ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ “ከባድ” ያለው ፈተና ውስጥ መውደቁን ገለጸ
ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ይዞ የቆየው ህወሓት (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) “በ50 ዓመት ታሪኬ ከባዱ ፈተና ተጋርጦብኛል” አለ።
ፓርቲው በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ለቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የከፍተኛ አመራሮች ጉባኤ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ የግል ጥቅምን ማስቀደም የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉን አስታውቋል።
ፓርቲው ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ከሕዝባዊ ወገንተኝነት ያፈነገጠ እና ለግል ጥቅም መሰባሰብ” በተደራጀ መልኩ መሥራት እንዳላስቻለው ገልጿል።
ፓርቲው በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ያጋጠመው የችግር ምንጭ “ቡድናዊነት፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት፣ ጎጠኝነት፣ ሕዝበኝነት እና ሙስና” ናቸው ብሏል።
ፓርቲው ከፌደራል መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቀስቅሶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ ድርጅት” ተብሎ ተፈርጆ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ በኋላም ፓርቲው ንብረቱ ተወርሶ እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅናው መሰረዙ የፓርቲው ህልውና ያበቃለት አስመስሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ፓርቲው ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ይገኛል።
ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጥሎበት የነበረው “የአሸባሪ ቡድንንት” ፍረጃም ተነስቶለታል።
ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብ የፍትሕ ሚኒስቴር መጠየቁ ይታወሳል።
ህወሓት በማክሰኞው መግለጫው ላይም ሕጋዊ ፍቃዱ እንዲመሰለት ለፌደራል መንግሥቱ ጥሪ አቅርቧል።
ፓርቲው ክልሉን እያስተዳደረ ሕጋዊ እውቅናውን ለማስመለስ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ቢሆንም ህልውናውን አደጋ ላይ የጣለ ውስጣዊ ችግር እንደተጋረጠበት በመግለጫው ገልጿል።
“በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ሕዝቡ ከባድ ሸክም እንዲሸከም አድርጎት ቆይቷል” ብሏል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ።
ህወሓት 2016 ዓ.ም. ከመገባደዱ በፊት የፓርቲውን አጠቃላይ ጉባኤ እንደሚያካሂድ ገልጾ፤ የአጠቃላይ የጉባኤው ዓላማ የፓርቲውን ህልውና ማረጋገጥ” መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።
ህወሓት በመግለጫው ይህ አጠቃላይ ጉባኤ እንዳይካሄድ ፍላጎት ያላቸው በፓርቲ ውስጥ ያሉ ቡድኖች መኖራቸውን ጠቁሞ፤ “ጉባኤው እንዳይካሄድ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም” ብሏል።
ፓርቲው በመግለጫው በትግራይ የከበሩ ማዕድናት ሃብት አያያዝ እና አጠቃቀምን በተመለከተም ችግሮች መኖራቸውን አውስቷል።
ፓርቲው ይህን ያለው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የክልሉ ባለሥልጣናት እና ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑበት ሕገ-ወጥ የማዕድን ብዝበዛ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ስም የሚደረጉ የመሬት ወረራዎች መስፋፋታቸውን የተመለከቱ ሪፖርቶች እየወጡ ባሉበት ወቅት ነው።
ፓርቲው የትግራይ ክልል ሃብት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ እና በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጿል።
ህወሓት አገሪቱን ለ27 ዓመታት በጥምረት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ መሥራች እና አስኳል የነበረ ሲሆን፣ በአገሪቱ አስደዳር ላይ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአመራር ለውጥ ከመጣ በኋላ ፓርቲው ለማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ነበር።
በትግራይ ደም አፋሳሹ ጦርነት ለሁለት ዓመት ከተካሄደ በኋላ ህወሓት መልሶ ለመጠናከር ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በአመራሩ ውስጥ አለመግባባት እንዳለ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
የህወሓት አመራሮች ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ለቀናት ቆዩ ስብሰባዎችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በቅርቡ ባካሄዱት ስብሰባም ድርጅቱ በአምስት አስርት ዓመታት ውስጥ ያላየው ከባድ ፈተና እንደገጠመው መግለጹ በቀጣይ በሚኖረው ጉባኤው ላይ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚል ግምትን አሳድሯል።