ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በህወሓት ጉባኤ መካሄድ ላይ ለሁለት በተከፈሉት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ተካርሯል
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል በትግራይ ውጥረት ተፈጥሯል።
በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የፓርቲውን ድርጅታዊ ጉባኤ ከማካሄድ እና ከፓርቲው ዳግመኛ ሕጋዊ እውቅና ከማግኘት ሂደት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ተካረዋል።
ይህን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሩዝዳንት እና የህወሃት ምክትል ሊቀ-መንበር ጌታቸው ረዳ እና በፓርቲው ሊቀ-መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራ ክፍፍል ተፈጥሯል።
በእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው ቡድን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ የተሰረዘው የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስለት እና ከነገ ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የፓርቲውን 14ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ማድረግ ይፈልጋል።
በሌላ በኩል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ያሉበት ቡድን፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅታዊ ጉባኤው እንዲካሄድ ፍላጎት የላቸውም። ፓርቲው፤ ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካቀረበው ጥያቄ ጋር የቀረቡ ሰነዶች ሕጋዊነት ላይም ጥያቄ ያነሳሉ።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመረጡበት ይህ ጉባኤ የሚካሄድ ከሆነ፤ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሊገለሉ ይችላሉ የሚል ግምትም አለ።
ትናንት እሁድ ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም. አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 14 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በፓርቲ ውስጥ ያለ “አንጃ” ለማዘጋጀት ባቀደው ጉባኤ ላይ አንሳተፍም ብለዋል።
ከእነዚህ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል፤ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኃላፊ ሰብለ ካሕሳይ፣ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ረዳኢ ሓለፎም እና ሓጎስ ጎድፋይ ይገኙበታል።
አስራ አራቱ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ ራሳቸውን ያገለሉት ክልሉ ሳይረጋጋ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ የፓርቲ ጉባኤ ለማካሄድ የሚደረገውን ጥረት አንቀበልም በሚል ነው።
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ፤ በህወሓት ጽህፈት ቤት ውስጥ ያለው ቡድን የሚያዘጋጀው ጉባኤ “ለራስ ጥቅም” ሲባል የሚደረግ ከመሆኑም በላይ “ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል” ነው ብለዋል።
የድርጅታዊ ጉባኤውን ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ያለውም፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይሁንታን ሳይገኝ እና የድርጅቱ የማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ውድቅ አድርጎት ባለበት ወቅት ነው ሲሉም የጉባኤውን መደረግ የተቃወሙበትን ተጨማሪ ምክንያት ጠቅሰዋል።
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበርን ያካተተው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብስብ ይህንን ተቃውሞ ቢያሰማም፤ ድርጅታዊ ጉባኤው የመካሄዱ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን የፓርቲው ሊቀ-መንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል አስታውቀዋል።
ዶ/ር ደብረጺዮን፤ ትናንት እሁድ ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “ጉባኤውን ለማድረግ የማንንም ይሁንታ ማግኘት አይጠበቅብንም” ሲሉ ጉባኤው በነገው ዕለት [ማክሰኞ] እንደሚካሄድ አስረግጠው ተናግረዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች አዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንደሚመርጡም ገልጸዋል። “አሁን በፓርቲ ውስጥ ያለው ውጥረት አዲስ ምርጫ ማድረግ እንደሚያስፈልገን የሚያሳይ ነው” ያሉት ደብረጺዮን፤ በዚህ ስብሰባ አዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ለማድረግ በአጀንዳ መያዙን አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክትል አስተዳዳሪ እና የክልሉ የፀጥታ ኃላፊ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ላለልተወሰነ ጊዜ የድጋፍም ይሁን የተቋውሞ ሰልፍ በክልሉ ውስጥ ማድረግ ተከልክሏል ብለዋል።
ጄኔራል ታደሰ ትናንት እሁድ ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህን ክልከላ ያስታወቁት፤ የጉባኤውን መደረግ የሚደግፉ ሰልፎች ዛሬ ሰኞ እና ነገ ማክሰኞ በመቀለ ከተማ እና በሌሎች ትግራይ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፎች ለማድረግ ዝግጅቶች አሉ መባሉን ተከትሎ ነው።
ጄኔራል ታደሰ በመግለጫቸው፤ ፓለቲካዊ አለመግባባት ወደ ማንኛውም የፀጥታ አደጋ እንዲሸጋገር አንፈቅድም ካሉ በኋላ “ፖለቲካዊ ልዩነቶች በንግግር ብቻ መፈታት አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል።
ጄኔራሉ ምንም እንኳ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ተከልክሏል ቢሉም ጉባኤው ላይ ለመታደም ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወደ መቀለ ከተማ ጉዞ የጀመሩ ተሳታፊዎች የአደባባይ ላይ ሽኝት እና አቀባበል ሲደረግላቸው ታይቷል።
በስብሰባው ለመሳተፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፓርቲው አባል ከተያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመነሳት ወደ መዲናዋ መቀለ እየተጓዙ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የህወሓት ምዝገባ
በህወሓት አመራሮች መካካል ልዩነት የፈጠረው ሌላኛው ጉዳይ የፓርቲው ዳግም ምዝገባ ወይም ሕጋዊ እውቅና መልሶ የማግኘት ሁኔታ ነው።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ ህወሓት “በአመጻ ተግባር ላይ መሰማራቱ በመረጋገጡ” ሕጋዊ የፓርቲ እውቅናው በምርጫ ቦርድ ተሰርዞ እንደነበረ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል በፕሪቶሪያ በተደረገ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ፓርቲው ዳግም በምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ” ከጥቂት ቀናት በፊት መመዝገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በፓርቲው ሊቀ-መንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን ፓርቲው ዳግም ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት እንጂ ዳግም እንዲመዘገብ እንደማይፈልግ አስታውቋል።
ፓርቲው ቅዳሜ ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ “የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ” የሚል መሆኑን በማስታወስ፤ በምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ መመዝገብን እንደማይቀበል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የሕጋዊ እውቅና ይመለስልኝ ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ብለዋል።
አቶ ጌታቸው፤ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ለቦርዱ በጻፉት ደብዳቤ “የምዝገባ ጥያቄው” የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያልወሰነበት መሆኑን ጠቅሰዋል፤ “እኛ ለዚሁ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም ዓይነት ሠነድ ሳይኖር፣ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው ከድርጅቱ አሠራር ውጪ የፈፀሙት ያልተገባ ተግባር መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን” ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ምላሽ
በህወሓት መካከል የተከሰተውን አለመግባባት በተመለተ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የህወሓት አመራሮች “ሕዝብን ከማይጠቅም ትርጉም አልባ ንትርክ” እንዲወጡ ጠይቋል።
መግለጫው፤ “የሕግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ሕግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው” ሲል የፌደራል መንግሥትን አቋም አስታውቋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት፤ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እና እውቅና ለማግኘት የሚጠበቅበትን ሠነዶች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል ካለ በኋላ፤ “የምዝገባ እና የሕግ ሰውነት ጉዳይ በዚህ መቋጨት አለበት” ብሏል።
“አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸውን ጎልህ የሰላም እና የልማት አደንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል” ሲል አክሏል።
በሁለት ወገን ተከፍለው ውዝግብ ውስጥ የገቡት የህወሓት መሪዎች በየፊናቸው አቋም የያዙ ሲሆን፣ በድርጅቱ ሊቀ መንበር የሚመራው ወገን የፓርቲውን ጉባኤ ለማካሄድ ወስኖ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።