ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቡናን ቦታ ለመያዝ እየተንደረደረ ያለው የኢትዮጵያ አቮካዶ
ከሦስት ዓመት በፊት በምሥራቅ ሸዋ አድአ ወረዳ ደንካካ ገበሬ ማኅበር የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳቸው ላይ አቮካዶ ተክለው የውጪ ምንዛሬ እንደሚያገኙ ሲናገራቸው ሁሉም በአንድ ልብ አልተቀበሉትም ነበር።
በማሳቸው ላይ ጤፍ እና ስንዴ የሚያበቅሉት ገበሬዎች እንደ አቮካዶ ያለ ቋሚ ተክል ተክሎ የውጪ ምንዛሬ ማለምን ፈጽሞ አስበውት አያውቁም።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ አቮካዶ አምርተው ወደ ውጪ ለመላክ ብቻ ሳይሆን ለምግብነት እንኳ ተጠቅመውት አያውቁም።
የመንግሥት ተወካዮች ወደ ቀበሌያቸው መጥተው የአቮካዶ ችግኝ እንዲተክሉ ሲነግሯቸው ሃሳቡን ተቀብለው ተግባራዊ ካደረጉ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ አቶ ሲሳይ መርሻ ናቸው።
አቶ ሲሳይ አቮካዶ ማምረት ከጀመሩ ሦስት ዓመት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
“አቮካዶ ከዚህ በፊት ምንነቱን እንኳ አላውቅም ነበር፤ ሱቅ ነበር የማየው። ቁም ነገር ነው ብዬ ገዝቼ አላውቅም። ልጆቹ እንኳ ገበያ ሲሄዱ ብርቱካን ይገዛሉ እንጂ አቮካዶ ገዝተው አያውቁም።”
አርሶ አደሩ ከዓመት ዓመት ጤፍ እና ስንዴ ዘርተው ለቤታቸውም ለገበያም ስለሚያቀርቡ አቮካዶ ተክዬ ምን እንበላለን ሲሉ ሰግተው እንደነበር አቶ ሲሳይ ያስታውሳሉ።
ስጋቱ ግን የአቶ ሲሳይ ብቻ አልነበረም “ይህ አቮካዶ እውነት ገንዘብ ያመጣልናል? እህል ብንዘራ በዓመት ይደርስልናል። ይህ ደግሞ በየዓመቱ አይደርስም የሚለው የአርሶ አደሮቹ ስጋት ነበር” ይላሉ።
ከስጋታቸው እንዲወጡ ያደረጋቸው የግብርና ባለሙያዎች ከአቮካዶ ችግኝ ጎን ለጎን ሌሎች አዝርዕቶችን በመዝራት ምርት ማግኘት እንደሚችሉ ከነገሯቸው በኋላ ነው።
“ባለሙያዎች ይህ አቮካዶ እስኪያድግ ድረስ ከስሩ ማረስ እና መዝራት ትችላላችሁ አሉን። እኔ ሁለት ሄክታር ላይ ነው የተከልኩት። ባለፉት ሦስት ዓመታት መሬቴን ለአቮካዶ ብቻ አላዋልኩትም። በቆሎ፣ ሽንኩርት እና ሌሎች ምርቶችንም አቮካዶው ስር ሳመርት ነበር” ይላሉ አቶ ሲሳይ።
የአካባቢው አርሶ አደሮች አድአ ከሚታወቅበት የጤፍ ምርት በተጨማሪ ሽንኩርት እና ድንች በማምረት ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ2021 (እኤአ) ብቻ ከኦሮሚያ ወደ ስፔን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ 18 ቶን አቮካዶ ተልኳል።
ኤጀንሲው ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የአቮካዶ ምርት በስፋት እንዲመረትና ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን በድረገፁ ላይ አስፍሯል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቮካዶ ምርትን ለመጨመር እና ጥራቱን በማሻሻል ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ ነው።
የግብርና ሚኒስቴር፣ ከእስራኤል መንግሥት የልማት ድርጅት እና ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስአይዲ) ጋር በመሆን የተለያዩ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ከእነዚህም ዝርያዎች መካከል ከፍተኛ ተመራጭ የሆነው ሃስ (Hass) ከእስራኤል በማስመጣት ለአርሶ አደሮች ተከፋፍሏል።
