በፓኪስታን የ13 ዓመቷን የቤት ሰራተኛ 'ቸኮሌት ሰርቃለች' በሚል የገደሉ ጥንዶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በሰሜን ምስራቅ ፓኪስታን የሚኖሩ ጥንዶች በቤት ሰራተኝነት ስታገለግላቸው የነበረችን የ13 ዓመት ታዳጊ 'ቸኮሌት ሰርቃለች' በሚል በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ኢቅራ በመባል የምትጠራው ይህች ታዳጊ፤ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሆስፒታል ስትደርስ በርካታ ጉዳቶች አስተናግዳ ነበር።

የመጀመሪያ ደረጃ የፖሊስ ምርመራ እንደሚያሳየው፤ ታዳጊዋ ከፍተኛ ድብደባ እና እንግልት ደርሶባታል።

ጉዳዩ በፓኪስታን ሰፊ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ #JusticeforIqra የሚል ዘመቻንም አስጀምሯል። የታዳጊዋ ሞት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፓኪስታናውያን በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ እና በቤት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና ጥቃት በተመለከተ እንዲወያዩ እና አንዲከራከሩ አድርጓል።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን የሚመለከቱ ሕጎች በመላ አገሪቱ የተለያዩ ቢሆኑም፤ በፑንጃብ ግዛት ውስጥ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው እንዳይሰሩ ተከልክሏል።

የኢቅራ አባት ሳና ኡላህ "መሞቷን ስሰማ ቅስሜ ሙሉ በሙሉ ተሰበረ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለ ልጃቸው ኢቅራ ከፖሊስ ጥሪ የደረሳቸው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት አንደነበር ገልጸዋል። በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ፣ ኢቅራ ራሷን ስታ አልጋ ላይ ተኝታለች። ከደቂቃዎች በኋላም ሕይወቷ አለፈ።

ኢቅራ በቤት ሰራተኝነት መስራት የጀመረችው ከስምንት ዓመቷ ጀምሮ ነው። የ45 ዓመት ጎልማሳ የሆኑት አርሶ አደር አባቷ፤ እዳ ስላለባቸው ሰርታ ገንዘብ አንድታመጣ እንደላኳት ተናግረዋል።

ኢቅራ በተለያዩ ቤቶች ከሠራች በኋላ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ስምንት ልጆች ላላቸው ጥንዶች ለመሥራት ተቀጠረች። በወር 3000 የኢትዮጵያ ብር ገደማ ($28 ዶላር) ታገኝ እንደነበር ተገልጿል።

የፖሊስ የቅድመ ምርመራ ሪፖርት ፤ ኢቅራ ከአሰሪዎቿ 'ቸኮላት ሰርቃለች' መባሏን እንዲሁም ስቃይ እና ድብደባ እንደደረሰባት መዝግቧል።

ፖሊስ በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጸምባት እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ መኖሩንም ገልጿል። ቢቢሲ ያገኛቸው ምስሎች እና ቪዲዮዎች እግሮቿ እና እጆቿ ላይ ብዙ ስብራት እንዲሁም ጭንቅላቷ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባት ያሳያሉ።

ሙሉ በሙሉ የጉዳቷን መጠን ለመገምገም የአስከሬን ምርመራ የተደረገ ሲሆን ፖሊስ የመጨረሻውን የሕክምና ሪፖርት እየጠበቀ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የመብት ተሟጋቹ ሸህ ባኖ፤ " ልቤ የደም እንባ ያነባል። ስንቶች... ለአነስተኛ ስራ በየቀኑ በቤታቸው ግፍ ይፈጸምባቸዋል?" ሲል በኤክስ ገጹ ላይ ጽፏል። " ድሆች ሴት ልጆቻቸውን በዚህ መንገድ ወደ መቃብር የሚሸኙት እስከ መቼ ነው?" በማለትም ጠይቋል።

ሌሎች ደግሞ ግድያዋ በጣም ቀላል በሆነ ምክንያት የተነሳ መሆኑን በማንሳት ቁጭታቸውን ግለጸዋል።

"በቸኮሌት ምክንያት ሞተች?" አንድ የኤክስ ተጠቃሚ የሰጠው አስተያየት ነበር።

"ይህ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ሀብታሞች ድሆችን ተጠቅመው እንዲጥሉ የሚያስችል ሥርዓት ነጸብራቅ ነው" ሲል ሌላው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ተናግሯል።

የኢቅራ አሰሪዎች ራሺድ ሻፊቅ እና ባለቤቱ ሳና፤ ከቤተሰቡ የቁርዓን መምህር ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል። መምህሩ ኢቅራን ወደ ሆስፒታል አምጥተው ለሆስፒታሉ ሰራተኞች የልጅቷ አባት መሞቱን እና እናቷ በአካባቢው እንደሌለች በመናገር ሄደዋል ተብሏል።

የኢቅራ አባት "በልጄ ሞት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ሲቀጡ ማየት እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ሕዝባዊ ቁጣ ቢቀሰቀስም በተለምዶ ጉዳዮቹ ከፍርድ ቤት ውጪ ይፈታሊ። ተጠርጣሪዎ ላይም በተገቢው ሁኔታ ክስ ሲመሰረት አይታይም።

እ.ኤ.አ. በ 2018 አንድ ዳኛ እና ባለቤታቸው 10 ዓመት የሚሆናት የቤት ሰራተኛቸውን በማሰቃየት ወንጀል ተከስሰው የሦስት ዓመት እስር የተፈረዶባቸው ነበር። በወቅቱ ይህም ድርጊት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

በኋላ ግን የጥንዶቹ ቅጣት ወደ አንድ ዓመት እንዲቀነስ ተደርጓል።

በፓኪስታን ሕግ ተጎጂዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው በበርካታ ከባድ ወንጀሎች የተከሰሱ ወይም ተጠርጣሪዎችን ይቅር የማለት መብት አላቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የተጠረጠረውን ወይንም የተከሰሰውን ግለሰብ "በእግዚአብሔር ስም" ይቅር ማለታቸውን በፍርድ ቤት መግለጽ አለባቸው።

እንደ ሕግ ታዛቢዎች ከሆነ የይቅርታው ዋነኛ መንስኤ ገንዘብ ነው። በሀገሪቱ ለተጎጂዎች መክፈል ሕገወጥ አይደለም።

በፓኪስታን ወደ 3.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በህጻናት የጉልበት ሥራ ተሰማርተዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።

እንደ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ መሰረት በፓኪስታንን 8.5 ሚሊዮን የቤት ሰራተኞችን የሚገኙ ሲሆን ሴቶች እና ወጣት ልጃገረዶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።