ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ላይ ለመድረስ የመጀመሪያውን ዙር የቴክኒክ ድርድር አካሄዱ

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቱርኩ ፕሬዚዳንት አሸማጋይነት ታኅሣሥ ላይ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Turkiye Today

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቱርኩ ፕሬዚዳንት አሸማጋይነት ታኅሣሥ ላይ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት

ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተደረሰ የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የመጀመሪያ ዙር የቴክኒክ ድርድር የካቲት 11/2017 ዓ.ም. በቱርክ መዲና አንካራ አካሄዱ።

ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ልዩነታቸውን በሰላም ቋጭተው ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት አሸማጋይ የሆነችው ቱርክ፤ የቴክኒክ ድርድሩ የአንካራውን ስምምነት የተከተለ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ አመልክታለች።

በቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም. የተደረሰው የአንካራ ስምምነት ለአንድ ዓመት ያህል በቃላት ጦርነት ሲወዛገቡ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ለመፍታት እንዲቀመጡ ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚያረጋግጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ የምታገኝበትን ስምምነት መድረስ የሚያስችል የቴክኒካል ድርድሮች እንደሚጀምሩ ተነጋግረው ነበር።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን በመሩት በዚህ የቴክኒክ ድርድር ኢትዮጵያን ወክለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ እንዲሁም ከሶማሊያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሐመድ ኦማር ተገኝተዋል።

በመጀመሪያው ዙር የቴክኒክ ድርድር ሁለቱም ልዑካን የአንካራው ስምምነት መፈጸም ላይ ያላቸን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነው ተብሏል።

ልዑካኑ የአገራቱ መሪዎች በአንካራ ስምምነት ላይ ያስቀመጡትን ራዕይ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲሁም ለጋራ የዘላቂ ልማት ተጠቃሚነት መሠረት ለመጣል ተጨባጭ ሥራ መጀመራቸውን የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አክሏል።

ቀጣዩ የቴክኒክ ድርድርም ለመጋቢት 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በቱርኩ ፕሬዚዳንት አሸማጋይነት ታህሳስ ወር ላይ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በቱርኩ ፕሬዚዳንት አሸማጋይነት ታህሳስ ወር ላይ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሠረት፤ "ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።"

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ "የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ" ሲል ያትታል።

በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ውስጥ ላለማካተት አሳልፋው የነበረውን ውሳኔ ልትቀለብስ እና በተልዕኮው ለማካተት እያጤነች እንደሆነ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት እና እራሷን ነጻ ሀገር ነኝ ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች ጦሯ በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ እንደማይካተት የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ውጥረት ያረገበውን የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ግንኙነታቸውን ለማደስ መወያየታቸው ይታወሳል።

መሪዎቹ ባለፈው አንድ ዓመት ተቀዛቅዞ የነበረውን "ግንኙነታቸውን ለማደስ በሁለቱ ሀገራት መዲናዎች በሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ ተወካዮች በኩል ለማጠናከር እንደተስማሙ" በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር መግባቢያ ስምምነትን በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የያዘው ነጻነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ መንግሥት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መካከል ቱርክ ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት በሚመለከት ሶማሊላንድ ሌላ ሀገር በመሆኗ ይህ ጉዳይ የሚመለከታት እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ፋራህ አብዲ "የፈረሙት ሁለቱ አገራት ናቸው፣ እኛ ሶማሊላንድ ነን። ሁለቱ ወንድማማች አገራት የራሳቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት። እነሱ ተነጋግረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተለመደ ነገር ነው። እኛን የሚመለከት አይደለም" ሲሉ መናገራቸው ቢቢሲ ሶማሊ ዘግቧል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በሶማሊላንድ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ያለበትን ሁኔታን በተመለከተ ሲናገሩ አዲሱ መንግሥት ገና ሥልጣን መረከቡ በመሆኑ ጊዜ ወስዶ እንደሚመለከተው እና የሚወስንበት መሆኑን ገልጸዋል።