የአማራ ክልል ዳኞች ያለመታሰር እና ያለመከሰስ ከለላ ተሰጣቸው

ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ ዳኞች
የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጉባኤ የጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን እንዲሁም የከፍተኛ እና ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ሹመትን አጽድቋል

በአማራ ክልል የሚገኙ ዳኞች "እጅ ከፍንጅ ካልተገኙ በቀር" እንዳይያዙ እና እንዳይከሰሱ የሚደነግግ አዋጅ በክልሉ ምክር ቤት ጸቀደ። አዋጁ፤ ዳኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ "ለፈጸሙት ወይም ሳይፈጽሙት ለቀሩት ድርጊት" ክስ ሊቀርብባቸው እንዳማይችልም ይደነግጋል።

ለአማራ ክልል ዳኞች ያለመከሰስ ከለላን የሰጠው "የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ" የተሰኘው አዋጅ ነው። ባለፈው ሳምንት ለአራት ቀናት ጉባኤውን ያደረገው የአማራ ክልል ምክር ቤት ይህንን አዋጅ ያጸደቀው አርብ የካቲት 7/2017 ዓ.ም. በነበረው የመጨረሻ ቀን ውሎው ነው።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንን አዋጅ ያዘጋጀው፤ የፍትህ ሥርዓቱ ላይ የተጀመሩ "የለውጥ ሥራዎችን በሕግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ" እንደሆነ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከጠቀሷቸው "የለውጥ ሥራዎች" መካከል የዳኝነት አገልግሎት "ዲጂታላይዜሽን" ይገኝበታል።

ይህንኑ የ"ዲጂታላይዜሽን" ሀሳብ የሚያነሳው አዲሱ አዋጅ፤ ፍርድ ቤቶች አቤቱታዎች፣ ክርክሮች እንዲሁም ምስክር የመስማት ሂደቶች "በኤሌክትሮኒክ፣ በድረ-ገጽ፣ በቪድዮ ኮንፈረንስ ወይም በሌላ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ" እንዲካሄዱ ይፈቅዳል።

"የክልሉ የዳኝነት ሥርዓት ከማናቸውም ውስጣዊ እና ውጫዊ ተጽዕኖ እንዲሁም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ እንዲሠራ" የማስቻል ዓላማ ያለው ይህ አዋጅ፤ ካስተዋወቃቸው አዳዲስ ጉዳዮች መካከል ጉልህ ሆኖ የሚጠቀሰው ለክልሉ ዳኞች የሰጠው ከላላ ነው።

በዚህ አዋጅ የተካተተው የዳኞች ከለላ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በ2007 እና 2014 ዓ.ም. ሁለት ጊዜ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበርም በክልሉ የሚገኙ ዳኞች ይህ ከለላ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር።

የክልሉ ዳኞች ከዚህ ቀደም ከለላ ያልነበራቸው በመሆኑ "በሰጡት ትዕዛዝ፣ ውሳኔ፣ ብይን" ምክንያት ይታሰሩ እንደነበር የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አሳሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ማኅበሩ ጥቅምት ወር ላይ አውጥቶት በነበረው መግለጫ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የወረዳ ፍርድ ቤት አመራሮችን ጨምሮ 11 ዳኞች ለእስር እንደተዳረጉ አስታውቆ ነበር።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ በማኅበሩ የተነሳውን ሀሳብ ይጋሩታል። "አልፎ አልፎ፤ [ጉዳዩ] በዳኞች አስተዳደር ጉባኤም ሳይታይ [ዳኞች] ጥፋት ፈጽመዋል ብሎ ያመነ የፀጥታ ወይም የአስተዳደር አካል የማሰር እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ" ብለዋል።

ይህ ዓይነቱ እስር፤ "ከዳኝነት እና ተቋማዊ ነጻነት ጋር" የሚያያዝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "የዳኝነት ነጻነትን በእጅጉ የሚጎዳ" መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ ለክልሉ ምክር ቤት ማሳየት እንዲሁም ይህ ከለላ "ለግለሰብ ዳኞች ተብሎ የሚሰጥ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ ለሕዝብ ጥቅም" የሚደረግ መሆኑን ማስረዳት እንደተቻለ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት
የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ለዳኞች ከለላ ለመስጠት የቀረቡለትን ጥያቄዎች ውድቅ አድርጎ ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ ቀደም ይህንን ከለላ ውድቅ አድርጎ የነበረው የክልሉ ምክር ቤትም በዚህ ሀሳብ "በማመኑ እና የክልሉ መንግሥትም ድጋፉን በመስጠቱ" አዋጁ እንደጸደቀም አቶ ዓለምአንተ አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት የጸደቀው ይህ የፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ፤ ማንኛውም የክልሉ ዳኛ "በዳኝነት ሥራ ለፈጸመው ወይም ሳይፈጽም ለቀረው ድርጊት ማንኛውም የፍትሐ ብሔር ወይም የወንጀል ክስ ሊቀርብበት" እንደማይችል ደንግጓል።

