የግድያ ሙከራው ለዶናልድ ትራምፕ ይዞላቸው የመጣው በረከቶች

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ዕጩ ለመሆን በተቃረቡበት ጊዜ የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ አሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከቀናት በኋላም ጉዳዩ ዋነኛ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይ የግድያ ሙከራው ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ በተካረረው የአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ሊከሰት ይችል የነበረውን ቀውስ በማሰብ አሜሪካውያን እፎይታን አግኝተዋል። ቢሆንም ግን አገሪቱን ከከባድ ፖለቲካዊ ማጥ ውስጥ ይከታት የነበረውን ግድያ በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች እና መካሰሶች እየተደመጡ ነው።

አንድ ዙር በፕሬዝዳንትነት ካገለገሉ በኋላ በሽንፈት ከዋይት ሐውስ የተባረሩት የ78 ዓመቱ አዛውንት መልሰው ወደ ኃያሏ አገር የሥልጣን መንበር ለመመለስ ቆርጠው በተነሱበት ጊዜ የገጠማቸው ፈተና ቀላል የሚባል አይደለም። ትራምፕ በመገናኛ ብዙኃን ከመብጠልጠላቸው ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ክስ ተከፍቶባቸው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ነው የከረሙት።

ከእነዚህ ውስጥም ታሪካዊ በተባለ የክስ ሂደት ትራምፕ ከንግድ መዝገቦች ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው 34 ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ ተብለዋል። ይህም በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ ያለም ይሁን ከሥልጣን የወረደ ፕሬዝዳንት በወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሲባል ትራምፕን የመጀመሪያው አድርጓቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሌሎች በፍርድ ቤት እያታዩ ያሉ ክሶች አሏቸው። ነገር ግን ትራምፕ ዋነኛው ግባቸው ወደ ሥልጣን መመለስ በመሆኑ ትኩረታቸውን ከወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ አድርገው የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ዕጩ ለመሆን ከጫፍ ደርሰዋል።

የግድያ ሙከራው

ክስ እና ትችቱ ሳይበግራቸው ዳግም ፕሬዝዳንት ለመሆን በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወሩ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከሚያደርጉት ጥረት በአንዱ ላይ ቅዳሜ ሐምሌ 6/2026 ዓ.ም. ፔንሲልቬኒያ ውስጥ በተገኙበት ወቅት ነበር የግድያ ሙከራ የተፈጸመባቸው።

ትራምፕ በፔንሲልቫኒያዋ በትለር ከተማ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉበት መድረክ በአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ከማሸብረቁ በተጨማሪ በስፍራው የነበረው የታዳሚው ስሜት ሞቅ ያለ ነበር። ትራምፕ ግን ወደ ስፍራው የደረሱት ከአንድ ሰዓት በላይ አርፍደው ቢሆንም በታዳሚው ላይ የፈጠረው ስሜት አልነበረም።

ትራምፕ ንግግር ማድረግ ጀምረው አምስት ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ዋነኛ የምርጫ መቀስቀሻ ርዕሳቸው ወደ ሆነው የሕገወጥ ስደተኞች ጉዳይ ሲገቡ ነበር ተኩሱ የተሰማው።

ከመድረኩ አቅራቢያ ከሚገኝ ሕንጻ አናት ላይ ሆኖ ትራምፕን አድብቶ ሲጠብቃቸው የነበረው የ20 ዓመቱ ማቲው ክሩክስ ለጭንቅላታቸው የተኮሳት ጥይት የቀኝ ጆሯቸውን መትታ ክፉ ሳይገጥማቸው ተርፈዋል።

