የሶማሊያ መንግሥት ሲያጓጉዘው የነበረ የጦር መሳሪያ በሚሊሻዎች እና በነዋሪዎች ተዘረፈ

ትናንት ሰኞ ሐምሌ 8/2016 ዓ.ም. በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ ግዛት የአገሪቱ መንግሥት ኃይሎች ሲያጓጉዙት የነበረ በርካታ ጦር መሳሪያ በሚሊሻ አባላት እና በአካባቢው ነዋሪዎች ተዘረፈ።

ዘረፋውን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ማክሰኞ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በድብቅ የገባ ጦር መሳሪያን የሶማሊያ የደኅንነት ኃይሎች ይዘው ሲጓጉዙ በአካባቢ ሚሊሻ አባላት መዘረፉን አሳውቋል።

የሶማሊያ መንግሥት የተዘረፈው ጦር መሳሪያው በሕገ-ወጥ መንገድ አገር ውስጥ የገባ ነው ይበል እንጂ አንዳንድ ሪፖርቶች ጦር መሳሪያው የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት የገዛው ስለመሆኑ እየገለጹ ነው።

ዘረፋው የተፈጸመበት የጋልሙዱግ ግዛት የደኅንነት ምክትል ኃላፊ አሊ ባሺ አብዱላሂ ጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የሶማሊያ መረጃ እና የደኅንነት ኤጀንሲ አባላት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል።

በዚህም አንድ ከፍተኛ መኮንን ጨምሮ አስር የሚሆኑ የሶማሊያ ደኅንት ተቋም አባላት በጥቃቱ ተገድለው በሁለት የጭነት መኮኖች ሲጓጓዙ የነበሩ ጦር መሳሪያዎች መዘረፉቸውን አሊ ባሺ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።

ጨምረውም “የተዘረፉት ጦር መሳሪያዎች መነሻ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢኖረንም ይህን እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም” ብለዋል።

ኩልሚዬ የተባለ የአካባቢው ራዲዮ ጣቢያ በበኩሉ በሁለት የጭነት መኪኖች ሲጓጓዙ የነበሩት በርካታ ኤኬ 47 ክላሾች፣ ሽጉጦች እና አራፒጂ የተባሉት ጦር መሳሪያዎች ከኢትዮጵያ በግዢ መምጣታቸውን ዘግቧል።

ነገር ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለጦር መሳሪያዎቹ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የሚሊሻ አባላት በወታደራዊ ‘ፒክ አፕ’ መኪኖች ጦር መሳሪያዎችን ጭነው ሲሄዱ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካባቢው ነዋሪዎች በፕላስቲክ የተሸፈኑ አዳዲስ የጦር መሳሪየዎች ይዘው አሳይተዋል።

ዘረፋው የተፈጸመበት የጋልሙዱግ ግዛት ምክትል የደኅንነት ኃላፊ አሊ ባሺ ለቢቢሲ አንደገለጹት የሶማሊያ መንግሥት ጦር መሳሪያውን በግዛቲቱ ውስጥ ለሚገኘው የአገሪቱ የመረጃ እና የደኅንነት ኤጀንሲ አገልግሎት እንዲውሉ ሲያጓጓዙ ነበር።

በዚህም በሁለት የጭነት መኪኖች ሲጓጓዙ የነበሩት የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች እና ሮኬት ማስወንጨፊያ የሆኑት አርፒጂ የቡድን መሳሪያዎች በደኅንነት ተቋሙ አባላት እንደነበር ገልጸዋል።

በአካባቢው ሚሊሻዎች በተሽከርካሪዎቹ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከደኅንነት አባላቱ ጋር የተኩስ ልውውጥ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ሁሉም የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የደኅንነት አባላት መገደላቸው ተነግሯል።

የጦር መሳሪያው ዘረፋ የተፈጸመበት አቡደዋቅ የተባለ አካባቢ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ሲናገሩ፣ ጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ተሸርካሪዎች በሚሊሻ አባላቱ እንዲቆሙ ከተደረገ በኋላ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል ብለዋል።

ኩልሚዬ የተባለው የራዲዮ ጣቢያ ዘረፋውን የፈጸመው ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የሚዋጋ በጎሳ የተደራጀ ቡድን መሆኑን ጠቅሶ፤ የሚሊሻ ቡድኑ ጦር መሳሪያው ሲጓጓዝ የነበረው የመንግሥት አጋር ለሆነ ቡድን ነው ስለማለቱ ጨምሮ ዘግቧል።

ዘረፋውን ተከትሎ የሶማሊያ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር ማክሰኞ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ግን በሕገ-ወጥ መንግድ ከኢትዮጵያ የገባ ነው ያለው የጦር መሳሪያ የአገሪቱ መንግሥት ከያዘ በኋላ ማገጓጓዝ ላይ ሳለ በሚሊሻ አባላቱ ተዘርፏል ብሏል።

የጋልሙዱግ የደኅንነት ምክትል ኃላፊ የጦር መሳሪያው የሶማሊያ መንግሥት ሲያጓጉዘው እንደነበር ገልጸው፤ ነገር ግን ትክክለኛ መረጃ ውጥረት ላለበት የአካባቢው ነዋሪዎች ባለመሰጠቱ ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጸዋል።

በመጀመሪያ ላይ ተሽከርካሪዎቹ የሬዲዮ አንቴናዎች እና መብራቶችን ያያዙ ናቸው ተብሎ የተነገረ ሲሆን፣ ይህም በአካባቢው ሚሊሻዎች ዘንድ ጥርጣሬ በመፍጠሩ ግጭት ተከስቶ የጦር ማሳሪያዎቹን ለዘረፋ እንደዳረጋቸው ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴሩ ዘረፋውን አጥብቆ አውግዞ ጦር መሳሪዎቹን መልሶ ለመያዝ የአካባቢው ማኅብረሰብ ትብብር እንዲያደርግ ጨምሮ ጠይቋል።

ይህ በማዕካላዊ ሶማሊያ የተፈጸመው የጦር መሪያ ዝርፊያ መረጋገት በተሳናት እና በእስላማዊው ቡድኑ አል-ሸባብ በምትታመሰው አገር የበለጠ የደኅንነት ስጋት ሆኖ ታይቷል።

አንዳንዶች ከዘረፋው በኋላ በማዕካለዊ ሶማሊያ የአንድ ክላሽንኮቭ ዋጋ በመዲናዋ ሞቃዲሹ ከሚሸጠው ዋጋ በአራት እጥፍ ባነሰ ዋጋ ለገበያ እየቀረበ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።

ሶማሊያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት ለሰላሳ ዓመታት ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር እንዲነሳ የተደረገው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የዚያድ ባሬ መንግሥትን ውድቀት ተከትሎ በአገሪቱ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለሶማሊያ መንግሥት ጦር መሳሪያ እንዳይተላለፍ ከልክሎ ቆይቷል።