በጋዛ ጦርነት ወላጅ አልባ የሆኑት ሕፃናት

ዩኒሴፍ 63 ልጆችን ከወላጆቻቸው ወይም ጠባቂዎቻቸው ጋር ማገናኘት ችሏል
የምስሉ መግለጫ, ዩኒሴፍ 63 ልጆችን ከወላጆቻቸው ወይም ጠባቂዎቻቸው ጋር ማገናኘት ችሏል

በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው አል-ማውሲ ጊዜያዊ መጠለያ ልጆች ይጫወታሉ፣ ይስቃሉ። አያታቸው ካውታር አል-ማስሪ "ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ነበር። ለግድያና ጥፋት ተጋልጠው ቆይተዋል" ይላሉ።

ከስድስት ሳምንት በፊት በእስራኤል የአየር ድብደባ ቤታቸውን አጥተዋል።

ቤታቸው የሚገኘው ቢት ላሂያ አካባቢ ነበር። በጥቃቱ የልጆቹ ወላጆች ሞተዋል።

ከልጆቹ አንዱ ጀማል ነው። ገና አንድ ዓመቱ ሲሆን ወላጆቹን አጥቷል።

እህትማማቾቹ ልጆች ማሪያ፣ ጃና እና ዘይና የጀማል አክስት ልጆች ናቸው። ዕድሜያቸው ከሁለት እስከ ዘጠኝ ነው። እናታቸውን በጥቃቱ አጥተዋል። አባታቸው ከዓመት በፊት በእስራኤል ኃይሎች ታስሯል።

ከጥቃቱ የተረፉት ልጆች ከቤት ፍርስራሽ ሥር ሲወጡ ተጎድተው ነበር።

የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከ14,500 በላይ ሕጻናት ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተጎድተዋል። 17,000 የሚጠጉ ሕጻናት ወላጆቻቸውን አጥተዋል ወይም ከወላጆቻቸው ጋር ተጠፋፍተዋል።

የተወሰኑት ጨቅላ ስለሆኑና ስማቸው ስለማይታወቅ ማንነታቸው አልተለየም።

በአየር ጥቃት፣ በፍንዳታ፣ መፈናቀልና ቀውስ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) 63 ልጆችን ከወላጆቻቸው ወይም ጠባቂዎቻቸው ጋር ማገናኘት ችሏል።

ቢቢሲ የማስሪ ቤተሰብ ልጆችን ታሪክ ተከታትሏል።

አያታቸው ካውታር አል-ማስሪ "በመመለሳቸው የተሰማኝን ደስታ መግለጽ ይከብደኛል። የተመለሱት ግን ያለ ወላጆቻቸው መሆኑ ደስታዬን ያጨልመዋል" ይላሉ።

አያትየው በአየር ጥቃቱ ሁሉም ቤተሰቦቻቸው መገደላቸውን ነበር የሰሙት። በወቅቱ አጥብቀው ይፀልዩ ነበር። ሦስት የልጅ ልጆቻቸው በሕይወት መትረፋቸውን አወቁ።

የልጅ ልጆቹን አያትየው ወሰዷቸው።

"ናፍቀውኝ ነበር። ወደ ደቡብ አካባቢ ሄጄ ራሴው ባመጣቸው ተመኘሁ። ፈጣሪ የፈቀደው ሆነ" ይላሉ።

እስራኤል ከዓመት በላይ ደቡባዊውን የጋዛ ክፍል ከተቀረው የጋዛ ሰርጥ ለይታለች።

የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች በልዩ ትብብር ካልሆነ በስተቀር የእስራኤልን ወታደራዊ ክልል ማለፍ አይችሉም።

የማስሪ የልጅ ልጆች ደኅንነት በዩኒሴፍ ከተረጋገጠ በኋላ ከአያታቸው ጋር እንዲገናኙ ተደረገ።

አራቱም ልጆች ምርመራ ሲደረግላቸው ዘመዶቻቸው እየተንከባከቧቸው ነበር።

ዩኒሴፍ ለምርመራ ሲወስዳቸው ቤተሰቦቹ እንዴት በለቅሶ እንደተሰናበቷቸው ድርጅቱ በቪድዮ ቀርጾ አስቀምጧል።

ከጋዛ ተነስቶ ለልጆቹ ምርመራ እስከሚደረገብት ዲር አል-ባላህ ድረስ ያለውን አጭር መንገድ ለማቋረጥ የእስራኤል ፍተሻ ማለፍ ግድ ነው።

መኪና ለመንዳት ከባድ ነው። ጦርነቱን ማለፍም ቀላል አይደለም። ሆኖም ዩኒሴፍ ልጆችን ከወላጆቻቸው ማገናኘትን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይገልጻል።

ጀማል ገና አንድ ዓመቱ ሲሆን ወላጆቹን አጥቷል
የምስሉ መግለጫ, ጀማል ገና አንድ ዓመቱ ሲሆን ወላጆቹን አጥቷል

የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ሮዛሊና ቦለን "ብዙ ፈተና ነው ያለው። ግን እነዚህ ልጆች አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው። በሥነ ልቦናም በአካልም ተጎድተዋል። ለማገገም ጊዜ ይስዳል። ከወላጆቻቸው ወይም ከሌላ የቤተሰብ አባል ጋር መገናኘታቸው ትልቅ ዕድል ነው" ትላለች።