ዳኞች "ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተገኙ በስተቀር" ያለ ክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ፈቃድ እንደማይያዙ እና እንደማይከሰሱም አስፍሯል።

አዋጁ፤ የክልሉን ፍርድ ቤት ለሚመሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትም ተመሳሳይ መብት ሰጥቷል። ክሱ፤ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸውን የሚመለከት ሲሆን ያለመከሰስ እንዲሁም ያለመያዝ ከለላው የሚነሳው በክልሉ ምክር ቤት እንደሆነ አዋጁ ላይ ተጠቅሷል።

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፤ በዳኞች ወይም በፍርድ ቤቱ አመራሮች "የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ካለው" የተሰጠው ከለላ እንዲነሳ ሊጠይቅ እንደሚችል አዋጁ ያስረዳል። በአዋጁ መሠረት፤ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ዳኞችን የተመለከተ ሲሆን ይህንን ጥያቄ የሚያቀርበው ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤው ሲሆን የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸውን የተመለከተ ሲሆን ደግሞ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ነው።

ፍትሕ ቢሮው አንድ ዳኛ "ከዳኝነት ሥራው ወይም ከኃላፊነቱ ጋር በተያያዘ ከባድ ወንጀል" መፈጸሙን በተመለከተ "ለጥርጣሬ በቂ መነሻ ማስረጃ" ካቀረበ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤው "በጥያቄው ላይ ወዲያውኑ ውሳኔ" እንደሚሰጥ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

አዋጁ እንደሚያስረዳው፤ ያለመያዝ ወይም ያለመከሰስ ከከላቸው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበባቸው ዳኞች "እንደነገሩ ሁኔታ በአካል በመቅረብ ወይም በጽሑፍ በመላክ" መልስ የመስጠት መብት ይኖራቸዋል። ይሁንና ዳኞች መልስ አለመስጠታቸው በጉዳያቸው ላይ "ውሳኔ ከመስጠት እንደማያግድ" ተደንግጓል።

በተጨማሪም አዋጁ የዳኞች "መልስ የማቅረብ መብት ታልፎ ከለላው ሊነሳ" የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አስቀምጧል። በአዋጁ መሠረት ይህ መብት የሚታለፈው ዳኛው "የተጠረጠረበትን ወንጀል ስለመፈጸሙ ግልጽ እና በቂ በሆነ ሁኔታ የሚያሳይ" ሲሆን እንዲሁም "የዳኛውን ምላሽ መጠበቅ በምርመራ ሥራው እና በማስረጃ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ሊፈጥር የሚችል ጉዳት ስለመኖሩ አሳማኝ ሁኔታ ከቀረበ" ነው።

አዲሱ አዋጅ ላይ የተካተተው የዳኞች ከለላ ጉዳይ እንዲደነገግ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው የአማራ ክልል የዳኞች ማኅበር የሕጉን መጽደቅ "በጣም በበጎ መልኩ" እንደሚቀበለው አስታውቋል። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህ የከለላ መብት እንዲሰጥ "ከፍተኛ ትግል" ማድረግ በመጥቀስ አድንቀዋል።

መስከረም፣ ጥቅምት እና ኅዳር ላይ ተከታታይ የሆኑ እስሮች ከተፈጸመባቸው የክልሉ ዳኞች "አብዛኞቹ" እንደተፈቱም አቶ ብርሃኑ ጠቅሰዋል። ይሁንና አሁንም "አምስት ገደማ ዳኞች" በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "እስከ ቅርብ ቀን ድረስ አልፎ አልፎ" ዳኞች ላይ እስር መፈጸሙን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ ዓለምአንተም በበኩላቸው ከዳኞች እስር ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች "በአብዛኛው መፈታታቸውን" ተናግረዋል። "በዘላቂነት መፍትሔ የሚሰጡ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው፣ በምክር ቤቱ ጸድቀዋል" ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ "አንዳንድ የቀረቡ ጉዳዮች ቢኖሩም የክልሉ መንግሥት ቁርጠኝነት የወሰደበት እና የእኛም የቅርብ ክትትል ያለው ነው" ብለዋል።