የናሳ መንኩራኩር 6.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ወደ ፀሐይ በመጠጋት ታሪክ ሠራች

ናሳ ያነሳው የፀሐይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, መንኩራኩሯ በሰዓት 692 ሺህ ኪ.ሜ. በመጓዝ 980 ሴልሲዬስ የሆነ ሙቀት ተቋቁማ አልፋለች

የናሳ መንኩራኩር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሙቀት በመቋቋም ወደ ፀሐይ መጠጋቷ ተሰማ።

ፓርከር ሶላር ፕሮብ የተሰኘችው መንኩራኩር ሐሙስ ምሽት ምልክት በማሳየት የፀሐይን ሙቀት ተቋቁሟ መጠጋት መቻሉን አሳውቃለች።

ናሳ እንዳስታወቀው መንኩራኩሯ ከፀሐይ 6.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሽከርከር እንደቻለች አሳውቋል።

ፓርከር ሶላር ፕሮብ ለቀናት ከግኝኑት ውጭ ሆና መቆየቷ የናሳ ሳይንቲስቶችን አሳስቦ ነበር።

መንኩራኩር የፀሐይን ከፍተኛ ሙቀት እና ጨረር መቋቋም መቻሏ ፀሐይ እንዴት ነው የምትሠራው የሚለውን ለመረዳት ጠቀሜታ እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የናሳ ድረ-ገፅ መረጃ እንደሚጠቁመው መንኩራኩሯ 692 ሺህ ኪሎ ሜትር በሰዓት በመጓዝ 980 ሴልሲዬስ የሆነ ሙቀት ተቋቁማ አልፋለች።

የአሜሪካው የሕዋ ምርምር ተቋም መንኩራኩር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ ፀሐይ የመጠጋት ሙከራ ያደረገው።

ፓርከር ሶላር ፕሮብ በአውሮፓውያኑ 2018 ነው ወደ ሶላር ሲስተም ማዕከላዊ ክፍል ያቀናችው።

መንኩራኩሯ እስካሁን 21 ጊዜ ፀሐይን የዞረች ሲሆን በየወቅቱ ወደ ፀሐይ ስትጠጋ ቆይታለች። በአውሮፓውያኑ ገና ዋዜማ ግን ከምን ጊዜውም በላይ ወደ ፀሐይ በመጠጋት ታሪክ ፅፋለች።

የናሳ የሳይንስ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ኒኮላ ፎክስ እንደሚሉት ይህ ርቀት በጣም የበዛ ቢመስልም በንፅፅር እጅግ ቅርብ ነው።

"እኛ ከፀሐይ 93 ሚሊዮን ማይል ርቀት ላይ ነው የምንገኘው። ለምሳሌ ፀሐይ እና መሬት አንድ ሜትር ርቀት ላይ ቢሆኑ ፓርከር ሶላር ከፀሐይ 4 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ነው ማለት ነው። ይህን ያህል ቅርብ ነው" ይላሉ።

መንኩራኩሯ ወደ ፀሐይ ስትጠጋ 1400 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ተቋቁማ ነው። የፀሐይ ሙቀት የመንኩራኩሯን ክፍሎች የማቅለጥ ኃይል አለው።

ፓርከር ሶላር 11.5 ሴንቲሜትር ስፋት ባለው ካርበን-ኮምፖሲት የተሸፈነች ቢሆንም ዓላማዋ ቶሎ ገብቶ መውጣት ነው።

መንኩራኩሯ የሰው ልጆች ከሠሯቸው ቁሶች እጅግ ፈጣን ስትሆን በሰዓት 430 ሺህ ማይል ትጓዛለች። ይህ ማለት ከለንደን ኒው ዮርክ በ30 ሰከንድ እንደመጓዝ ነው።

ፓርከር ሶላር ፕሮብ

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, ፓርከር ሶላር ፕሮብ በአውሮፓውያኑ 2018 ነው ወደ ሶላር ሲስተም ማዕከላዊ ክፍል ያቀናችው

ሳይንቲስቶች፣ መንኩራኩሯ ኮሮና በተባለው በትልቋ ኮከብ የውጭኛው ክፍል አልፋ ለዘመናት ያልተፈታ ጥያቄ ምላሽ ታስገኛለች የሚል ተስፋ አላቸው።

"ኮሮና በጣም በጣም ሞቃት ነው። ለምን እንዲህ ሞቃት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም" ይላሉ የፊፍዝ ሰታር ላብስ የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጄኒፈር ሚላርድ።

"የፀሐይ ሙቀት 6 ሺህ ሴልሺየስ አካባቢ ነው። ነገር ግን ኮሮና የተባለው የውጭኛው ክፍል በፀሐይ ግርዶሽ ጊዜ የምናየው ሲሆን ሚሊዮን ዲግሪዎች ሊደርስ ይችላል። የሚገኘው ከፀሐይ ራቅ ብሎ ነው። እንዴት ነው ይህ ከባቢ ሞቃት የሚሆነው?"

ከዚህ በተጨማሪ ሳይንቲስቶች 'ሶላር ዊንድን' ለመረዳት ሙከራ ያደርጋሉ። ሶላር ዊንድ ከኮሮና የሚመነጭ ነው።

ይህ ሶላር ዊንድ ከመሬት 'ማግኔቲክ ፊልድ' ጋር ሲዋሀድ አውሮራ የተባለውን ሰማይ ላይ የሚያበራ ብርሃን ይሰጣል።

ይህ የሕዋ የአየር ሁኔታ የተባለ ሒደት ኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን፣ ኤሌክትሮኒክስ እና የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓቶችን ሊያውክ ይችላል።

"ሐይን መረዳት፣ ሒደቱን ማወቅ፣ የሕዋ የአየር ሁኔታ እና ሶላር ዊንድን መገንዘብ መሬት ላይ ለምንኖር ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ ዶ/ር ሚላርድ።