በዚያች መድረክ ላይ ትራምፕ ለከባድ ጉዳት ወይም ለሞት ልትዳርጋቸውን ከነበረችው ጥይት የተረፉት “በዕድል ወይም በእግዚአብሔር ጥበቃ” መሆኑን ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ይህ የግድያ ሙከራ በትራምፕ የቀኝ ጆሮ ላይ ቀላል የሚባል ጉዳትን፣ የአንድ ሰው ሞትን እና የሁለት ሰዎችን ክፉኛ መጎዳትን ከማስከተሉ በሻገር የአሜሪካ ፖለቲካን እና ቀጣይ የምርጫ ሂደትን ድንግጋጤ ውስጥ ከትቷል። ከዚህ ባሻገር ግን ለትራምፕ አውንታዊ አጋጣሚዎችን የፈጠረ ነው እየተባለ ነው።

ያልታሰበ በረከት

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት የቀጥታ የቴሌቪዥን ውይይት ተሽለው የተገኙት ዶናልድ ትራምፕ በኅዳር ወር ለሚካሄደው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ሪፐብሊካኖችን ወደ ዋይት ሐውስ ይመልሳሉ ተብሎላቸዋል።

ስጋት የገባቸው ዲሞክራቶች ደግሞ የ81 ዓመቱ ባይደን በዕድሜ መግፋት የተነሳ ከትራምፕ ጋር ተከራክረው እና ተፎካክረው በፕሬዝዳንትነት ለመቀጠል የሚያስችላቸው አካላዊ እና አእምሯ ጥንካሬ የላቸውም በሚል ስጋት ከዕጩነት እንዲለቁ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ነገር ግን ባይደን ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየፈጸሙም ቢሆን ለሁለተኛ ዙር የመሪነት ዘመን ለመቀጠል የሚያግደኝ ነገር የለም በሚል ዕጩነታቸውን የሙጥኝ ብለዋል። ይህም በዲሞክራቶች መካከል ክፍፍልን ፈጥሯል።

ይህ በእንዲህ ባለበት ወቅት ነው ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገው። ክስተቱ በተለያዩ ክሶች ስማቸው ለጠለሸው ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ እና ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማግኘት ያልታሰበ በረከት ሆኖላቸዋል።

የአሸናፊነት ተስፋ

ከግድያው ሙከራ በኋላ በፕሬዝዳንታዊ የጥበቃ ቡድን አባላት ተከበው ከመድረኩ እንዲወርዱ በሚደረግበት ጊዜ ትራምፕ ፊታቸው ላይ ደም እየታየ ጥንካሬያቸውን እና አይበገሬነታቸውን ለማሳየት እጃቸውን አንስተው ለደጋፊዎቻቸው መልዕክት ሲያስተላልፉ የተነሱት ፎቶ ከአሜሪካ አልፎ በመላው ዓለም ትኩረትን ስቧል።

ጥቃቱ በፓርቲያቸው ላይ የተሰነዘረ ነው ብለው የሚያምኑ እና ትራምፕን ለመደገፍ ሲያመነቱ ለነበሩት ሪፐብሊካኖች መነቃቃትን የፈጠረ ምሥልም ሆኗል። በዚህም ተጨማሪ ድጋፍን ለማግኘት ሳይችሉ እንደማይቀር ተገምቷል።

የግድያ ሙከራው ከተቀናቃኞቻቸው የተሰነዘረ ነው ብለው የሚያስቡ በርካቶች ትራምፕ ከጥቃቱ በሕይወት መትረፋቸው ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ፕሬዝዳንታቸው እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ነው።

ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውርርድ በሚካሄድባቸው መድረኮች ላይ ከግድያው ሙከራ በኋላ ትራምፕ ምርጫውን ያሸንፋሉ ብለው የሚወራረዱ ሰዎች አሃዝ ወደ 66 በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክቷል።

ለዕጩነታቸው ወሳኝ ድጋፍ

ትራምፕ ባለፈው ግንቦት ወር የሂሳብ ሰነዶችን በማጭበርበር በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሲባሉ፣ በመጪው ኅዳር ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማግኘት ይቸገራሉ ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

