ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን ያልተጠናቀቀው ቆጠራ አሳየ
በርካታ የድምጽ ጣቢያዎች ላይ ቆጠራው በተጠናቀቀው የሩዋንዳው ምርጫ አገሪቱን ለ24 ዓመታት የመሯት ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን አሳዬ።
79 በመቶው ቆጠራ በተጠናቀቀው ብሔራዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ 99.1 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
ሰኞ ሐምሌ 8/ 2016 ዓ.ም በተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ የ66 ዓመቱ ፖል ካጋሜ ሁነኛ ተቃዋሚ አላጋጣማቸውም ተብሏል። ምርጫው የተካሄደው ተፎካካሪዎቻቸው በታገዱበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በእጩነት የተወዳደሩት ሁለቱ ተቀናቃኞች እስካሁን ባለው ቆጠራ ከ1 በመቶ ያነሰ ድምጽ ነው ያገኙት።
ፕሬዚዳንት ካጋሜ በፓርቲያቸው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ዋና መስሪያ ቤት ባደረጉት ንግግር ሩዋንዳውያን በሳቸው ላይ ስለጣሉት እምነት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
“ 100 በመቶ ብናሸንፍ እንኳን እነዚህ አኃዞች ብቻ አይደሉም። መሰረታዊ የሚባለውን የህዝቡን እምነት የሚያሳዩ ናቸው” ሲሉ ነው ካጋሜ የገለጹት
ከእሳቸው ጋር የተወዳደሩት ተቀናቃኞቻቸው የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ ፍራንክ ሃቢኔዛ 0.53 በመቶ እንዲሁም ጋዜጠኛ እና ደራሲ ፊሊፕ ምፓይማና 0.53 ድምጾችን አግኝተዋል።
የመጀመሪያው ውጤት ከአራት ቀናት በኋላ የሚነገር ሲሆን የመጨረሻው ውጤት ሐምሌ 20/ 2016 ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ የማሸነፋቸው ውጤት ምንም አያስደንቅም።
ከዚህ በፊት በነበረው የአውሮፓውያኑ 2017 ምርጫ ተመሳሳይ እጩዎች ተሳትፈው ካጋሜ በ98.8 ድምጽ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ምርጫ ካጋሜን በሰላ በመተቸት የሚታወቁት ዳያን ርዊጋራን ጨምሮ ቢያንስ ሶስት እጩ ተወዳዳሪዎች ከፉክክሩ እንዲወጡ ተደርገዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ በምርጫው ከ9.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ፣ 98 በመራጮች ድምጽ መስጠታቸውን አስታውቋል።
በዚህ ምርጫ ለፕሬዚዳንቱ እና 53 ህግ አውጭዎች ድምጽ ሰጥተዋል።
ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለአካል ጉዳተኞች የታሰቡ ልዩ የፓርላማ መቀመጫዎች ምርጫ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል። ካጋሜ ከአውሮፓውያኑ 1994 የሩዋንዳ የዘር ፍጅት በኋላ በመሪነት ስፍራ የተቀመጡ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2000 በኋላም በፕሬዚዳንትነት ቀጥለዋል።
ደጋፊዎቻቸው በአገሪቷ ያለውን የምጣኔ ኃብት በማሳደግ እንዲሁም ያለውን የብሔር ክፍፍል አንድነት በማምጣት ቢያወድሷቸውም የመብት ተሟጋቾች ነጻነትን በመገደብ የሚወቅሷቸው መሪ ናቸው ካጋሜ።