ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አደባባይ ያወጡት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር ይገባኛል ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሕይወት ያጠፋ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ከ20 ዓመታት በላይ በጠላትነት ቆይተዋል።
ይህ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በፍጥነት ተቀይሮ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ከማደስ ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን አንድ ለማድረግ ጥረቶችን አድርገዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ጦርነት በተካሄደበት ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረው ህወሓት ከኤርትራ መሪ ጋር የነበረው ግንኙነት ተበላሽቶ በጠላትነት የሚተያዩ እና የየአገራቱን ተቃዋሚዎች በመደገፍ ስማቸው ይነሳል።
በኋላ ላይም በፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ መንግሥትን ወግኖ መሳተፉ ይታወሳል።
በ2010 ዓ.ም. የታደሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግንኙነት ጠንክሮ መሪዎቹ ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አንዳቸው በሌላው አገር ውስጥ አድርገዋል።
በተደጋጋሚ ጉብኝታቸው ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እና ወታደራዊ ተቋማት ሳይቀሩ ጎብኝተዋል። ምንም እንኳ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ሲያድሱ ስለደረሱት ስምምነት እስካሁን የሚታወቅ ነገር ባይኖርም።
የኢትዮጵኣ የውጭ ኡዳይ ሚኒስቴር በየሳምንቱ በሚሰጠው መግለጫ በተደጋጋሚ ከሚነሱት ጥያቄዎች መሃል የሁለቱ አገራት ግንኙነት በምን ላይ ይገኛል የሚል ቢሆንም፤ ግልፅ ምላሽ ሳያገኝ ዛሬ ላይ ደርሷል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት መቀዛቀዝ የጀመረው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ መሆኑ በስፋት ይነገራል።
በሁለቱ አገራት በኩል የነበረውን ግንኙነት የበለጠ የማጠናከሩ ሁኔታንዎችን በተመለከተም ምንም የሚሰማ ነገር የለም።
በትግራይ በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ "ልዩ መልዕክተኛ" ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በአልጀዚራ ላይ ያጋሩት ጽሁፍ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚሳይ ሆኗል።
የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል በተለያዩ መድረኮች የሚገኙት የቀድሞው አምባሳደር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በተለያዩ ወገኖች በማኅበራዊ ሚዲያ እና በውይይቶች ላይ በተዘዋዋሪ ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮችን በቀጥታ በማንሳት፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአካባቢው ሰላም ላይ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን በመጥቀስ ከሰዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያውን ግጭት የማቆም ስምምነት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ብሎም በአካባቢው ላይ ማሳደር ለሚፈልጉት ተጽእኖ እንቅፋት አድርገው እንሚመለከቱት እና ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት ነበራቸው ብለዋል።
እንዲሁም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና በአማራ ክልል ውስጥ ሚሊሺያ እንዲፈጠር አድርገዋል በማለትም የከሰሱም ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ መሆናቸውን በጽሁፋቸው ወቅሰዋል።
ይህንን ክስ በተመለከተ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ምንጭ ከውጭ እንደመጣ ማድረግ እና ኤርትራን መሸሸጊያ የሚያደረግ ነው በማለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ዝርዝር መልስ ሰጥተዋል።
ጠማስታወቂያ ሚኒስትሩ በግል የኤክስ ገጻቸው ላይ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ጽሁፍ በሰጡት ምላሽ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች በእርግጥም በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት መበላሸቱን እንዲሁም የመከዳት ስሜት መኖሩን የሚያመለክቱ ናቸው።
እየተካረረ የመጣው ግንኙነት
ከመገናኛ ብዙኃን ርቀው የቆዩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ባልተለመደ ሁኔታ አልጀዚራ ላይ "በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭት ለማስቀረት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው" በሚል በስማቸው ያወጡት ጽሁፍ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ያለበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት እና ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከ20 ዓመታት በላይ በቆዩበት ጊዜ ሁለቱም ለተቃዋሚዎች ከለላ እና ትጥቅ በመስጠት ይፋዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ፈቅደው እንደነበር ይታወሳል። በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነገሮች ተቀይረው ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኤርትራ ተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች በይፋ አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባቸውን ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ እንዳሉት ደግሞ የኤርትራ መንግሥት የህወሓትን አንድ ወገን እንዲሁም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን በመደገፍ ከሰዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለአገራቸው ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልለስ ላይ የተነሱ ሐሳቦችን በመጥቀስ ለገዢው ፓርቱ ብልጽግና ቅርብ በሆነው ፋና ቴሌቪዥን ላይ ግልጽ ነቀፋ በፕሬዝዳንቱ ላይ መቅረቡ ይታወሳል።
እንዲሁም የአምባሳደር ሙላቱ ተሾመ ጽሁፍ በወጣበት ዕለት ከ50 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ተፈጽሟል የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን ባልተለመደ ሁኔታ ለመዘከር "ፈጽሞ አንረሳውም" የሚል ጽሁፎችን የያዙ ወጣቶች በአስመራ ጎዳና ላይ ሰልፍ አድርገዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዝዳንት በግልጽ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ በመቆም ከግብፅ እና ከሶማሊያ ጋር በመወገን በተቃራኒ የሦስተዮሽ ትብብር መድረክን አሥመራ ላይ መመሥረታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ከኤርትራ አንጻር አሁን ያለውን አቋሙን ባይገልጽም እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች እየተደራረቡ በመሄድ የድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በአንጀዚራ ላይ በጽሁፍ ካንጸባረቁት አመለካከት የተለየ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)
በኢህአዴግ ውስጥ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ የነበረው የኦህዴድ አባል የነበሩት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ስስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸው ድረስ የተማሩት ቻይና ውስጥ ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ከሚኒስትርነት እስከ ፕሬዝዳንትነት በሚደርስ የኃላፊነት ቦታ ላይም ሠርተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የኢኮኖሚ ልማት እና ትብብር ምክትል ሚኒስትር፣ የግብርና ሚኒስትር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም በቻይና፣ በጃፓን፣ በቱርክ እና አዘርባጃን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
ኋላ ላይም ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን በመተካት ወሳኝ የሆነ ሥልጣን በሌለው የአገሪቱ የርዕሰ ብሔርነት ቦታን ይዘው ለአምስት ዓመታት ያህል ሠርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ የሥልጣን ዘመናቸውን አጠናቀው ተሰናብተዋል።
ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክቶች ይዘው ወደ ተለያዩ አገራት ሲያመሩ እንደነበር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ከእነዚህም መካከል በቻይና፣ በጃፓን፣ በኡጋንዳ እና በሶማሊላንድ በተካሄዱ ይፋዊ ዝግጅቶች ላይ የተገኙ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ልዩ መልዕክቶችን ማድረሳቸውም ተዘግቧል።
በተጨማሪም ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) "ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትዎርኪንግ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ድርጅት ማቋቋማቸው ከአራት ዓመት በፊት ተነግሮ ነበር።
ምንም እንኳን ሙላቱ (ዶ/ር) ከመንግሥት በይፋ የተሰጠ ኃላፊነት ስለመኖሩ ባይታወቅም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መልዕክቶች በተደጋጋሚ ወደ ተለያዩ አገራት መሪዎች ከማድረሳቸው ጋር በተያያዘ "ልዩ መልዕክተኛ" እንደሆኑ ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም በተለያዩ መንግሥታዊ ታላላቅ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ከሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ከመታየታቸው አንጻር በመንግሥት ዘንድ ተሰሚነት እንዳላቸው ይታመናል።
የአገሪቱ መሪ ፓርቲ በልፅግና በቅርቡ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያደርግም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ሆነው ታይተዋል።