ነገር ግን የፍርድ ውሳኔው በምርጫ ቅስቀሳቸው ዙሪያ አዲስ ጉልበት እንደፈጠረላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ከብይኑ በኋላ በነበሩት 24 ሰዓታት ውስጥ ወደ 53 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የምርጫ ድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል።

አሁን ደግሞ ፔንሲልቬኒያ ውስጥ የተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ድጋፍ እያስገኘላቸው ነው።

የዓለማችን ቀዳሚው ባለሃብት እንዲሁም የግዙፍ ተቋማት መሥራች እና ባለቤት የሆነው ኤሎን መስክ በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ከተፈጸመ በደቂቃዎች ውስጥ ትራምፕ ዕጩ ሆነው እዲቀርቡ ድጋፉን እንደሚሰጥ ገልጿል።

የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ባለቤት የሆነው ቢሊየነሩ መስክ፣ ትራምፕ ለህክምና መወሰዳቸውን ተከትሎ በገጹ ላይ “ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ እንዲሆኑ ሙሉ ለሙሉ እደግፋለሁ፤ ከጉዳታቸው በቶሎ እንደሚያገግሙም ተስፋ አለኝ” ብሎ ነበር።

ኤሎን መስክን ተከትሎ ደግሞ ሌላኛው ቢሊየነር ቢል አክማን ከጥቃቱ በኋላ ተጨባጭ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ የባይደን ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀርቡ ሙሉ ድጋፉን እንደሰጣቸው ይፋ አድርጓል።

ባለሃብቱ አክማን ከአራት ዓመት በፊት የትራምፕን የምርጫ ሽንፈት ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ካፒቶል ሂልን በመውረር ካጠቁ በኋላ ፊቱን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ አዙሮ ነበር። በወቅቱም ትራምፕ ከሥልጣን ለቀው አሜሪካውያንን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ነበር።

አሁን ከግድያው ሙከራ በኋላ ግን ቢል አክማን ያንን ተቃውሞውን በመተው ትራምፕ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ለመሆን ዕጩ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ይህ ትራምፕ ከተጽእኖ ፈጣሪ አሜሪካውያን ያገኙት ዕውቅና ከሌሎች የሪፐብሊካን ፓርቲ ወሳኝ ደጋፊዎች እና ከመራጮች ተጨማሪ ድጋፍ እና ድምጽ ለማግኘት በር ይከፍታላቸዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያቸው ዋጋ መጨመር

ትራምፕ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በሚያሰራጯቸው አወዛጋቢ ምልዕክቶች ምክንያት ከሚገጥሟቸው ተቃውሞ እና ውግዘቶች በተጨማሪ ከመድረኮቹ ባለቤቶች ማስጠንቀቂያዎች ይደርሷቸው ነበር።

ነገር ግን ትራምፕ ሁሉን ችላ ብለው የሚፈልጉትን እና የሚሰማቸውን በተደጋጋሚ በማቀረባቸው ከትዊተር እና ከፌስቡክ እስከመታገድ ደርሰው እንነበር ይታወሳል።

ይህ ያበሳጫቸው ዶናልድ ትራምፕ የግዙፎቹ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ተቀናቃኝ የሆነ እና እሳቸው ያለማንም ሃይ ባይ መልዕክታቸውን የሚያሰራጩበት ‘ትሩዝ ሶሻል’ የተባለ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ከፍተዋል። አሁንም ድረስ ትራምፕ መልዕክታቸውን የሚያቀርቡት በዚሁ መድረክ ላይ ነው።

የግድያ ሙከራውን ተከትሎ ትራምፕ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ በጥቃቱ የቀኝ ጆሯቸው የላይኛው ክፍል በጥይት መመታቱን እና በደህና ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ያሳወቁት በዚሁ የሶሻል ሚዲያ በኩል ነው።

