ለማፅዳት” ጉባኤው ሳይውል ሳያድር በማካሄድ ላይ ተጠምዷል።
“በድርጅቱ ውስጥ ተፈልፍሎ የደለበ” ያሉትን የእነ አቶ ጌታቸው ቡድንን “ቆርጦ ለመጣል” ብቸኛው መፍትሄ እንደሆን ሊቀመንበሩ ደብረጽዮን በመክፈቻ ንግግራቸው ፍንጭ መስጠታቸውን ልብ ይሏል።
እንዲሁም ደግሞ የህወሓት ጽህፈት ቤት “ቂም ቋጥሮብናል” የሚሏቸውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን በምንም መንገድ ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ በከፍተና ደረጃ ዘመቻ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ከአባላቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጄኔራል ፃድቃን በ1993 ዓ.ም. በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል ወቅት በአንጃነት ተፈርጀው ከሥልጣን ከተገለሉት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካክል ሲሆኑ፣ በትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎችን ተቀላቅለው በአመራርነት መሳተፋቸው ይታወቃል።
በተጨማሪም በፕሪቶርያ የስላም ስምምነት ላይ የትግራይ ኃይሎችን ወክለው ተደራዳሪ ሆነው የተገኙ ሲሆን፣ ከስምምነቱ በኋላ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር “አካሄዱ አካታች አይደለም” በሚል ህወሓት ላይ ወቀሳ ሰንዝረው ነበር።
የህወሓት አባል ባይሆኑም ጄኔራል ፃድቃን በአሁኑ ውቅት በምክትል ፕሬዝዳንትነት የልማት እና መልካም አስተደዳር ዘርፍ አስተባበሪ ሲሆኑ፣ በህወሓት ጽህፈት ቤት በበጎ ከማይታዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት መካከል መሆናቸውን የህወሓት ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የተጠናከረው መቧደን
ህወሓት 13ኛ ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ በፓርቲው ውስጥ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እና መቧደን ሰፍኖ እንደነበር እንዲሁም የሕዝቡን መብት እና ነፃነት የማፈን አዝማሚያዎች እንዳሉ ማመኑ ይታወሳል።
ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የገባው ውዝግብ እና ውጥረት ተካሮ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ለሚጠግ ሕዝብ ዕልቂት ምክንያት የሆነው የሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሹ ጦርነት ተቀሰቀሰ።
አንዳንድ ሰዎች በተለይ ደግሞ የትግራይ ብሔርተኛ ድርጅቶች ለጦርነቱ መቀስቀስ እና ላስከተለው ጥፋት ህወሓትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ድርጅቱ ግን “ሕዝባዊ ትግሉን መርቼ ሕዝቡን ከጥፋት አድኜዋለሁ” ብሎ ያምናል።
“አመራሩ የሚያሳስበው የፓርቲው ማገገም እና ደኅንነት እንጂ የሕዝብን ኪሳራ ለማካካስ ወይም ይቅርታ ለመጠየቅ አይደለም” ሲሉ የውስጥ አዋቂው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እያንዳንዱ የህወሓት ቡድን አንዱ ሌላውን በመክሰስ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚሞክር ሲሆን፣ የህወሓት ሊቀመንበሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ይቅርታ ይጠይቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም ምንም የተሰማ ነገር የለም።
ጦርነቱን እና የደረሰውን ጉዳት የጉባኤው አጀንዳ ስለ መሆኑንም የሚያመለክት አንዳች ነገር አስካሁን አልተሰማም።
የተመናመነው አመራር
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወት ሳሉ በድርጅቱ ውስጥ የተጀመረው የ“ጥልቅ ተሃድሶ” ዕቅድ አቅጣጫውን ስቶ ወደ መጠቃቃት መድረክነት ተሸጋግሯል የሚሉ የህወሓት አባላት አሉ።
ይህ አዝማሚያ በተለይ በ12ኛው እና በ13ኛው ጉባኤዎች ላይ በደንብ የተንፀባረቀ ሲሆን፣ የመቧደን ዝንባሌ እያደገ፣ ልዩነቶች እየሰፉ፣ የድርጅቱ ውስጣዊ ውጥረት እየሰፋ አሁን የሚታየው ከፍተኛ መሰነጣጠቅ ላይ ተደርሷል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ አመራሩ መካከል የተፈጠረው ውዝግብን አስመልክተው “የውስጥ ግጭቶችን የመፍታት ዲሞክራሲያዊ ባህል የለውም፤ የድርጅቱ ኮሚኒስታዊ ባህሪው አይፈቅድለትም” ይላሉ የቀድሞ የህወሓት አመራር አባል እና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት።
አሁን የሚታየው መከፋፈል ድርጁቱን ወዴት እንደሚያመራ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም ከድርጅቱ ያለፈ ታሪክ ተለይቶ የማይታይ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
የሚያስከተልው አደጋው
በአመራሩ መካከል ያለው አለመግባበት የታጠቁ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዳያስከትል የሚሰጋ ሲሆን፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት ምክትል የሆነት የፀጥታ ኃላፊ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ግን የፀጥታ ኃይሉ ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ ይቀጥላል የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።
ሆኖም የፌደራል መንግሥቱ ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ሃሳብ “ህወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት በመጣስ ለሦስተኛ ጊዜ ስህትት ሰርቷ” ማለታቸውን ተክትሎ ግንኙነቱ ውዴት ሊያመራ እንደሚችል ኣሳሰቢ ሆኗል።
የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በህሓወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው መከፋፈል እና የፌዴራል መንግሥቱ በቀጣይ ሊወስድ ከሚችለው እርምጃ ጋር በተያዘ ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዙ ያልታወቀ ሲሆን፣ ይህም ወደ ሌላ ዙር ውዝግብ እና ጦርነት እንዳያመራ ስጋት ተፈጥሯል።
ለወራት ሲብላላ ቆይቶ አሁን ይፋ የወጣው የህወሓት አመራሮች ክፍፍል “የትግራይን ሕዝብ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ሕዝብ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከሥነ ልቦናዊ እና ከፀጥታ ችግር እንዳይወጣ የሚያደርግ አዝማሚያ” መሆኑን የፓርቲው ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።