አቮካዶ ቡናን ሊገዳደር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት ጤፍ በማምረት የሚታወቁ የሸዋ አካባቢዎች አሁን በስፋት አቮካዶ ማምረት መጀመራቸው ገልጸው፤ አቮካዶ ከዓመታት በኋላ የቡናን ያህል በወጪ ንግድ ገቢ የማስገኘት አቅም እንዳለው ገልጸው ነበር።
እንደ የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር መረጃ ከሆነ አንድ አርሶ አደር 2600 የቡና ችግኞችን በሄክታር መትከል የሚችል ሲሆን ከዚህም ከ10 እስከ 12 ኩንታል የሚደርስ ምርት ይሰበስባል።
ነገር ግን በሄክታር 416 የአቮካዶ ችግኞችን መትከል የሚቻል ሲሆን በሄክታርም እስከ 20 ኩንታል ማግኘት ይቻላል።
ይህንን ንጽጽርም በመጠቀም ኢትዮጵያ ከአንድ ሄክታር ቡና ከምታገኘው የውጪ ምንዛሪ በተሻለ ከአቮካዶ የተሻለ ማግኘት ትችላለች ይላል።
የኢትዮጵያ መልከአ ምድር እና አየር ጠባይ የተለያዩ አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎች ለማብቀል ምቹ ነው።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ አቮካዶ አብቃይ ከሆኑ 10 ቀዳሚ አገራት ተርታ ትገኛለች።
ዓለም በመጪው 20 ዓመታት ሊኖራት የሚችለው የአቮካዶ ምርት ፍላጎት ትንበያም የሚያሳየው እየጨመረ እንደሚሄድ ነው።
ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደር አቶ ጌቱ ብሩ በበኩላቸው አቮካዶ ማምረት ላይ ከተሰማሩ መካከል አንዱ ናቸው።
ላለፉት ሦስት ዓመታት አንድ ሄክታር መሬት ላይ አቮካዶ ተክለው ሲንከባከቡ እንደነበር ገልጸው፤ ከአቮካዶ እና ፓፓያ ጎን ለጎን በቆሎ ተክለው ምርት ለመሰብሰብ እየጠበቁ ነው።
አቶ ጌቱ እና አቶ ሲሳይ መንግሥት ባመቻቸላቸው የንግድ መስመር ያመረቱትን አቮካዶ ወደ ውጪ አገር በመላክ ገቢ ለማግኘት ቀናት እየቆጠሩ ነው።
አቶ ሲሳይ እና አቶ ጌቱ አቮካዶ ተክለው ምርት ለመሰብሰብ ይዘጋጁ እንጂ በአካባቢያቸው ጤፍና ስንዴ ማምረት ይሻለናል ያሉ አርሶ አደሮች አሁንም አሉ።
የእነርሱ ውጤታማ መሆን ሃሳባቸውን እያስቀየራቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ “. . .አሁን ምርታችንን በጥሩ ደረጃ ላይ ስላለ ሃሳባቸውን የቀየሩ አሉ። ወደ ውጪ አገር መላክ ስንጀመር ሌሎችም ሃሳባቸውን ይቀይራሉ ብለን እናምናለን” ይላሉ።
የአቮካዶ ችግኝ መትከል ሲጀመር ከእስራኤል የተሻሻሉ ዝርያዎች የመጡ ሲሆን፣ አሁን አርሶ አደሮቹ ከምርቱ በተጨማሪ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በማባዛት ላይ እንደሚገኙም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም የተሻሻሉ ዝርያዎች በችግኝ ጣብያዎች ውስጥ እየተባዙ ስለሚገኝ ችግኙ ለአርሶ አደሮች ከአገር ውስጥ እየቀረበ መሆኑን የኦሮምያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በኦሮምያ ክልል ብቻ 6229 ሄክታር ላይ አቮካዶ የተተከለ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም ከምሥራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ የመጀመሪያው የአቮካዶ ምርት ወደ ውጪ መላኩን የግብርና ቢሮ ኃላፊው አክለዋል።
“አምና ትንሽ ምርት ለውጪ ገበያ ልከናል። ዘንድሮ ደግሞ 1ሺህ ቶን የሚጠጋ የአቮካዶ ምርት ወደ ውጪ ገበያ እንልካለን ብለን እንጠብቃለን።”
አቶ መሐመድ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በኦሮምያ ክልል ብቻ ወደ 200 ሺህ ቶን አቮካዶ ወደ ውጪ ለመላክ እንዲቻል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል የሚል ዕቅድ አለ።