በድርሻ ገበያው ውስጥ ባለፉት ዓመታት የጎላ ገቢ ያልነበረው ይህ የትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ የግድያ ሙከራው ከተደረገባቸው በኋላ በድርሻ ገበያው ላይ የ67 በመቶ ጭማሪ አግኝቷል።

ትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስር የሚገኘው ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ አብዛኛው ወይም 65 በመቶው ባለቤትነት በዶናልድ ትራምፕ ባለቤትነት ስር ያለ ሲሆን፣ በአክሲዮን ገበያው ውስጥ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ዋና እንዳለው ይነገራል።

ታዲያ የቅዳሜው የግድያ ሙከራ ለትራምፕ የምርጫ ጥረት ከባለሃብቶች እና ከመራጮች ድጋፍን ከማስገኘቱ በተጨማሪ ከማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማቸው የድርሻ ዋጋ መጨምርም እንደምክንያት እየቀረበ ነው።

ክሳቸው ውድቅ መሆን

ሌላው ከግድያ ሙከራው ሁለት ቀን በኋላ ትራምፕ የሰሙት መልካም ዜና ሰኞ ዕለት አመሻሽ ላይ የፍሎሪዳዋ ዳኛ ትራምፕ ፍርድ ቤት እየተመላለሱባቸው ካሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውን ክሳቸውን ውድቅ ማድረጋቸው ነው።

ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ከእጃቸው የገቡ ምሥጢራዊ ሰነዶችን በአግባቡ ይዘው ለሚመለከተው አካል ባለማስረከብ እና እያወቁ የብሔራዊ የመለከላከያ ሰነዶችን ይዘው በማቆየት ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ከለቀቁ በኋላ በርካታ የመንግሥት ምሥጢራዊ ሰነዶችን ማራ ላ ጎ በሚባለው ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አስቀምጠው በደኅንነት ሠራተኞች ፍተሻ ተገኝቶባቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥታዊ ምሥጢሮችን የያዙ ሰነዶችን በአግባቡ ባለመያዝ 40 ክሶች የቀርበውባቸው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸው ግን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ የሾሟቸው ዳኛዋ ኤይሊን ካነን ጉዳዩን የያዙት ዐቃቤ ሕግን በተመለከተ በሂደቱ ውስጥ ሁለት የሕገ መንግሥታዊ ጥሰትን ማግኘታቸው ጠቅሰው ነው ክሱን ውድቅ ያደረጉት።

ይህ የዳኛዋ ውሳኔ ይግባኝ የሚጠየቅበት ቢሆንም ከግድያ ሙከራው በኋላ ትራምፕ ከገጠሟቸው መልካም ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ

ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን ከጫፍ በደረሱበት ጊዜ ከተፈጸመባቸው ጥቃት ከመትረፋቸው ባሻገር የግድያ ሙከራውን ተከትሎ ለምርጫ ዘመቻቸው የሚያግዟቸው አውንታዊ ነገሮች እየገጠሟቸው ነው።

በመጪው ሐሙስ በፕሬዝዳንትነት የሚወክለውን ዕጩ በይፋ የሚያሳውቀው ሪፐብሊካን ፓርቲያቸው ወሳኙን ጉባኤ ያደርጋል።

ከግድያው ሙከራ በኋላ በበርካታ የፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ እንደ ሰማዕት እና የፓርቲው ምልክት ሆነው እየቀረቡ ያሉት ትራምፕ ያለችግር ዕጩነታቸውን የሚያረጋግጡበት ይሆናልም እየተባለ ነው።

በዚህም ጥቃቱ የተፈጸመበት ጊዜ ወሳኙ የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ጉባኤ ከሚካሄድበት ከቀናት በፊት መሆኑ ለትራምፕ የማይገኝ ግጥምጥሞሽ ሆኖላቸዋል።

የግድያ ሙከራው ድንጋጤ እና ስሜት ሳይቀዘቅዝ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይም ትራምፕ በኅዳር 2017 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ሆነው እንደሚወጡ ይጠበቃል።