የህንድ የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ መሐንዲስ የሚባሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲንግ አረፉ

 ማንሞሃን ሲንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህንድን የምጣኔ ኃብት በማሻሻሉ ዘርፍ ቁልፍ ሚና የነበራቸው እና አገሪቷን ለረጅም ጊዜ የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ በ92 ዓመታቸው አረፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓውያኑ 2004- 2014 ፣ ለአስር ዓመታት ህንድን የመሩ ሲሆን የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት የሊበራል ዘርፉን እንዲከተል ስር ነቀል ማሻሻያዎችን አድርገዋል።

የጤንነታቸው ሁኔታ መዳከሙን ተከትሎ በመዲናዋ ደልሂ በሚገኝ ሆስፒታል ለህክምና ገብተው እንደነበር ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ህልፈተ ህይወታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ "ህንድ ትልቅ ስፍራ ያለውን መሪዋን በማጣቷ አዝናለች" ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ሞዲ ባገኟቸውም ወቅቶች "ጥበብ እና ትህትናቸው ሁልጊዜም ይታይበት" እንደነበር ጠቅሰው በመሪነት ዘመናቸው "የሰዎችን ህይወት ለማሻሻል ሰፊ ጥረት አድርጓል" ሲሉ ዘክረዋቸዋል።

ከሞዲ በተጨማሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራጂቭ ጋንዲ ልጅ እና ኮንግረስ የተሰኘው ፓርቲ አባል የሆኑት ፕሪያንካ ጋንዲ "እስከ መጨረሻው ድረስ በእውነት በእኩልነት የሚያምን፣ ብልህ፣ ጠንካራ እና ደፋር ነበሩ" ብላለች።

ኮንግረስ ፓርቲን የሚመሩት ወንድማቸው ራሁል በበኩላቸው "መካሪየን እና አርዓያዬን አጣሁ" ሲሉ ገልጸዋል።

ሲንግ የህንድ የመጀመሪያው መሪ ከሆኑት ጃዋሃርላል ኔህሩ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በድጋሚ የተመረጡ መሪ ሲሆኑ የሃገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን የተቆጣጠሩ የመጀመሪያው የሲክ እምነት ተከታይ ናቸው።

በስልጣን ዘመናቸው ወቅት በአውሮፓውያኑ 1985 በተነሰው ግርግር 3 ሺህ የሚጠጉ የሲክ እምነት ተከታዮች መገደላቸውን አስመልክቶ በፓርላማ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ነገር ግን በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው አስተዳደራቸው በበርካታ የሙስና ወንጀሎች ተከሷል። የሙስና ቅሌቶቹ በአውሮፓውያኑ 2014 በነበረው ምርጫ ኮንግረስ ፓርቲያቸው እንዲሸነፍ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ናቸው።

ሲንግ በህንዷ ፑንጃብ ግዛት በአውሮፓውያኑ 1932 ነው የተወለዱት። የትውልድ ስፍራቸው መብራትም ሆነ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አልነበራትም።

በፑንጃብ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በካምብሪጅ እና ፒኤችዲያቸውን ደግሞ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል።