ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት ሊያደርግ ካሰበው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ፓርቲያቸው በቅርቡ ሊያደርግ ካቀደው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ። አቶ ጌታቸው፤ ፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ ለማድረግ እያካሄደ ያለውን ዝግጅት “በአንድ አካል እየተፈፀመ ያለ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ” ብለውታል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ይህንን አቋማቸውን ያሳወቁት ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም. ለፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና ለፓርቲው ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በጻፉት ደብዳቤ ነው።
አቶ ጌታቸው፤ ይህንን አቋማቸውን ለፓርቲው በጻፉት ደብዳቤ ማስታወቃቸውን አንድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ጌታቸው ደብዳቤውን የጻፉት ህወሓት ሊያደርግ እየተዘጋጀ ያለውን 14ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤን በተመለከተ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል ልዩነት እየተስተዋለ ባለበት ወቅት ነው። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሚመረጡበት በዚህ ጉባኤ የሚታደሙ ተሳታፊዎች መረጣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተከናወነ ነው።
ይሁንና በደቡብ ትግራይ እና ደቡብ ምሥራቅ እንደርታ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች በጉባኤው በዚህ ወቅት መካሄዱን እንደማይደግፉት አስታውቀዋል።
የፓርቲው የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም ጉባኤው “ድርጅቱ ውስጥ ‘በተሰባሰቡ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል” በማለት ራሳቸውን ማግለላቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳም በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ከድምጺ ወያነ ትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጉባኤው በአሁኑ ወቅት መካሄዱን እንደማይደግፉ አመልክተው ነበር።
በቃለ መጠይቁ ላይ “ድርጅቱ ጊዜው የሚጠይቀውን ሃሳብ ማመንጨት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው” ሲሉ የተቹት አቶ ጌታቸው፤ “ሃሳብ በሌለበት የሚደረገው ጉባኤ ላይ የሚመረጠው ኃይል ምን ላይ ተመሥርቶ ነው ትግራይን የሚያስተዳድረው?” በማለት ጠይቀዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ትናንት በጻፉት ደብዳቤ ላይም ጉባኤው ተችተዋል። ጉባኤውን ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ያለው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ “ጉባዔው መቼ እና እንዴት ባለ ሁኔታ ይከናወናል ስለሚለው ጉዳይ መግባባት ባልደረሰበት” ሁኔታ እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው፤ “አሁን እየተደረገ ያለው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ ኮሚቲውም ሆነ ከእኔ እውቅና ውጪ ነው። የጉባዔው ዲሞክራሲያዊነት እና ሕጋዊነት ላይ መረዳዳት ሳይደረስ ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እውቅና ውጪ ምዝገባ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳለ ተረድተናል” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ለጉባኤው እየተደረገ ያለውን ዝግጅት “በአንድ አካል እየተፈፀመ ያለ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ” ሲሉ የጠሩት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ ይህንን እያዘጋጀ ያለው “አካል የድርጅታችንን አሠራር በመጣስ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ፓርቲያችን በማያዋጣው መንገድ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው” ሲሉ ከስሰዋል።
“መሬት ላይ ያለው ቅጣ ያጣ እንቅስቃሴ በስተመጨረሻ ድርጅታችን እና ሕዝባችንን አደጋ ላይ እንደሚጥለው ግልፅ ነው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ህወሓት፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የተሰረዘበት እውቅናው እንዲመለስለት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄንም በተመለከተ አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ፓርቲው ይህንን ጥያቄውን ያቀረበው ከሁለት ሳምንት በፊት ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነበር።
ፓርቲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የለጠፈው ድብዳቤ፤ “ቦርዱ የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመልስ” መጠየቁን የሚያሳይ ነው። የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሓት የተሰረዘው ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ ተናግረው ነበር።
አቶ ጌታቸው፤ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ግን “በአዲሱ አዋጅ መሠረት ማዕከላዊው ኮሚቲ ያልፈመበትን የተጭበረበረ ሰነድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስገብቷል” ሲሉ ከስሰዋል።
አቶ ጌታቸው “አዲሱ አዋጅ” በማለት የጠቀሱት በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ላይ የተደረገ ማሻሻያ፤ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት የሚመዘግበበትን አካሄድ በዝርዝር ያስቀመጠነው።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት፤ “ይሄ ተራ ስህተት ብቻ ሳይሆን ድርጅታችንን ለማፍረስ እና የትግራይ ሕዝብን ትግል ከንቱ ለማድረግ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው” ሲሉ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ተጽፏል ያሉትን ደብዳቤ ተቃውመዋል።
“እውቅና ለማግኘት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የገባው ጥያቄም ሆነ በህወሓት ስም ጉባዔ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ፓርቲውን የማይወክል እና በአንድ አካል እየተፈፀመ ያለ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ስለሆነ እንደማልቀበለው አሳውቃለሁ” ብለዋል። አቶ ጌታቸው፤ “ሕጋዊ ያልሆነ” ያሉትን ይህንን እንቅስቃሴን “አለመቀበል ብቻ ሳይሆን” እንደሚታገሉትም ገልጸዋል።
“እኔ በማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን በኩል ያቀረብኩት ጥያቄ እና ሌሎች በርከት ያሉ የድርጅታችን መሪዎች ያቀረቡት ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ በአንድ አካል የተሰናዳ ጉባዔ ላይም ሆነ [የፓርቲው] ምዝገባ ላይ የማልሳተፍ መሆኑን አሳውቃለሁ” ሲሉ አቋማቸውን አስረድተዋል።