ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ህወሓት ከፈረሰ የፕሪቶሪያው ስምምነት አይኖርም” ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “ህወሓት ከፈረሰ የፕሪቶሪያው ስምምነት አይኖርም” ሲሉ ተናግሩ።
ደብረጺዮን ይህን ያሉት በድርጅቱ ውስጥ ከፍፍል በፈጠረው እና እያነጋገረ ባለው የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ ላይ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
የፓርቲው ሊቀ መንበር ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. “ህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት መከልከል ማለት ውሉን ማፍረስ ነው” ካሉ በኋላ ፓርቲው የሚፈርስ ከሆነ “የትግራይን ሕዝብ ለበላተኛ አሳልፎ መስጠት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ፕሪቶሪያ ላይ የደረሱትን ሰምምነት ተከትሎ መቋጨቱ ይታወሳል።
ደብረጽዮን ህወሓትን ማፈርስ የፕሪቶሪያን ስምምነት ማጥፋት ነው ይበሉ እንጂ፤ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ግን ህወሓት ይህን ጉባኤ ማደረጉ “በተጨባጭ ተግባር የፕሪቶሪያውን ስምምነት ደምስሶታል” ብለዋል።
ህወሓት ባለፉት ወራት የፕሪቶሪያን ሰምምነት ሲሸራርፍ ቆይቷል ያሉት ለገሰ ቱሉ፤ “የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል። አንዴ፣ ሁለቴ፣ መሳሳት ያለንና የነበረ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ስህተት ሶስቴ መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ ብቻኛው ተጠያቂ እራሱ ይሆናል” ሲሉ በማሕበራዊ ሚዲያቸው ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህወሓት አመራሮች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንከር ያለ ክፍፍል ተፈጥሯል።
በአመራሮች መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እና አሁን እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ነው።
በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው ቡድን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ የተሰረዘው የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስለት እና ከማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የፓርቲውን 14ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ እንዲደረግ አድርጓል።
በሌላ በኩል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ያሉበት ቡድን፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅታዊ ጉባኤው እንዲካሄድ ፍላጎት የላቸውም። ፓርቲው፤ ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካቀረበው ጥያቄ ጋር የቀረቡ ሰነዶች ሕጋዊነት ላይም ጥያቄ ያነሳሉ።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመረጡበት ይህ ጉባኤ የሚካሄድ ከሆነ፤ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሊገለሉ ይችላሉ የሚል ግምትም አለ።
የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ቢቃወሙትም እነ ደብረጽዮን ጉባኤውን ከትናንት ጀምሮ በትግራይ መዲና መቀለ ማድረግ ጀምሯል።
“በውስጣችን የተፈለፈለ የጥፋት ቡድን አለ”
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የፓርቲው ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ባደረጉት ንግግር “ባለፉት 49ኛ ዓመታት ካካሄድናቸው 13 መደበኛ እና 1 አስቸኳይ ጉባኤ ይህ ጉባኤ በዓይነቱ እና በባህሪው የተለየ ነው” ብለዋል።
ሊቀመንበሩ ይህ ጉባኤ የተጠራው ከስደስት ዓመታት በኋላ መሆኑን አስታውሰው፤ የጦርነት መዘዝ የትግራይን ሕዝብ የተለያየ ችግር ውስጥ ባስገባበት ወቅት እየተካሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ “ፓርቲው በከባድ የውስጥ ቀውስ በተወጠረበት ጊዜ እየተካሄደ ያለ” ነው ብለዋል።
ጨምረውም “በዋናነት በፓርቲያችን ያለፉ 50 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ፤ ባለፉት 6 ዓመታት ፓርቲያችንን ሲመራ በቆየ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የታየ መበስበስ ፓርቲውን አፍርሶ ሕዝብ እንዲበተን የሚያደርግ ሁኔታን በባሰበት ወቅት ነው እየተካሄደ ያለ ጉባኤ ነው።”
ደብረጽዮን (ዶ/ር) የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንደማይመለስ እና ጉባኤ እንዳይካሄድ የሚያደናቅፍ “በውስጣችን የተፈለፈለ የጥፋት አንጃ/ቡድን የሚያካሄደው እንቅስቃሴ የፓርቲውን ሁኔታ ወደካፋ ደረጃ እንዳሸጋገረው” ተናግረው “ጉባኤ ማካሄድ ብቸኛ መፍትሄ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የጉባኤውን መካሄድ በመቃወም በርካታ የፓርቲው አመራሮች ከሂደቱ እራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደግሞ ሰኞ ዕለት ለህወሓት በጻፈው ጉባኤው የሚጠበቀውን ሕጋዊ ሂደት የተከተለ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል።