ከረሃብ የተረፉት ኬንያውያን ራስን በማጥፋት ወንጀል ክስ ቀረበባቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከእምነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በረሃብ ከተረፉት መካከል 65ቱ ኬንያውያን ራስን በማጥፋት ወንጀል ክስ ቀረበባቸው።
መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ራሳቸውን ያስራቡት እነዚህ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከረሃብ ተርፈው በነፍስ አድን ማዕከል ውስጥ ቢገቡም ምግብ አንመገብም ብለው አሻፈረኝ ማለታቸው ተሰምቷል።
አቃቤ ህግ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ ከረሃብ በህይወት የተረፉት እነዚህ ግለሰቦች የአዕምሮ እና የህክምና ምዘና እስኪደረግላቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ አመልክቷል።
ምግብ አንበላም በማለታቸውም የነፍስ አድን ማዕከሉ እነሱን ለማቆየት እንደማይቻለውም ተገልጿል።
ለአቃቤ ህግ ጥያቄውም ፍርድ ቤቱ ከሰሞኑ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የብሪታንያ ቅኝ ገዥዎች ባወጡትና ኬንያ በምትተዳደርበት ህግ መሰረት የራስን ህይወት ማጥፋት ወንጀል ነው።
እነዚህ ህጎች በእንግሊዝ ከ60 ዓመታት በፊት የተወገዱ ሲሆን የኬንያ ተሟጋቾችም እነዚህ ህጎች እንዲቀሩ እየታገሉ ነው።
በህይወት የተረፉት 65ቱ ግለሰቦች የፓስተር ፖል ማኬንዚ ተከታዮች መሆናቸው ተነግሮላቸዋል።
ፓስተሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቹን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ በጾምና በረሃብ እንዲሞቱም አሳምኗቸዋል።
ፓስተሩ በሚንቀሳቀስበት የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ባለው ሰፊ የሻካሆላ ጫካ እስካሁን ድረስ ከ280 በላይ አስከሬኖች ጥልቀት በሌላቸው መቃብሮች ውስጥ ተቀብረው ተገኝተዋል።
ከነዚህ ውስጥ አስሩ በያዝነው ሳምንት ሰኞ ተቆፍረው የተገኙ ናቸው። የአስከሬን ምርመራ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ህፃናትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች በረሃብ ቢሞቱም አንዳንዶቹ ግን ታንቀው፣ ተደብድበውና ታፍነው እንደሞቱም ነው።
ይህ የአስከሬን ምርመራ ይፋ ያደረገው ውጤት የእምነት ቡድኑ አባላት ከገጠማቸው ሞት በተጨማሪ፣ ለሌሎች ሰዎች ሊተላለፉ ይችላሉ የሚባሉ የውስጥ የአካል ክፍሎችን የማውጣት እና የማዘዋወር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።