ማስሪ የልጅ ልጆቻቸው እንደሚመጡ ከዩኒሴፍ ተደውሎ የተነገራቸውን ቀን አይረሱትም። ለ14 ወራት የልጅ ልጆቻቸውን አላዩም ነበር።

"ማንን ቀድሜ እንደማቅፍ ግራ ገባኝ። መጀመሪያ ጀናን ከዛ ዘይናን አቀፍኳቸው። ሳምኳቸው። የልጄ ልጆች ኩኮ ብለው ነበር የሚጠሩኝ። ዘይና ገና መናገር ባትጀምርም ቅጽል ስሜን ግን ታውቀው ነበር። ኮኮ ነሽ? አንቺን ለማግኘት ነው የመጣነው? ብላ ደጋግማ ጠየቀችኝ። ኮኮ መሆኔን ስነግራት ጉዳት እንደማይደርስባት አውቃ እፎይታ ተሰማት።"

ቤተሰቡ የተለያየው ጦርነቱ ሲጀመር ነበር።

የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የእስራኤል ጦር የእግረኛ ወረራ ለማድረግ 1.1 ሚሊዮን የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል።

የማስሪ ልጆች ወደ ራፋህ ሸሹ። ሁለቱ ልጆቿ ረመዳን እና ሐምዛ ግን መኪና አጥተው ሳይጓዙ ቀሩ። የአንደኛው ልጇ ባለቤት ነፍሰ ጡር ነበረች። ትንንሽ ልጆችም ነበሯት።

ሐምዛ በእስራኤል ኃይሎች ታስሯል። ቤተሰቡ እንደሚለው ሐምዛ አርሶ አደር ሲሆን በፖለቲካ ውስጥም ተሳትፎ የለውም።

ቢቢሲ ስለ ሐምዛ ከእስራኤል መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

እስራኤል በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎችን አስራለች። በሽብር መጠርጠራቸውን ትገልጻለች።

ማስሪ "እጣ ፈንታችን ነው። ቤታችንን፣ መሬታችንን፣ የምንወዳቸውን ሰዎች አጥተናል። በሰሜንና ደቡብ ተከፍለናል" ይላሉ።

በርካቶች የጠፉባቸውን ቤተሰቦች ፍለጋ ወደ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ይሄዳሉ።

የጠፉ ሰዎችን ለማግኘት የሆስፒታል መረጃን ጨምሮ የታገቱ ሰዎችን ዝርዝርና ሌሎችም ሰነዶችን ማገላበጥ ይጠይቃል።

እስካሁን ከ8,300 በላይ ሰዎች በጥፋታቸው ለቀይ መስቀል ተገልጿል። ጉዳያቸው እልባት ያገኘው 2,100 ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው የተቀላቀሉ ውስን ናቸው።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኛ ሳራ ዴቪስ "ሰዎች ግራ ገብቷቸዋል። ቤተሰቦቻቸው ይኑሩ ይሙቱ ወይ ተጎድተው ሆስፒታል ይሁኑ አልያም ከፍርስራሽ ሥር ታፍነው እንደሆነም አያውቁም። መልሰው ቤተሰቦቻቸውን ያገኙ እንደሆነ እርግጠኛ አይደሉም" ትላለች።

ሕሙማን ከጠፉ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ረገድ ሐኪሞችም ሚና አላቸው።

ከአንድ ዓመት በፊት ቢቢሲ የቀረጸው ቪድዮ እናቷ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደለችባት እናት በቀዶ ሕክምና ስትወለድ ያሳያል።

ሐኪሞች ልጅቷን "የሃና አቡ አምሻ ልጅ" ብለው መረጃዋን አስቀምጠው ነበር። ዘመዶቿ አንድ ቀን መጥተው ይወስዷታል ብለው ተስፋ አድርገዋል።

በዲር አል-ባላህ የሚገኘው የአል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል ለቢቢሲ እንደገለጸው ልጅቷ ከአባቷ ጋር ተገናኝታ ጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።

ማስሪ እና የልጅ ልጆቻቸው
የምስሉ መግለጫ, ማስሪ እና የልጅ ልጆቻቸው

ማስሪና የልጅ ልጆቻቸው ከተገናኙ በኋላ በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

የእርዳታ አቅርቦት ውስን ቢሆንም ዩኒሴፍ ተጨማሪ ምግብና መድኃኒት እያቀረበላቸው ነው።

ልጆቹ አሁን ቅዝቃዜውን ለመቋቋም የሚለብሱት አላቸው።

በርካታ ሕጻናት በቅዝቃዜ ሞተዋል።

ማስሪ የልጅ ልጆቻቸውን ማግኘታቸው ቢያስደስታቸውም አሁንም ስለ ደኅንነታቸው ስጋት አላቸው። እንዴት የአእምሮ ጤናቸውን መጠበቅ እንደሚችሉም ይጨነቃሉ።

"ድንጋጤ ውስጥ ናቸው። ስለ ጦርነቱ ባለማውራት ልናረሳሳቸው ብንሞክርም ትክዝ ብለው በሐሳብ ይጠፋሉ። ሲመሽ ይፈራሉ። 'አውሮፕላን መጥቶ ይደበድበናል' ይላሉ። እስከሚነጋ ይጠብቃሉ። ሲነጋ ነው ደኅና እንደሆኑ የሚያምኑት።"

ሕልማቸው የተኩስ አቁም ተደርጊ ማየት ነው። የልጅ ልጆቻቸው ሕይወትን እንዲገነቡ ይሻሉ። የጠፋ ትውልድ አካል መሆንን አይፈልጉም።